አንዳንዶች ፋሽን እና ምቾት የማይነጣጠሉ ናቸው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ በቀጥታ ከውበት ጋር ያገናኙታል። ሰዎች ወደ ስራም ሆነ አንድ ጉዳይ ለመከወን ከቤታቸው ሲወጡ አለባበሳቸው ለቦታው የሚመጥን እንዲሆን ያደርጋሉ። ውሏቸው ምን እንደሚመስል ከገመገሙ በኋላ ከልብሳቸው ባሻገር የሚያደርጉት ጫማ ከቀን ውሏቸውና ካላቸው ፕሮግራም ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል እንዲሆን ያደርጋሉ።
ታዲያ ሴቶች አብዝተው የሚጠቀሙበትና ቁመትን ከፍ የሚያደርገው ሒል ጫማ በተለምዶው ‹‹ታኮ ጫማ›› ለአንዳንዶች የእለት ተዕለት ምርጫ ሲሆን ጥቂት ለማይባሉ እንስቶች ደግሞ ከእለታት በአንዱ ቀን ብቻ የምታደርገው ይሆናል። ሒል ጫማ እንስቷ ለዚያን ቀን ምርጫዋ ባደረገችው ልብስ ላይ ውበትን የሚጨምር ሲሆን በምትራመድበት ወቅትም በራስ መተማመንን የሚያላብስ መሆኑን ሰዎች ይገልጻሉ።
ይህ ቁመትን ረጅም፤ አለባበስንም ለየት አድርጎ የሚያሳየው ሒል ጫማ ከተለመደው የእለት ተዕለት ጫማ ከፍ ያለ ነው። ቀለል ካለው የሒል ጫማ ዓይነት እጅግ ረጅም መስሎ የሚታይ እና በሌሎች ሰዎች እይታ ዘንድ ከአሁን አሁን ወደቁ የሚል መሳቀቅን የሚፈጥር ከፍታ ያላቸውን ጫማዎች ምርጫቸው የሚያደርጉ እንስቶች አሉ። እነዚህ ከፍ ያሉ ጫማዎችን ቢያንስ ከልክ በላይ ረጅም እና ለተረከዝ ምቾት የማይሰጥ ከሆነ ለጤና መልካም እንዳልሆነ ይገልጻሉ።
ከ16 በላይ የተለያዩ የሒል ጫማዎች ሲኖሩ በአጠቃላይ ግን ባላቸው የከፍታ መጠን ረጅም (ከፍ ያለ)፣ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ከፍታ ያላቸው ተብለው ይለያሉ። ‹‹Ally Shoes›› በሚል መጠሪያ የተለያዩ የሴቶች ጫማዎችን ወደ ገበያ በተለያዩ የራሱ ድህረ ገጾች እና መገበያያዎች የሚያቀርበው ተቋም በሴቶች ተመስርቶ ለሴቶች ምቹና ከህመም ነፃ የሆኑ ከፍታ ያላቸው ጫማዎችን ያቀርባል። ይህንንም ለማድረግ የሚያስችል የተለያዩ የራሱ ዲዛይነሮች በኩባንያው ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ ዲዛይን የሚያደርጓቸው ሒል ጫማዎችም በአዕምሮ ንብረት በኩባንያው ስም የተመዘገቡ ናቸው። ኩባንያው የሚያቀርባቸው ጫማዎች በይበልጥ ምቾትን እና ውበትን አጣምረው የያዙ ሲሆን በአራት የተለያዩ አማራጭ በተለያየ ከፍታ መጠን ያላቸውን ያቀርባል።
አንድ ሒል ጫማ ለምትጫማው እንስት ምቾት እንዲኖረው ጫማው የሚኖረው ከፍታ ብቻ ሳይሆን በውስጥ ያለው ምቾትም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው። ይህ ጥያቄ በሒል ጫማ ብቻም ሳይሆን በሌሎች የጫማ ዓይነቶች ላይም ደንበኞች የሚመርጡትን የጫማ መሸጫ የረጅም ጊዜ ደንበኛ እንዲያደርጉትም ሆነ ደንበኝነታቸው እንዲቋረጥ የሚያደርግ ነው።
ታዲያ በርካታ የሒል ጫማዎች ሲኖሩ የዚህ ጫማ አድናቂና ወዳጅ የሆኑ እንስቶች ቀጭን የሆነ ቅርጽ ያለው መካከለኛ እና ዝቅተኛ የሚባል የከፍታ መጠን ያላቸውን ጫማዎች በሥራ ቦታቸው ያዘወትራሉ። ሌላኛው በሥራ ቦታም ሆነ ከዘወትር የአለባበስ ፋሽን ጋር አብሮ የሚሄድ እና ምቾትን የማይነፍገው ጫማ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ሲሆን፣ ሒል ጫማ ማድረግ ያልለመዱ ሰዎች በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ቢያደርጉት በቶሎ ሊለምዱት የሚችሉት እና ቀጭን የሆነ ቅርጽ ያለው ሒል ጫማ ምቾት ለማይሰጣቸው እንስቶች የመጀመሪያ ምርጫ ነው። ሌላኛው የሒል ጫማ ዓይነት ከፍ ያለ ጫማ ምቾት ለማይሰጣቸው አልያም በምቾት ለመራመድ ምቹ ቦታዎችን ለሚፈልጉ ሰዎች የተዘጋጀው የጫማ ዓይነት ከኋላ የራሱ ማሰሪያ ያለው እና መጠነኛ ቀጭን ቅርጽ ወይንም በአራት ማዕዘን ዲዛይን የተሰራ ነው። ይህ የጫማ ዓይነት በአሁን ሰዓት እንደ ፋሽን ተደርጎ በተለያየ ዓይነት እና ብራንድ በገበያው ላይ ይገኛል።
በ ‹‹Ally Shoes›› የሒል ጫማ ገበያ ላይ እነዚህን ሌሎች በርካታ የጫማ ዓይነቶች በመጠን እና ባላቸው የከፍታ ዓይነት እና በቀለም በርከት ብለው ይገኛሉ። አብዛኛዎቹ በ ‹‹Ally Shoes›› የሚገኙ ሒል ጫማዎች ከቆዳ የተሰሩም ጭምር ናቸው።
ታዲያ አንዲት እንስት ሒል ጫማ በተለምዶው አጠራር ደግሞ ታኮ ጫማ ምቹ የሆነ ቀን እንዲኖራት ከምትገዛው ጫማ ጥራት፣ ከምትገኝበት ቦታ ባሻገር እንደተለመደው ዓይነት አረማመድ ላይኖራት ይችላል። ነገር ግን በቀኗ ውስጥ ሒል ጫማ ያደረገች እንስት በምትራመድበት ወቅት ከፊት ለፊተኛው የእግሯ ክፍል ይልቅ መሬት ላይ የምታሳርፈው ተረከዟ የሚያርፈበትን የጫማ ክፍል ቢሆን ይመረጣል። ይህም አረማመድ ሚዛኗን እንድትጠብቅ ይረዳታል፤ በተጨማሪም በምትራመድበት ወቅት በመድረክ ላይ ልብስ የሚያስተዋውቁ ሞዴሎች የሚከተሉትን ዓይነት አካሄድ ማለትም እግሯን ከፊት እያስቀደመች እና ሌላውን እያስከተለች ብታደርገው በአረማመዷ እንዳልሰጋች አልያም መተማመን ያላት መሆኑ ያሳብቃል።
ሌላኛው ጥንቃቄ የሚፈልገው ስፍራ የተለያዩ ደረጃዎችን በሚጠቀሙበት ጊዜ ነው። ደረጃን በምትወጣበት ጊዜ የእግሮቿን ጣቶች በማስቀደም ብትጓዝ የተሻለ ሲሆን በምትወርድበት ጊዜ ደግሞ በደረጃው ላይ ሙሉ ለሙሉ እግሯን በማሳረፍ መጠቀም ትችላለች። በየቀኑ ሒል ጫማ ማድረግ በጉልበት አካባቢ እና በጀርባ ላይ ጫና የሚያሳድሩ በመሆናቸው በሚያደርጉበት ጊዜ ከሚኖራቸው እንቅስቃሴ ጋር የተጣጣመ፣ የጫማዎቹ ጫፍ ላይ ምቾት የሚሰጡ አራት ማዕዘን ጌጦችን ማስደረግ፣ የጫማዎቹን ሶል ለእግራቸው በሚመች መልኩ ማሰራት እና በአብዛኛው ከፍታ ያላቸውን ሒል ጫማዎች የሚጠቀሙበትን ቀን መገደብ ይመከራል።
የሒል ጫማ ዓይነቶች ከላይ በተጠቀሱት ባላቸው ቁመት ብቻ ሳይሆን ጫማዎቹ ከፊት ለፊት ያላቸው ዲዛይን እና የቀለም ዓይነት እንዲሁ ገዢዎች ከምርጫቸው ውስጥ የሚያስገቡት ነው። ከፊት ለፊታቸው ክፍት እና የእግር ጣትን የሚያሳዩ ሲሆኑ የተለመዱ የሚባሉ የሒል ጫማ ቀለሞች ደግሞ ከማንኛውም የልብስ ቀለም ጋር አብረው የሚሄዱ ጥቁር፣ ነጭ እና ደማቅ የማይባል ቀለም ያለው ጫማ ተመራጭ እና ሴቶች ቢኖራቸው የሚመከሩ የጫማ ዓይነቶች ሲሆኑ የሰዎች የቀለም ምርጫ የተለያየ በመሆኑ ሌሎች የቀለም አማራጮችም በገበያው ላይ ይገኛል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም