አካል ጉዳተኞችና የአረንጓዴ ዐሻራ ተሳትፎ

በኢትዮጵያ 17 ሚሊዮን የሚጠጉ የተለየያ የአካል ጉዳት ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉ ይታመናል። ይህም ሁለት አነስተኛ የቆዳ ስፋት ካላቸው ሀገራት የህዝብ ቁጥር ጋር ይስተካከላል። በኢትዮጵያ ካለው ከፍተኛ የሆነ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር አንፃር ግን አካል ጉዳተኞች ልክ ሌሎቹ ዜጎች አመቺ የሆኑ መሰረተ ልማት፣ የትምህርት፣ ስራና ሌሎችም ማህበራዊ አገልግሎቶችን በበቂ ሁኔታ ተጠቃሚ ሲሆኑ አይታይም። ያም ሆኖ አካል ጉዳተኞች በማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ያላቸውን ተሳትፎ እየጨመሩ መጡ እንጂ አልቀነሱም።

አሁን አሁን ደግሞ ለአካል ጉዳተኞች ከሙአለ ሕፃናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ድረስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ በመሆኑ ሁለንተናዊ ውጤት እየተመዘገበ መጥቷል። በተለይ ለአይነ ስውራንና ሌላም አይነት የአካል ጉዳት ላለባቸው ብቻ ታስበው የተገነቡ የቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጥራት ያላቸውና ከመደበኛው ተማሪ የሚበልጡ እንጂ የማያንሱ ተማሪዎችን በማፍራት ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ ይገኛል።

በተመሳሳይ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች አመቺ ሆነው በመሰራታቸውና እነርሱን አካተው እያስተማሩ በመሆኑ በተማሪዎቹ ውጤት መሻሻል ላይ ትልቅ ለውጥ መጥቷል። ይህም ለውጥ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ታይቷል። ይህንንም የከተማ አስተዳደሩ የ2016 ዓ.ም እቅድ አፈፃፀሙን ባቀረበበት ወቅት አስታውቋል።

በሌላ በኩል በቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው አነሳሽነትና በሌሎች የረድዔት ድርጅቶች የተገነቡ የአይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤቶችም የአካል ጉዳተኞችን የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ያረጋገጡና ለነገዋ ኢትዮጵያ ከሌላው ዜጋ እኩል በሁለንተናዊ መልኩ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ናቸው። እንዲያም ሆኖ ግን በኢትዮጵያ ካለው የአካል ጉዳተኞች ቁጥር አንፃር ይህ ጅምር እንጂ ፍፃሜ አይደለም። አካል ጉዳተኞችን በሁለንተነዊ መልኩ ተጠቃሚ ለማድረግ አሁንም በርካታ ስራዎችን በመንግሥትና በሁሉም ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት መስራት ይጠይቃል።

ከዚህ ባለፈ የአካል ጉዳተኞች የማህበራዊና ሀገራዊ ጥሪ ተሳትፏቸውም ቀላል የሚባል አይደለም። ከዚህ በፊት አካል ጉዳተኞች በተለያዩ ሀገራዊ ጥሪዎች ላይ ያላቸውን ንቁ ተሳትፎ በሚገባ አሳይተዋል። በዓባይ ግድብ ግንባታ የገንዘብ፣ እውቀት፣ ጉልበትና ሌላም አስተዋፅኦ አድርገዋል። እርዳታ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችም የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አድርገዋል። በሌሎችም ህዝብን አንድ በሚያደርጉ ሀገራዊ ጥሪ ተሳትፈዋል።

አካል ጉዳተኞች በዘንድሮ የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሀ ግብርም በነቂስ ወጥተው አረንጓዴ ዐሻራቸውን አሳርፈዋል። አካል ጉዳተኞች በዘንድሮ የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ለመሳተፍ ዝግጅታቸውን ቀድመው ነበር የጀመሩት። በዚህ ዓመት በመላው ሀገሪቱ ለስድስተኛ ጊዜ እየተከናወነ ባለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። በዚሁ መሰረትም አካል ጉዳተኞች በዚህ የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በንቃት ተሳትፈዋል።

በዘንድሮው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር 600 ሚሊዮን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመገኘት መርሀ ግብሩን አስጀምረዋል፤ አረንጓዴ ዐሻራቸውንም አኑረዋል። በመርሀ ግብሩ ከልጅ እስከ አዋቂ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በንቃት እንዲሳተፉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ባቀረቡት አካል ጉዳተኞችም ጥሪውን ተቀብለው በመርሀ ግብሩ ተሳትፈዋል።

በዕለቱ አዋቂዎች በነፍስወከፍ ከ20 በላይ፣ ታዳጊዎች ከ10 በላይ ችግኝ በመትከል ለነገ ሀገር ተረካቢዎች የምትመች ሀገር ለማስረከብ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ኃላፊነታችንን እንወጣ ባሉት መሠረት የተለያዩ የአካል ጉዳት ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 በተዘጋጀው ቦታ በመገኘት አረንጓዴ ዐሻራቸውን አሳርፈዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ እንደሚሉት፣ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ፌዴሬሽኑ በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል። ፌዴሬሽኑ አባላቱን በማስተባበር በዘንድሮው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በንቃት ተሳትፏል። ለዚህ ተሳትፎም ፌዴሬሽኑ ከአባላቱ ጋር በመሆን ከወራት በፊት ቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 በተዘጋጀው ቦታ የችግኝ ተከላው የተከናወነ ሲሆን፤ በመርሀ ግብሩ 17 ሺህ አካል ጉዳተኞች ተሳትፈዋል። ችግኝ ከመትከል በተጨማሪ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የእንክብካቤ ስራ ለመስራት እቅድ ተይዟል። በቀጣይም አካል ጉዳተኞች ከአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር በተጨማሪ በቀጣዩ አመትም በዚሁ መርሀ ግርብር በመሳተፍ አረንጓዴ ዐሻራቸውን በማሳረፍ ሀገራዊ ተሳትፏቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 23/2016 ዓ.ም

Recommended For You