የዓባይ ግድብ በዘመናት መካከል ከመጣበት ተግዳሮት አኳያ በዚህ ትውልድ ተገንብቶ ወደ ሥራ እየገባ ያለበት እውነታ፤ በርግጥም ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ፣ በአንድ መንፈስ እና መነቃቃት ከተነሱ፣ ታሪክ ከመሥራት የሚያግዳቸው ምንም ነገር እንደማይኖር በተጨባጭ ያመላከተ፤ መጪዎቹን ትውልዶች የይቻላል መንፈስ የሚያላብስ ትልቅ ሀገራዊ ስኬት ነው።
ግንባታ ገና ከጠዋቱ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈ፤ በተለይም ግብጽ የወንዙ ብቸኛ ተጠቃሚ ለመሆን የሄደችበት ዘመን ያለፈበት የሴራ መንገድ፤ ለግንባታው የሚያስፈልገውን ሀብት በማፈላለግ ሂደት ሆነ በራሳችን አቅም ግድቡን ለመገንባት ለጀመርነው ሀገራዊ ንቅናቄ ትልቅ ፈተና ነበር።
ቅኝ ገዥዎች የግብጽን ሕዝብ ሆነ የተፋሰሱን ሀገራት ፍላጎት ፤ በተለይም የወንዙን ውሃ ከዘጠና ከመቶ በላይ የምታመነጨውን የኢትዮጵያን ይሁንታ /ተሳትፎ ያላካተቱ ስምምነቶች አቅም አግኝተው፤ በዚህ ፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነት ዓለም አቀፍ መርህ በሆነበት ዘመን ተግባራዊ እንዲሆኑ ብዙ ርቀት ተጉዛለች።
ኢትዮጵያውያንን ድንበር ተሸጋሪ የውሃ ሀብታቸውን ፍትሐዊ በሆነ መልኩ የማልማት ዓለም አቀፍ መብቶቻችውን ተጠቅመው ፤ ዛሬ ላይ እንደ ሀገር ከሚታወቁበት ድህነት እና ኋላቀርነት ለመውጣት የጀመሩትን ትግል ፤ትግሉ በተጨባጭ ያመጣውን ተስፋ ለመቀልበስ ሰፊ ጥረት አድርጋለች።
ባላቸው አቅም ሁሉ አበዳሪ ሀገራት እና ተቋማት እራሳቸው እንገዛለታለን ከሚሉት ዓለም አቀፍ ሕግ እና መርህ ውጪ ለግንባታው ብድር እንዳይሰጡ ፈተና ሆናለች፤ ከዚህም ባለፈ በራሳችን አቅም ግድቡን ለመገንባት የጀመርነውን ጥረት ለማደናቀፍም ያልፈነቀለችው ድንጋይ አልነበረም።
ከዛቻ ጀምሮ የተለያዩ ሀገራትን በተሳሳተ መንገድ ከጎኗ አሰልፋለች ፤ በጸጥታው ምክር ቤት የግድቡ ግዳይ አጀንዳ እንዲሆን ሰፊ ጥረት አድርጋለች፤ በቅርቡ በአደባባይ ይፋ እንደሆነው የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑ ግለሰብን በጥቅማ ጥቅሞች /በሙስና በመደለል አጀንዳው የምክር ቤቱ አጀንዳ እንዲሆን ባልተገባ መንገድ ተጉዛለች።
በርግጥ ይሕን የግብፅ የተሳሳተ፤ በዘላቂነት ማንንም ተጠቃሚ ማድረግ የማይችል ከዘመኑ የተጣላ አስተሳሰብ አሸንፎ ፤የግድቡን ግንባታ እውን ማድረግ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት የቱን ያህል ፈተና ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ፤ ምን ያህል ትግስት እና ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ መገመት የሚከብድ አይደለም።
የዚህን ግድብ ግንባታ ሀገር በብዙ የውስጥ እና የውጭ ፈተናዎች ውስጥ ሆና፤ እራሱ ግንባታው በውስብስብ ችግሮች ወደ መቆም በደረሰበት ትናንታዊ ሁኔታ ውስጥ፤ ዛሬ ላይ ወደ ግንባታው የመጨረሻ ምእራፍ ማድረስ እንደ ሀገር ችግሮችን ተቋቁሞ መሻገር የሚያስችል ሀገራዊ አቅም እየገነባን መሆኑን አመላካች ነው።
በተለይም እንደሀገር እየተፈጠረ ያለው የለውጥ አመራር እና በአመራሩ በኩል የሚታየው ቁርጠኝነት፤ በችግሮች ውስጥ ከመቆዘም ይልቅ መፍጥሄ የማፈላለግ፤ ከችግሮች ከፍ ብሎ የማሰብ የአመራር ባህል እየዳበረ መምጣቱን የሚያመላክት ነው።
አሁናዊው የዓባይ ግድብ ግንባታ ስኬታችን አንድም፣ በብዙ መልኩ አይቻልም በሚል በዘመናት መካከል ያስቆዘሙንን ችግሮቻችንን ተመልሰን በይቻላል መንፈስ አሸንፈን እንድንሻገራቸው የሚያስችለን፤ ከዚህም ባለፈ እንደ ትውልድ የራሳችንን የታሪክ ዐሻራ አኑረን እንድናልፍ ከፍ ያለ መነቃቃት የሚፈጥርልን ነው።
በተለይም አሁን ላይ ድህነትን ታሪክ አድርገን ለማለፍ እንደ ትውልድ በጀመርነው ሁለንተናዊ የልማት ጉዞ ውስጥ ሊያጋጥሙን የሚችሉ ፈተናዎችን በይቻላል መንፈስ በጽናት ታግለን በማሸነፍ፤ የተመኘነውን ሀገራዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚኖረው አስተዋጽኦ “አልፋ እና ኦሜጋ “ እንደሚሆን ይታመናል።
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም