ሆስፒታሉን የምርምርና የትምህርት ልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ፣ በምርምርና በትምህርት የልህቀት ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየሠራ መሆኑን አስታወቀ።

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የሕክምና ኮሌጅ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲሳይ ስርጉ (ዶ/ር) በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ተቋሙን በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ፣ በምርምርና በትምህርት የልህቀት ማዕከል ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት ከግብ ለማድረስ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

ለኅብረተሰቡ የሚቀርበውን የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል እና የሆስፒታሉን የአስተዳደር ልህቀትን እውን ለማድረግ የተለያዩ ግንባታዎችን እንዲሁም የማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።

ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ለአንጀት፣ ለጉበት፣ ለካንሰር እና ለልብ ሕክምና ማዕከላት የሚያገለግሉ የሦስት አዳዲስ ሕንፃዎችን ግንባታ በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ዶክተር ሲሳይ ገልጸዋል።

ማዕከላቱ በሆስፒታሉ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማስፋትና ጥራት ለመጨመር እንዲሁም የሕክምና አገልግሎት መስጫ ቦታ ጥበት እንዳይከሰት የሚረዱ መሆናቸውን አንስተዋል።

ዋና ሥራ አስኪያጁ እንዳመለከቱት፤ ማዕከላቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ በአጠቃላይ 110 የሕክምና አልጋዎች ሲኖራቸው በከፍተኛ ቴክኖሎጂ እንዲደራጁ ይደረጋል።

ሆስፒታሉ ከማዕከላቱ ግንባታ ባለፈ የጤና አጠባበቅ አገልግሎቱ ላይ ልዩ ልዩ ማሻሻያዎች ማድረጉን ጠቁመው፤ በተቋሙ ቀዶ ጥገና ተሠርቶ ሌላ ታካሚ ለማስገባት የሚወስደውን ጊዜ ከ30 ደቂቃ ወደ 15 ደቂቃ ማውረድ መቻሉን ገልጸዋል። ይህም በርካታ ታካሚዎችን ለማስተናገድና የተገልጋይን እርካታ ለማሳደግ አግዟል ብለዋል።

በተጨማሪ በሆስፒታል ተመላልሰው የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙ ሰዎች በአካል ከመምጣት ይልቅ በቤታቸው ሆነው በነፃ የስልክ ጥሪ የሕክምና ውጤታቸውንም ማግኘት እና ቀጠሮ ማስያዝ እንዲችሉ ተደርጓል ሲሉ አስታውቀዋል። ሆስፒታሉ 13 የላብራቶሪ አገልግሎት ፈቃድ ስላለው የእውቅና ሥርዓት ውስጥ እንዲገባ ለማስቻል በቀጣይ ይሠራል ብለዋል።

ለታካሚዎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ ከስፔሻሊስቶች፣ ከአገልግሎት መስጫ ቦታዎች ጥበትና ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር ተያይዞ ውስንነቶች ነበሩ፤ ግንባታ ላይ ያሉት ሦስቱ ሕንፃዎች በ2017 ዓ.ም ለአገልግሎት ሲበቁ ለችግሮቹ ምላሽ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ በአጠቃላይ አራት ሺህ 350 ሠራተኞች አሉት፤ ከዚህ መካከል 300ዎቹ የሕክምና ስፔሻሊስቶች ናቸው።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2016 ዓ.ም

Recommended For You