
ሀዋሳ:- በሀዋሳ ከተማ የትኛውንም ክስተት በደኅንነት ካሜራዎች በሚገባ የመያዝና የመከታተል አቅም እንደተፈጠረ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ መኩሪያ ማርሻዬ ገለፁ።
የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ መኩሪያ ማርሻዬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ እንደገለፁት፤ ሀዋሳ አሁን ላይ በደኅንነት ካሜራዎች የምትጠበቅ ከተማ ናት። ይህንንም ይበልጥ ለማጠናከር በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
ከዚህ ውስጥ አንዱ ከ450 በላይ የንግድ ተቋማት የደኅንነት ካሜራዎችን እንዲገጥሙ ተደርጓል ያሉት ከንቲባ መኩሪያ፤ ይህንንም ከዋናው የመረጃ ማስቀመጫ ቋት ጋር የማስተሳሰር ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል። በእነዚህ ሥራዎች በሀዋሳ ከተማ የትኛውንም ክስተት በደኅንነት ካሜራዎች በሚገባ የመያዝና የመከታተል አቅም መፈጠሩን ገልፀዋል።
በከተማዋ ድንገተኛ ችግር ከተከሰተ በቅርበት የሚደርሱ ከ40 በላይ የፖሊስ የማቆያ ቦታዎች መኖራቸውን የተናገሩት ከንቲባ መኩሪያ፤ በፖሊስ ማቆያ ቦታዎች የደኅንነት ካሜራ የተገጠመ ሲሆን ከአንዱ የፖሊስ ማቆያ ወደ ሌላኛው መረጃዎች በፍጥነት እንደሚተላለፉም ነው የገለፁት።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሠላማዊት ካሣ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ የከተሞች ፎረምን ከነሐሴ 29 ጀምሮ ታስተናግዳለች። በመድረኩ ከተሞች ልምዶቻቸውን የሚያካፍሉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ የሀዋሳ ከተማ እንደምትገኝ ተናግረዋል።
ከተሞቻችን በዚህ ብዙ ልምዶችን ከማካፈል ባለፈ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ሊወስዱ ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታ ሠላማዊት፤ የሀዋሳ ከተማ የኮሪደር ልማት በጅማሮ ደረጃ ላይ ቢሆንም እስከ አሁን ባለው የሥራ ሂደት ውስጥ ከተማዋን የሚገልፁ ትልልቅ ነገሮች በፎረሙ ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
ከተሞች የከተማ ነዋሪዎች ፍላጎት እና የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች መመለስ እንዲችሉ ራሳቸውን በየጊዜው ማሻሻል ይኖርባቸዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ አዲስ አበባ ላይ የተጀመረው የኮሪደር ልማት በርካታ ውጤቶችን ያስመዘገበ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የሥራ ዕድሎችን የፈጠረ እንዲሁም የከተማዋን ገፅታ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቀየር ያስቻለ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑንም ገልፀዋል።
ይህንን ፕሮጀክት በሁሉም ክልሎች በተለይ ብዙ ነዋሪዎች ያሉባቸውና አቅም ያላቸው ከተሞች ላይ እንዲሠራ በስፋት እቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል፡፡
በዚህ መነሻነት የኮሪደር ልማት በሀዋሳ ከተማ የተጀመረ ሲሆን በርካታ እቅዶችም በሂደት ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል። በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስተባባሪነት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በሀዋሳ ከተማ የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
በመስክ ምልከታው የሀዋሳ ከተማ የኮርደሪ ልማት በሁለት መልኩ ተግባራዊ የሚደረግ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን የመጀመሪያው የማስፋፊያ አካባቢ ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ሆኖ ሥራውም 10 መንገዶችን 35 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ይሆናል።
ሁለተኛው በመሐል ከተማ ነባር መንገዶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራ በሦስት መንገዶች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ሆኖ ከአምስት ነጥብ ሰባት በላይ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው።
ይህም በጥናት የተለዩ ከሳውዝ ስኘሪንግ እስከ ኃይሌ ሪዞርት ያለው የሚያካልል ሲሆን በዚህም የሻፌታ አደባባይ ድረስ ያለው በ50 እና 40 ሜትር ስፋት ያለው ሦስት ነጥብ ሰባት ኪሎ ሜትሮች ያህል መንገድ ግንባታ የሚከናወንበት ነው።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24/ 2016 ዓ.ም