አዲስ አበባ፡- 100 የኤሌክትሪክ የከተማ አውቶብሶች በግዥ ሂደት ላይ መሆናቸውን የአዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አካሉ አሰፋ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የአዲስ አበባን ከተማ ትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ድርጅቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሠራ ይገኛል፡፡
አሁን ባለው መረጃ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ 100 የኤሌክትሪክ የከተማ አውቶብሶች በግዥ ሂደት ላይ ነው ብለዋል ፡፡
የአውቶብሶቹ ወጪ ሙሉ በሙሉ በከተማ አስተዳደሩ የተሸፈነ መሆኑን ያነሱት አቶ አካሉ፤ ግዥው ተጠናቆ ወደ ሀገር ሲገቡም በቀጥታ ወደ ስምሪት እንደሚገቡም ተናግረዋል፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ የአውቶብሶቹ የግዥ ሂደት በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆኑን ጠቁመው፤ ግዥው ተጠናቆ የኤሌክትሪክ አውቶብሶቹ ወደ ሥራ ሲገቡም የነዳጅ ወጪን የሚያድኑ እና የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድም ከፍተኛ አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
የኤሌክትሪክ አውቶብሶቹ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሙላት (ቻርጅ ለማድረግ) በሸጎሌና እና በቃሊቲ የተገነቡት መሠረተ ልማቶች ወሳኝ መሆናቸውን ያነሱት አቶ አካሉ፤ በቀጣይም በርከት ያሉት ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከሎችን ለመገንባት እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡
በዓለም ላይ ያለው የኤኤክትሪክ መኪናዎች ዋጋ ከፍተኛ ቢሆንም የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል፣ የነዳጅ ፍጆታን ከመቀነስ እንዲሁም ለጥገና የሚወጣን ከፍተኛ ወጪ ከመቀነስ አንጻር ጥቅማቸው እንደሚያመዝንም ገልጸዋል፡፡
አቶ አካሉ፤ ድርጅቱ 30 በመቶ የሚሆነውን የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ በመስከረም ወር ተማሪዎች ትምህርት የሚጀምሩበትና የተለያዩ እንቅስቃሴዎች የሚጨምሩበት ጊዜ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ አውቶብሶችንና አገልግሎት ያቆሙ አውቶብሶችን በማደስ ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ ነው። በዚህ የክረምት ወቅትም በልዩ ሁኔታ የእድሳት ፕሮጀክት በመንደፍ ጥገና ላይ ትኩረት ተሰጠቶ በመሥራት በርካታ አውቶብሶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡
70 የተማሪ አውቶብሶች በድርጅቱ ይገኛሉ ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ያለውን የወላጅ ፍላጎት በማገናዘብ ለማሰማራት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ አውቶብሶች እንዲሁም የተማሪ አውቶብሶችን (ባሶችን) ያለውን የተገልጋይ ቁጥር እንዲመጣጠን በማድረግ የትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም