ወታደር ያቆየው ታሪክ- ሉዓላዊነት

መከላከያ ሠራዊቱ በተለያዩ ጊዜያት የተሰጡትን ተልዕኮዎች በብቃት በመፈጸም አንጸባራቂ ድል ሲያስመዘግብ እንደቆ ሰሞኑን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ እዝ 74ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በተከበረበት ወቅት መገለጹ ይታወቃል፡፡ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የህይወት ዋጋ ጭምር እየከፈለ ያለው ይህ ሠራዊት ታሪኩ እንደምን ይገለጻል?

ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ መረጋጋት ያላትን ቁርጠኝነት የራስን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባሻገር በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ውስጥ በመሳተፍ ከፍተኛ ድል ማስመዝገብ መቻሏን ዓለም አቀፍ ተቋማትና የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ:: እንደ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ዳርፉር ባሉ አካባቢዎች ከፍተኛ ተሳትፎ አድርጋለች:: በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ሥራዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ከሚያደርጉት ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መሆኑም የሚታወቅ ነው:: በተለይም በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ (አሚሶም) ውስጥ የአልሸባብ አማፂያንን በመዋጋት እና የአፍሪካ ቀንድን በማረጋጋት ረገድ ሚናው ከፍተኛ ነው።

በተለያዩ ፈተናዎችና ስኬቶች ያለፈው የመከላከያ ሰራዊት ተቋሙ በለውጥ ንቅናቄ ሂደት የተጓዘባቸው መንገዶች ላይ ከከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ጋር የጋራ አረዳድ ለመፍጠር መድረክ በቅርቡ ሲካሄድ ፤ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ታሪክ ዋነኛ መሠረት ወታደር እንደሆነ ተናግረዋል:: ወታደር ሆኖ ማገልገል ትልቅ ክብር መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብቸኛ ህይወትን በመስጠት የሚከፈል መስዋዕትነት መሆኑንም አብራርተዋል::

“የሀገራችን ኢትዮጵያ ታሪክ መሠረቱ ወታደር ነው:: ኢትዮጵያ ስለምትባል ሀገር ደርዝ ያለው ታሪክ አንስተን የምንናገር ከሆነ ከውትድርና ታሪክ ብዙ አንርቅም” ነው ያሉት::

“ሀገር የሚባል ነጻነት ያለው፤ ድንበር ያለው በቅኝ ያልተገዛ ቢባል አሁን የምናውቀው ቅጥር የተፈጠረው በወታደር ነው:: ሉዓላዊነት የምንለው ወታደር ያቆየው ታሪክ ነው:: ነጻነት የምንለው ወታደር ያቆየው ታሪክ ነው:: ይህ በብዙ ዘርፍ ቢታይ የኢትዮጵያ ታሪክ ሲቀዳ ዋናው የሚገኘው ጉዳይ የወታደር ታሪክ ነው” ሲሉ ሠራዊቱ ያለውን የሀገር ወዳድነት ሞራል አብራርተዋል::

ኢትዮጵያ ስንል በውስጡ የምናየው ሀገሩን የሚወድ፤ ስለ ሰፈሩ ሳይሆን ስለ ሀገሩ የሚያስብ የሀገሩን ክብር በጥልቀት የሚያየ የወታድር ታሪክ ነው በማለት፤ ይህ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሲቪል አመራሮችም ለኢትዮጵያ ጊዜያቸውን እየሰጡ ስለመሆናቸው ጠቅሰዋል::

አይተኬ የሆነው የህይወት መስዋዕትነት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አንዴ ብቻ የሚገኝና ዳግም በእውቀትና በገንዘብ አቅም ማደስ የማይቻለውን ህይወት የሚገብረው ወታደር መሆኑን አንስተዋል:: ይህንን ወታደር የመውደድና የማክበር የሀገር ታሪክ አካል የማድረጉ ጉዳይ ይበልጥ እየሰፋ ልማድ እንዲሆን ወታደር ምንድነው የሚለውን ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወታደር የላቀ ዓላማ ሊኖረው እንደሚገባ በመግለጽ፤ ከሰፈር የዘለለ የላቀ ዓላማ ከሌለውና ለመስዋዕትነትም ዝግጁ ካልሆነ ወታደር ሊባል አይችልም ነው ያሉት::

የትኛውንም ተስፋፊ ኃይል የሚመክት ሠራዊት ተገንብቷል ሲሉ የገለጹት ደግሞ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ናቸው:: እርሳቸው ይህንን ያሉት በ47ኛው የምሥራቅ ዕዝ ምስረታ በዓል ላይ ያስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡

ተስፋፊነት የጦርነት ነጋሪት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ፤ ሠራዊቱ ኢትዮጵያን ለመውረር የሞከሩ ኃይሎች ለመመከት የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል:: “ሀገራችንን ለመውረር ግፊት ሲያደርጉና ግጭት ሲያባብሱ የነበሩ የሀገራችን ታሪካዊ ጠላቶች አብረው የቆሙ ቢመስሉም በሽንፈት ጊዜ እንደማይገኙ ከታሪክ መማር ይገባል” ነው ያሉት፡፡

ሠራዊቱ በቀጣናው ያለውን የተስፋፊዎች የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ ለመመከት የሚያስችል የተሟላ ወታደራዊ ቁመና ላይ እንደሚገኝና ሕዝቡ ላይ ስጋት ለመፍጠር የሚሞክሩ ተላላኪዎችን መስማት እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡

ውስጣዊ ችግሮች ቢኖሩም ሀገርን ከጥቃት ለመከላከል ብቻ ሳይሆን ከሞከሩ ዳግመኛ እንዳያስቡት አድርጎ ለመመከት የሚያስችል ዝግጁነት መኖሩን የተናገሩት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ በጦርና በጋሻ ታንክ በመመከት በነፃነት የቆየን የጀግኖች መገኛ መሆናችንን የምሥራቁ የሀገራችንን ድንበር ለመመከት ለዕዙ የሚደረግ ማንኛውንም ድጋፍ መከላከያ እንደሚያደርግ መላው የሀገራችንና የክልሉ ማህበረሰብ ለዕዙና ለሠራዊታችን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

በዓሉን አስመልክተው መልእክት ያስተላለፉት ጀኔራል አምባሳደር ባጫ ደበሌ፤ የምሥራቅ እዝ የሀገርን አንድነት ሰላምና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈሉን ገልጸዋል:: ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር ህይወታቸውን ጭምር መስዋዕት ለማድረግ ወደ ኋላ የማይሉ የሠራዊት አባላት መኖራቸውንም ነው የጠቀሱት::

በተለይም ምሥራቅ ዕዝ የተቋቋመው የሶማሊያን ወረራ ለመከላከልና የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር እንደሆነ የጠቀሱት ጀኔራል አምባሳደር ባጫ፤ ዕዙ የተሰጠውን ሀገርን የማስከበር ተልዕኮ በታላቅ ጀግንነትና በትጋት በከፈለው መስዋዕትነት ከሌሎች አሃዶችና ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን ወራሪውን ኃይል አሳፍሮ መመለስ እንደቻለ አብራርተዋል:: ምሥራቅ እዝ በሀገር ውስጥ በተለይም በምሥራቅ ኢትዮጵያ በሐረሪ፣ ሱማሌ፣ ኦጋዴን እንዲሁም በምሥራቅና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች፣ አርሲና ባሌ አካባቢዎች ላይ ይፈጠሩ የነበሩ ከፍተኛ የጸጥታ ችግሮችን በወሰደው ተከታታይና እልህ አስጨራሽ የጸረ ሽምቅ ተጋድሎ አካባቢዎቹ አሁን ላይ ለሚገኙበት ሰላምና ዕድገት የራሱን አስተዋጽኦ የተወጣ መሆኑን አንስተዋል::

የኤርትራን ወረራ ተከትሎ ወደ ቡሬ የተንቀሳቀሰው ምሥራቅ ዕዝ ከሌሎች አጋር እዞችና ክፍሎች ጋር ተሳስሮ የተቃጣውን ወረራ ድል በማድረግ ወደ ሰላም ስምምነት እንዲመጣ ያደረገ የሀገር ዋልታና ማገር መሆኑን ጀኔራል አምባሳደር ባጫ ተናግረዋል:: የሀገርን ሰላምና ሉዓላዊነት ከማስከበሩም ባሻገር በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ተሰማርቶ የሶማሊያን ሕዝብና መንግሥት ከአልሻባብና ከሌሎች ጥቃቶች በመከላከል ከፍተኛ የሆነ መስዋዕትነት በመክፈል ድል ያስመዘገበ ነው ያሉት::

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You