ከኢትዮጵያ ሕዝብ የመልማት ፍላጎት በተቃርኖ በመቆም ጥቅሞችን ማስከበር አይቻልም

ውስብስብ ፍላጎቶች በሞሉበት ባለንበት ዘመን ቀርቶ በቀደሙት ዘመናትም የትኛውም ሀገር እና ሕዝብ ብሄራዊ ጥቅሙን ለማስጠበቅ ይሠራል። ዘመኑ እንደተገዛበት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ይንቀሳቀሳል። ባለው ላይ ለመጨመር ሆነ ያለውን አስቀጥሎ ለመሄድ ዘመኑ ለደረሰበት አስተሳሰብ ተገዝቶ ይራመዳል ። ይህ የነበረ፣ ያለ እና የሚኖር ነው።

በዚህ ሂደት ውስጥ ዘመናት አልፈዋል። መንግሥታት ተነስተዋል ወድቀዋል ፤ ሀገራት ከአንድ የታሪክ ምእራፍ ወደሌላ የታሪክ ምእራፍ ተሸጋግረዋል ። ትናንት ሃያላን የነበሩ ሀገራት ፤ የሃያልነታቸው ዘመን ታሪክ ሆኖ በሌሎች ተተክተዋል ። ዓለምን ለውጠዋል የተባሉ አስተሳሰቦች ለሌላ ተራማጅ አስተሳሰብ ዘመንን ለቀው ሄደዋል።

በዚሁ ልክ የሀገራት ብሄራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ የሁሌ መሻት እንደየዘመኑ ተለዋዋጭ ዓለምአቀፋዊ እውነታ የሚለዋወጥ እና ለዚሁ የተገዛ ነው። ትናንት በሃይል ብሄራዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ የሚደረግ ጥረት አሁን ዓለም ከደረሰችበት የአስተሳሰብ ልእልና አኳያ ቢያንስ ቢያንስ ዘላቂ ጥቅም ማስጠበቂያ ሊሆን እንደማይችል ይታመናል ።

የሴራ ፖለቲካ መሠረቱ ማህበረሰብን ከራሱ እውነተኛ ፍላጎት ጋር በተቃርኖ እንዲቆም ማስቻል ነው። በዚህ ላይ የተመሠረተ የሀገራት የተጠቃሚነት መሻት፤ የሴራው ሰለባ ከሆነው ማህበረሰብ ንቃተ ህሊና ጋር የተያያዘ፤ በአንድም ይሁን በሌላ የማህበረሰብ ንቃተ ህሊና ባደገ ቁጥር ከአትራፊነቱ ይልቅ ኪሳራው የበዛ ነው።

የሃይልም ይሁን የሴራ ፖለቲካ አሁን ያለንበትን ዘመን የማይመጥን፤ ከተዛባ አስተሳሰብ የሚመነጭ፤ በየትኛውም መመዘኛ አስተማማኝ የሆነ ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚያጎናጽፍ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሀብት እና ጊዜን የሚያባክን፤ በሕዝቦች መካከል ያለና ሊኖር የሚገባን ግንኙነት ወደ አልተገባ መንገድ የሚወስድ ነው።

ኢትዮጵያ እንደ አንድ የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክ ባለቤት እንደሆነች ሀገር ፤ በነዚህ ዘመናት ካካበተችው የታሪክ ትርክት አኳያ፤ ከግብጽ ወንድም ሕዝብ ጋር በሚያስተሳስራት የዓባይ ወንዝ ውሃ ጋር በተያያዘ፤ የሀገራቱን ሕዝቦች /በተለይም የግብጽን ሕዝብ የሚጎዳ ተግባር አላደረገችም፤ ወደፊትም ታደርጋለች ተብሎ አይታመንም።

የዓባይ ወንዝ የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ፍጥረታዊ በሆነ የማይበጠስ ትስስር ያቆራኘ ነው፤ ከሁሉም በላይ እንደ አንድ ትልቅ ማህበረሰብ ለነጻነት፤ ለፍትሀዊነት እና ለጋራ ተጠቃሚነት ካላት ከፍ ያለ ማህበረሰባዊ አሴት አኳያ፤ ለጋራ የሕዝቦች ተጠቃሚነት ከመሥራት ባለፈ በራስ ወዳድነት የተቃኘ ከግብጽ ሕዝብ ጋር ያለንን ተፈጥሯዊ ትስስር የሚያላላ ተግባር አትፈፅምም፤ እስካሁንም የሆነው ይኸው ነው።

በየዘመኑ በነበሩ የግብጽ ነገሥታት ሆኑ ሀገሪቱን በቅኝ ግዛት የገዙ ሃይሎች ግን ፤ በወንዙ ውሃ ጉዳይ ጦር ከመስበቅ ጀምሮ፤ በወንዙ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ በሚደረሱ ስምምነቶች ኢትዮጵያን ባይተዋር አድርገዋል፤ የወንዙን ውሃ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ አጀንዳ በማድረግ፤ የሥልጣን ጊዜ መግዥያ ሲያደርጉም ማየት የተለመደ ነው።

ቀደም ባሉት ጊዜያት በቅኝ ገዥ እንግሊዝ በወንዙ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ተግባራዊ የተደረጉ ውሎች የውሃውን 90 ከመቶ በላይ አመንጪ የሆነችውን ኢትዮጵያን አለማካተቱ ፤ ሀገሪቱ በስምምነቱ ድምጽ እንዳይኖራት ከማድረግ ባለፈ፤ የወንዙ ውሃ ተጠቃሚ እንዳትሆን የተቀመጡ ክልከላዎች የዚህ ተጨባጭ እውነታ ማሳያ ናቸው።

ግብጽ ነጻነቷን ከተቀዳጀች ጀምሮ እስከ ዛሬ ባሉት ዓመታት ውስጥም ወደ ሥልጣን የመጡ የሀገሪቱ መሪዎች፤ የወንዙ ውሃ የሀገር ውስጥ ፖለቲካ አጀንዳ በማድረግ ፤ ሕዝቡ በወንዙ ውሃ አጠቃቀም ሆነ በወንዙ ዙሪያ ተገቢውን ግንዛቤ እንዳይጨብጥ አድርገውታል። የኢትዮጵያን በወንዙ ውሃ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ የመጠቀም ፍላጎት ባልተገባ መንገድ በመተርጎም የፖለቲካ አቅም ለማድረግ ረጅም ርቀት ተጉዘዋል።

እነዚህን የቅርብ ጊዜ እውነታዎች አነሳን እንጂ፤ ባልተገባ ስጋት እና ትርክት ፤ የግብጽ ነገሥታት በተለያዩ ወቅቶች የወንዙን ውሃ ከምንጩ ለመቆጣጠር ያካሄዷቸው ጦርነቶች እና ያጋጠሟቸው ሽንፈቶች በሀገራቱ ታሪክ ውስጥ የተለያየ ቀለም ይዘው የተቀመጡ፤ የትናንት ታሪክ ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው።

ይህ ካልተገባ ስጋት እና ይህንን ስጋት የፖለቲካ አጀንዳ የማድረጉ የግብፅ መሪዎች ያልተገራ የፖለቲካ መንገድ የሁለቱንም ሀገራት ሕዝቦች ብዙ ዋጋ እንዲከፍሉ አድርጓቸዋል። ከሁሉም በላይ በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከለል ያለውን ወንድማማችነት በየወቅቱ በመሸርሸር በመካከላቸው አለመተማመን እንዲሰፍን አድርገዋል።

የግብጽ መንግሥታት የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት እንደ ስጋት በማየት ፤ መችም ቢሆን ሊያቆሙት የማይችሉትን የኢትዮጵውያንን የመልማት ፍላጎት ለማቆም ለጋራ ልማት ቢውል ትርጉም ያለው ውጤት ሊያመጣ የሚችል ሀብት በከንቱ ሲያባክኑ ማየት የተለመደ ነው።

በርግጥ በሀገራቱ መካከል የሚፈጠሩ አለመተማመኖች የወንዙን ውሃ የሀገር ውስጥ ፖለቲካ አጀንዳ ማድረግ ተጠቃሚ መሆን ለሚፈልጉ የግብጽ መሪዎች እንደ መልካም እድል የሚታይ ቢሆንም ፤ አጠቃላይ በሆነው የሕዝቦቹ ዘላቂ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ እያሳደረ ያለው አሉታዊ ተጽእኖ ከፍ ያለ ስለመሆን መገመት አይከብድም።

በተለይም ፍትሃዊ የጋራ ተጠቃሚነት ዓለም አቀፍ መርህ ሆኖ ዘመኑን በሚዋጅበት በዚህ ዘመን፤ የግብጽ መንግሥት ዘላቂነት ላለው፤ በመተማመን ላይ ለተመሠረተ የሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ከመስራት ይልቅ ፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የመልማት መሻት በተቃርኖ በመቆም በተለመደው የሴራ መንገድ ብሄራዊ ጥቅሞቹን ለማስከበር የሚሄድበት መንገድ ዘመን ያለፈበት እና አክሳሪ ነው!

አዲስ ዘመን ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You