
ዜና ትንታኔ
የተባበሩት መንግሥታት የትራፊክ አደጋ ሞትን በ2020 ዓ.ም በ50 በመቶ ለመቀነስ እቅድ አውጥቷል፡፡ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ኮንቬንሽንና የአፍሪካ ቻርተርንም ፈራሚ እንደመሆኗ የትራፊክ አደጋ መከላከያ ስታንዳርዶችን በማስጠበቅ ሞትን ለመቀነስ ቃል ከገቡ የዓለም ሀገራት አንዷ ናት፡፡
አደጋውን ለመከላከል የተሻለ ንቅናቄ እየተፈጠረ ቢገኝም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ አደጋ ከሚደርስባቸው ሀገራት ተርታ ትመደባለች፡፡
በ2016 ዓ.ም 46 ሺህ 571 የተሽከርካሪ አደጋ ሲከሰት፣ ሶስት ሺህ 111 ሞት ተመዝግቧል፡፡ አምስት ሺህ 581 ከባድ አካል ጉዳት መድረሱንም የመንገድ ደህንነት እና መንገድ ፈንድ መረጃ ያመለክታል፡፡
አጠቃላይ ሞት በ2015 ዓ.ም ሶስት ሺህ 577 የነበረ ሲሆን ከዘንድሮ ጋር ሲነጻጸር በ262 ቀንሷል፡፡ በንብረት ላይ የደረሰው ውድመት ግን ከአምናው ከእጥፍ በላይ ጨምሮ አራት ቢሊዮን ብር እንደሚገመት የመንገድ ደህንነት እና መንገድ ፈንድ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ጀማል አባሶ ይናገራሉ፡፡
በ2015 ዓ.ም አምስት ሺህ 818 ከባድ አካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ የደረሰው የተሽከርካሪ አደጋም 37 ሺህ አካባቢ፣ በንብረት ላይ የደረሰው ውድመት ደግሞ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ገደማ ይገመት እንደነበረም አቶ ጀማል ይጠቁማሉ፡፡
ለመሆኑ በኢትዮጵያ የሚከሰተውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ምን መደረግ ይኖርበታል?
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ጌቱ ሰኚ (ዶ/ር)፤ የአሽከርካሪዎች ጥንቃቄ ጉድለት፣ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ጉድለትና የመንገዶች አለመመቸት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለትራፊክ አደጋ መንስኤ ከሆኑት መካከል ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡
የተመደበውን የፍጥነት ወሰንን ጠብቆ አለማሽከርከር፣ ጠጥቶ ማሽከርከርና ተንቀሳቃሽ ስልክ እያናገሩ ማሽከርከርም ለአደጋው በምክንያትነት ይጠቅሳሉ፡፡
የጥንቃቄ ቀበቶ አለመጠቀምና እያሽከረከሩ ጫት በመቃም ረጀም ሰዓት ማሽከርከር ለሚደርሱ አደጋዎች በመንስኤነት እንደሚቀመጡም ይገልጻሉ፡፡
የተሽከርካሪዎች ቴክኒክ ጉድለት እና አሮጌ መሆናቸው ሌላው ለትራፊክ አደጋ መንስኤ መሆኑን የሚጠቁሙት ጌቱ (ዶ/ር)፤ በከተሞች ሊሽከረከሩ ይችላሉ ወይ የሚል ጥያቄ የሚያስነሱ ተሽከርካሪዎች አሉ፣ ወደ ገጠር ሲወጣ ይብሳል ነው የሚሉት፡፡
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ የአሽከርካሪ ብቃት ማነስም የአደጋ መንስኤ ነው፡፡ የአሽከርካሪ ማሠልጠኛዎች ተገቢውን መስፈርት ያላሟሉና የመንጃ ፍቃድ የሚሰጥበት ሥርዓት ችግር የሚስተዋልበት ነው፡፡
የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር አለበት የሚሉት ጌቱ (ዶ/ር)፤ በመንገድ ሁኔታ የትራፊክ ጠቋሚ ምልክቶች በተሟላ መልኩ አለመቀመጥ ችግሩን እንደሚያባብስም ነው የሚገልጹት፡፡
የመንገድ ደህንነት እና መንገድ ፈንድ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ጀማልም የመምህሩን ሃሳብ ይጋራሉ፤ ለሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች ቁልፍ ችግሮች ከሆኑት መካከል የአሽከርካሪዎች ጥንቃቄ ጉድለት እንዲሁም የተሽከርካሪ ቴክኒክ ጉድለት 82 በመቶ እንደሚሸፍኑ ይጠቁማሉ፡፡
ለተሽከርካሪ አደጋዎቹ ቁልፍ ችግር ተብሎ በጥናት ከተለየው መካከል የአሽከርካሪዎች ቸልተኝነትና ጥንቃቄ ጉድለት 68 በመቶ ድርሻ እንዳለው፣ የአሽከርካሪዎች የችሎታ ማነስ፣ ሃሰተኛ መንጃ ፍቃድ መጠቀም፣ ባግባቡ ሽልጠና አለመውሰድና መሰል ችግሮች ሕይወት እየቀጠፈ ለሚገኘው የትራፊክ አደጋ መንስኤ መሆናቸውንም ይናገራሉ፡፡
የተሽከርካሪ ቴክኒክ ጉድለት ለአደጋው ካላቸው ድርሻ 14 በመቶ የሚሸፍን ችግር መሆኑን በጥናት መለየቱንም ነው የሚጠቁሙት፡፡ በእግረኞች ክፍተት፤ ዜብራ ጠብቆ አለመሻገር፣ የመንገድ አለመመቸትና ሌሎች ችግሮችም ቀሪውን ድርሻ እንደሚይዙ ያመለክታሉ፡፡
ጌቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው የትራፊክ አደጋ የድሃ ሀገራት ችግር መሆኑን በመጠቆም፤ ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ ከመንገድ መሠረተ ልማት መሟላት፣ ከሚንቀሳቀሰው የተሽከርካሪ ብቃትና ከአሽከርካሪ የባህሪ ሁኔታ ጋር እንደሚገናኝ ይናገራሉ፡፡
በአደጉ ሀገራት የትፊክ አደጋ ቢከሰትም ከሚኖረው የተሽከርካሪ አደጋ አኳያም አነስተኛ ነው ባይ ናቸው፡፡
ከስምንት እስከ አስር ሚሊዮን የሚገመቱ ተሽከርካሪዎች በሚንቀሳቀስባት ስዊድን በዓመት የሞት አደጋ የሚመዘገበው 225 አካባቢ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡
አሽከርካሪዎች ለሕግ ተገዢና ብቃት ያላቸው መሆናቸው፣ የተሽከርካሪዎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ መሆን እና ምቹ የመንገድ መሠረተ ልማት መኖር ተዳምረው ለውጤቱ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ይገልጻሉ፡፡
አደጋውን ለመቀነስ ከታሰበ በከተሞች ፍጥነት እንዳይኖር ማገድና መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ በሰዓት ከ50 በታች ቢቻል 30 ማሽከርከር አደጋ ቢከሰት እንኳን መጠኑን መቀነስ ያስችላል ነው ጌቱ (ዶ/ር) የሚሉት፡፡
እግረኞችን ከትራፊክ አደጋ ለመታደግ የመንገድ ዲዛይንን የማሻሻል ሥራ በስፋት መከናወን እንዳለበት ይመክራሉ፡፡
ለመንገድ ትራፊክ አደጋ መንስኤ በሆኑት በተለይም ጠጥቶ ማሽከርከርና ከተፈቀደው ፍጥነት ልክ በላይ ማሽከርከርን ለመከላከል በማህበረሰቡ ዘንድ የባህሪ ለውጥ ለማምጣት መሥራት ያስፈልጋል ባይ ናቸው፡፡
አሽከርካሪዎች ፍጥነታቸውን ቀንሰው እንዲያሽከረክሩ የተጀመረውን የቁጥጥር ሥራ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ እግረኞች የእግረኛ መንገድን ብቻ እንዲጠቀሙ ተገቢና ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉም ያክላሉ፡፡ የመንገድ መሠረተ ልማትን ምቹ በማድረግ ተግባር ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያካተተ መሆን ይኖርበታል የሚሉት ጌቱ (ዶ/ር)፤ የኮሪደር ልማቱን አካል ጉዳተኞችን ባገናዘበ መልኩ መገንባት እንደሚገባና ተሞክሮው በሌሎችም አካባቢዎች ሁሉንም ሕብረተሰብ አካታች ባደረገ መልኩ እንዲተገበር ይመክራሉ፡፡
የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና በመንገድ የሚጠቀም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባም እንዲሁም ለተማሪዎች ግንዛቤ ፈጠራ በመሥራት የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ ትኩረት እንደሚደረግም አቶ ጀማል ጠቁመዋል፡፡
የቴክኒክ ምርመራና የአሽከርካሪዎች ማሠልጠኛ ተቋማት ሥራቸውን ሃላፊነት በተሞላበት መልኩ ሊተገብሩ እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡
በከተማው የተሠሩ እና በመሠራት ላይ ያሉ የኮሪደር ልማት ለከተማዋ መልካም ገፅታ ከማላበስ ባሻገር የትራፊክ አደጋን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ተስፋ እንዳላቸው የሚጠቁሙት ጌቱ (ዶ/ር)፤ በየቦታው ሳቢና ጽዱ የመንገደኞች ማረፊያ ቦታዎች መዘጋጀታቸውም ለትራፊክ አደጋ መቀነስ በጎ ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ ነው የሚናገሩት፡፡
‹‹ሁሉም መንገደኞች ለመጓዝ እኩል አቅም የላቸውም በድካም የዛሉ መንገደኞች ረፍት ይፈልጋሉ፤ የኮሪደር ልማቱ አካል ሆነው የተሠሩ ማረፊያዎች በትራፊክ ሁኔታ ላይ ወሳኝ ናቸው›› በማለት የተጀመረውን ተግባር በማስፋፋት የኮሪደር ልማቱን አካል ጉዳተኞችን ያማከለ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ጌቱ (ዶ/ር) አስተያየታቸውን ይቋጫሉ
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም