የአፍሪካን ልማት ወደፊት የሚያራምደው ፎረም

ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ተደርጋ ትወሰዳለች፡፡ በተለይ ታላቁን ዓድዋ ድል ተከትሎ በርካታ የአፍሪካና ሌሎች ጥቁር ሕዝቦች ኢትዮጵያን የነፃነታቸው ተምሳሌት በማድረግ ነፃነታቸውን ለማስከበር አርዓያ አድርገው ተከትለዋታል፤ ስኬትም አስመዝግበዋል፡፡ በዚህ መነሻነትም የአፍሪካ ሀገራትን በአንድ ላይ ያሰባሰበው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሠረት ምክንያት ሆናለች፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተመሠረተ በኋላ በርካታ ተግዳሮቶች ቢገጥሙትም ስኬት ያስመዘገበባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ በተለይ የአፍሪካ ኅብረት መመሥረትን ተከትሎ አፍሪካውያን አሕጉራቸውን የበለፀገና ለዜጎቹ ምቹ ለማድረግ በርካታ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ከዚህ ጥረታቸውም ውስጥ አንዱ አጀንዳ 2063ን በመቅረጽ አሕጉሪቱን በተለያዩ ዘርፎች ስኬታማ ለማድረግ ያደረጓቸው ጥረቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሰሞኑንም ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ለማዘጋጀት ዝግጅት ስታደርግ ቆይታ በትናንትናው እለት ድግሷን ለታዳሚዎቿ አቅርባለች። በዚህ የመክፈቻ መርሐግብር ላይም ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ እንግዶች የተሳተፉ ሲሆን በርካታ ጥናቶችም ቀርበው ውይይቶች ተደርገዋል፡፡

“ዘላቂ የከተሞች ልማት ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063” በሚል መሪ ቃል በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተካሄደው የመክፈቻ ንግግር ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እንደተናገሩት በአዲስ አበባ ከተማ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም የአሕጉራችንን ልማት ወደፊት ለማራመድ የጋራ ቁርጠኝነትን የምናሳይበት ነው፡፡

አቶ ተመስገን፤ የምንፈልጋትንና የበለፀገች አፍሪካን ለመፍጠር “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” በሚለው የኢትዮጵያውያን ምሳሌያዊ ንግግርን መሠረት በማድረግ በጋራ ልንሠራ ይገባል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአጀንዳ 2063 የተቀመጡ እሳቤዎችን ለማሳካትና እያጋጠሙን ያሉ አሕጉራዊ ችግሮችን ለመፍታት ወቅቱ የሚፈልገውን ተለዋዋጭ የፖለቲካ ስልትና ጠንካራ ውሳኔ ማሳለፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪኮች ባለቤትና ዲፕሎማሲያዊ ልምዶች ያላት ሀገር ናት፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካን እሳቤዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ከመቼውም በበለጠ ቁርጠኛ እንደሆነች በማንሳት፤ በአሕጉር ደረጃ የኢኮኖሚ ትስስር፣ የመሠረተ ልማት እድገትና ፖለቲካዊ አንድነት በመፍጠር የተቀናጀ የአፍሪካ ክትመትን እውን ለማድረግ ፎረሙ ልዩ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ ከተማ በመከናወን ላይ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ መሆናቸውን በመግለጽ፤ ከተማዋን አረንጓዴ፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ፅዱ ተስማሚ የአየር ሁኔታ እንዲኖራት የማድረጉ ተግባር ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሠራበት እንደሚገኝ አውስተዋል።

የመንግሥትና የሕዝብን አቅም በማስተባበር ሰው ተኮር የልማት ተግባራትን በማከናወን ከተማዋን መለወጥና ማልማት እንደተቻለ ያነሱት ከንቲባዋ፤ የተማሪዎችና ማኅበረሰብ ምገባዎች፣ የቀዳማይ ልጅነት፣ የሴቶች የተሐድሶና የክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከላት ግንባታና የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራን ጨምሮ ሌሎችም ሥራዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደ ከንቲባዋ ገለፃ፤ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ከማደስና ገጽታዋን ከመለወጥ ባሻገር ዘመናዊ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት ለተሽከርካሪዎች ብቻ ሳይሆን ለእግረኞችና ለብስክሌተኞች ምቹ መጓጓዣዎችን አሟልቶ የተገነባ ነው፡፡

እንዲሁም የሕዝብ መናፈሻ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ፓርኮችንና የአረንጓዴ ልማቶችን አካቶ የተሠራ ነው። ከዚህም ባለፈ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች ሥራ ዕድል በመፍጠር ለከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ መነቃቃት ምክንያት መሆኑን ከንቲባዋ አብራርተዋል፡፡

የከተሞች እድገት የራሱ በጎና አሉታዊ ጎኖች እንዳሉት በመጥቀስ፤ ይህ ፎረም ይህንን ወደመልካም አጋጣሚ በመቀየር ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን የገለጹት ደግሞ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ናቸው፡፡

አፍሪካ እንደአሕጉር በርካታ የከተማነት አጀንዳዎች አሏት ያሉት ሚኒስትሯ፤ ከተሞች ሲስፋፉ በቂ የመሠረተ ልማት መስፋፋት እጅጉን አስፈላጊ ነው። ከተሞቻችንን ለማሻገርና ለዜጎች ምቹ መኖሪያ እንዲሆኑ ለማድረግ በጋራ መሥራት አለብን ብለዋል።

በአፍሪካ ፈጣን የከተሞች እድገት እየተስተዋለ ይገኛል። በዚህም በዓመት በአፍሪካ 3 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሁም በኢትዮጵያ 5 ነጥብ 4 በመቶ የከተሞች እድገት እንደሚታይ ገልጸው፤ እድገቱ የከተማና የገጠር ምጥጥንን የሚቀይር ማሳያ እንደሆነ አብራርተዋል።

ፎረሙ በአፍሪካ ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በትብብርና በቅንጅት ለመፍታት የድርሻችንን የምንወጣበት ነው። ለአፍሪካ 2063 አጀንዳ እውን መሆን የከተሞችን ዘላቂ ልማት ማረጋገጥና የክትመት ምጣኔውን ማጣጣምና ለዚህም መሥራት ይገባል ሲሉ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በአፍሪካ እየጨመረ ላለው የሕዝብ ቁጥርና የአየር ንብረት ተፅዕኖ ምላሽ መስጠት የሚችል የከተሞች ዘላቂ ልማት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ከተሞች ፅዱና ለነዋሪዎች ምቹ በማድረግ ምሳሌ የሚሆኑ ሥራዎችን እያከናወነች መሆኑን ተናግረዋል።

ፎረሙ በቀጣይ ቀናት በተለያዩ ሁነቶች ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን አፍሪካውያን በአንድ አቋም የክትመት ምጣኔን የሚያጤኑበት፣ በአፍሪካ የክትመት ምጣኔና የከተማ ልማት መዋቅራዊ መፍትሄዎች ላይ የጋራ አቋም የሚያንጸባርቁ ውሳኔዎች ይፀድቁበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You