በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ ማኅበረሰብ የቅድሚያ ቅድሚያ ፍላጎቶቹ በመሠረታዊነት የሚጠቀሱት ምግብ፣ ልብስ እና መጠለያ ናቸው። ባለንበት ዘመን ስለነዚህ ፍላጎቶች ማውራትም ሆነ ፍላጎቶቹን ማሟላት አለመቻል አንገት የሚያስደፋ፣ የድህነት እና የኋላቀርነት ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
በተለይም በአንድ ወቅት የትልቅ ሥልጣን ባለቤት የሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት፣ ለሕዝቦቻቸው እነዚህን መሠረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት አቅቷቸው፣ ተመፅዋች ሆነው የመገኘታቸው እውነታ፣ አንገት ከማስደፋት ባለፈ፤ በትውልዶች ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ ሊፈጥር የሚችለው አሉታዊ የሥነ ልቦና ተፅዕኖ ከፍ ያለ ነው።
ለእነዚህ ሀገራት አሁናዊ የተመፅዋችነት ትርክት፤ ዋነኛ ምክንያት የሚሆነው፤ የቀደመውን የሥልጣን መንገድ ማስቀጠል የሚያስችል ሠላም እና ማኅበረሰባዊ መረጋጋት አለመኖር ነው። ያለ ሠላም ሥልጣኔን ማምጣት ሆነ፤ ለሥልጣኔ በሁለንተናዊ መልኩ እራሱን የሰጠ ማኅበረሰብ መፍጠር አይቻልም።
ሠላም ለሰው ልጅ መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶችን ከማሟላት ጀምሮ ወደ ዘመነኛ የአኗኗር ሥርዓት ለመሻገር ወሳኝ ጉዳይ ነው። ለዚህ ደግሞ በሠላም እጦት ከፍ ካለ ሥልጣን ደረጃ ወርደን ለመሠረታዊ ፍላጎቶቻችን እጃችንን ለምፅዋት ለማንሳት ለተገደድነው ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የሚነገረን አዲስ እውነት አይደለም። በየዘመኑ ትውልዶችን ዋጋ እያስከፈለ እንደ ጥላ የሚከተለን ችግራችን ነው ።
ትናንት ያለፍንበት ፖለቲካ ኢኮኖሚ ከፈጠረው አስገዳጅ እውነታ አኳያ፤ ኃይልን መሠረት ባደረገ፤ በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት በተቃኘ የፖለቲካ አስተሳሰብ፤ እንደ ሀገር የቆምንበትን መሠረት እስኪናጋ ድረስ በብዙ የርስ በርስ ግጭቶች አልፈናል ። በዚህም እያንዳንዱ ትውልድ ብዙ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል ተገድዷል። ተስፋ ያደረገውን ሕይወት መኖር ሳይችልም ቀርቷል።
እያንዳንዱ የግጭት ታሪክ ከታሪክነት ባለፈ፤ ለቀጣይ ግጭት እርሾ እየሆነም፤ እንደሀገር በግጭት አዙሪት ውስጥ ዘመናትን ለማለፍ ተገድደናል። ይህም የሕዝባችንን ሠላም እና መረጋጋት፤ ከዚያም ባለፈ የመልማት ፍላጎት ሲፈታተነው ቆይቷል። በየዘመኑ የተጀመሩ የመልማት መነቃቃቶች ትርጉም ያለው ውጤት እንዳያመጡም አድርጓል።
ከትናንት የተደጋገሙ ስህተቶቻችን ቆመን ለመማር ፈቃደኝነት ማጣታችን፤ ከሁሉም በላይ ታሪኮቻችንን የመማሪያ ዕድሎች አድርገን አለመውሰዳችን፤ እያንዳንዱ ትውልድ በየዘመኑ ተመሳሳይ ስህተቶችን እንዲሠራና ለስህተቶቹ ራሱን ከደሙ ንጹሕ አድርጎ እንዲያስብ አድርጎታል።
ችግሩ ከዚህም ባለፈ በየወቅቱ ለተፈጠሩ ሀሳብ አልባ ፖለቲከኞች፤ የጥፋት አስተሳሰብ የትርክት ግብዓት በመሆን፤ በሀገሪቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን ተቻችሎ እና ተከባብሮ አብሮ የመኖር ባሕል ፈተና ውስጥ ጨምሮታል። ለጽንፈኛ አስተሳሰቦች መወለድም አቅም ሆኗል።
እንደ ሀገር የማኅበረሰባችንን ባሕላዊ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ የጋራ እሴቶችን በመሸርሸር፤ አሁን ላይ ለሚታዩ ግጭቶች ትልቅ ግብዓት ሆኗል፤ አጠቃላይ የሆነውን ሀገራዊ ሠላም እና መረጋጋትም ችግር ውስጥ ከቶታል። እንደ አንድ ማኅበረሰብ የጀመርነውን የለውጥ መነቃቃት እየተፈታተነውም ይገኛል።
እንደ ሀገር አብሮን እየተጓዘ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ካለው ከታሪክ አለመማር፤ ለታሪካዊ ስህተቶች እንደ ትውልድ ኃላፊነት ወስዶ ዘላቂ መፍትሔ ያለማፈላለግ ችግር መውጣት አለብን። ችግሩን በተጨባጭ ተረድተን፤ አውቀንና ገብቶን በኃላፊነት መንፈስ መፍትሔ ለማፈላለግ መንቀሳቀስ ይኖርብናል፤ ለዚህ የሚሆን የአስተሳሰብ ተሐድሶ መፍጠርም ይጠበቅብናል።
ከትናንት ታሪኮቻችን ለመማር ይህ ትውልድ ከየትኛውም ትውልድ በላይ የተሻለ ዕድል አለው። አንድም የትርክት መዛባት ካስከፈለው ያልተገባ ዋጋ፤ ከዚያም ባለፈ ለራሱም ሆነ ለመጪዎቹ ትውልዶች ብሩህ ነገዎች ካለው በጎ ሕሊና እና ከፍ ያለ መሻት አኳያ ይህን ላለማድረግ ምክንያት አይኖረውም።
ከትናንት የታላቅነት ማንነቱ እና አሁን ካለበት አንገት አስደፊ ሕይወት የሚመነጨውን የማደግ/ የመበልፀግ ቁጭታችን ተጨባጭ ሆኖ ለራሳችን ሆነ ለመጪዎች ትውልዶች የተሻለች ሀገር ለመፍጠር የጀመርነው የለውጥ መንገድ ውጤታማ እንዲሆን፤ ከሁሉም በላይ ከአዎንታዊውም ሆነ አሉታዊ ታሪኮቻችን በቅን መንፈስ በጎ በጎውን ለመማር በሁለንተናዊ መልኩ ዝግጁ መሆን ይጠበቅብናል። ከተዛነፈ የታሪክ ትርክት ወጥተን፤ ራሳችንን እና መጪውን ትውልድ ከግጭት አዙሪት መታደግ ይኖርብናል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም