– በለውጡ ዓመታት ያጋጠሙትን ውስብስብ ችግሮች በሕዝቡ ትብብር መቋቋም ተችሏል
አዲስ አበባ፡– ባለፉት የለውጥ ዓመታት ያጋጠሙትን ውስብስብ ችግሮች በሕዝቡ ትብብርና በአመራሩ ቁርጠኝነት መቋቋም መቻሉን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ። አምስቱ የጷጉሜን ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች ተከብረው እንደሚውሉ ተመላክቷል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የ2016 ዓ.ም የጷጉሜን ቀናትን ስያሜና አከባበር በተመለከተ በትናንትው ዕለት መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ደሲሳ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ ከነበረችበት አዙሪት ያሻገሩና ታሪክ ቀያሪ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሀገርን ሊያጠፋ የሚችል ጦርነት፣ ግጭቶችና የውጭ ሀገር ጫናዎች ያጋጠሙ ቢሆንም በሕዝቡ ትብብርና በአመራሩ ቁርጠኝነት በመቋቋም የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት ማጽናት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በጠላቶች ምኞትና ፍላጎት ሳትፈርስ ከበፊቱ በተሻለ ደረጃ ላይ መቆም ችላለች ያሉት አቶ ከበደ፤ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በተወሰዱ ርምጃዎች በተለይ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል አጋጥሞ የነበረውን አውዳሚ ጦርነት በሠላማዊ መንገድ እንዲቋጭ መደረጉን አስገንዝበዋል፡፡
መቼም ሊሳካና ሊጠናቀቅ አይችልም ሲባል የቆየው የኢትዮጵያውያን የጋራ ዐሻራ የሆነው የህዳሴ ግድብም ኃይል ማመንጨት የጀመረው ባለፉት የለውጥ ዓመታት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የለውጡ ዓመታት አምራች ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው የሚያመርቱበትን ምቹ ሁኔታ የተፈጠረበት፣ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን የለሙበት፣ ኢትዮጵያ ከምትታወቅበት ስንዴ ልመና ወጥታ በስንዴ ራሷን የቻለችበት እና ሌሎች በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል አምስቱ የጷጉሜን ቀናት አብሮነትን በሚያጎለብቱ መልካም ተግባራት ለማክበር ታቅዷል ያሉት አቶ ከበደ፤ በዚሁ መሰረት ጷጉሜን 1 የመሻገር ቀን፣ ጷጉሜን 2 የሪፎርም ቀን፣ ጷጉሜን 3 የሉዓላዊነት ቀን፣ ጷጉሜን 4 የኅብር ቀን፣ ጷጉሜን 5 የነገ ቀን በሚል ስያሜ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበሩ አስታውቀዋል።
ጷጉሜን 1 ቀን ባለፉት የለውጥ ዓመታት በህዳሴ ግድብ፣ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በኢትዮጵያ ታምርትና በሌሎች ሥራዎች የተገኙ ስኬቶችን ለማሳየት እና ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት በቀጣይ ዓመት የተሻለ ስኬት ለማስመዝገብ መሆኑን አስረድዋል፡፡
ጷጉሜን 2 ቀን የሀገሪቱን ተቋማት ለማዘመን፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት፣ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ፣ የተጀመሩ የተቋም ግንባታና የሪፎርም ሥራዎችን አጠናክሮ በሚያስቀጥል መልኩ ይከበራል ብለዋል።
ጷጉሜን 3 ቀን ግጭቶችና የሀገርን ሉዓላዊነት በሚያስከብሩ መርሐግብሮች የሚከበር ሲሆን፤ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያሳትፍ የብሔራዊ መዝሙር የመዘመር እና የሀገሪቱን የሰንደቅ ዓላማ የመስቀል መርሐግብር እንደሚከናወን ገልጸዋል።
ጷጉሜን 4 ቀን ኅብረተሰቡ በማንነት በቋንቋ፣ በብሔርና በሃይማኖት ሳይለያይ የአብሮነት እሴትን በማጉላት እንደሚከበር ተናግረዋል።
ጷጉሜን 5 ቀን የነገን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና ማኅበረሰቡ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርጉ በሚጠቁሙ መርሐግብሮች እንደሚከበር ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የተጀመረ የኮሪደር ልማት እና ሌሎች የነገ ትውልድን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል፡፡
አምስቱም የጷጉሜን ቀናት በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ በፌደራል ተቋማት፣ በውጭ ሀገር በሚገኙ የሀገሪቱ ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶችና በማኅበረሰቡ ዘንድ በድምቀት እንደሚከበሩ አመላክተዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የጷጉሜን ቀናት የዜጎችን አንድነትና አብሮነት በሚያጎላ መልኩ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት መከበራቸውን ይታወሳል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም