አምራቹን በማበረታታ ወጪ ንግድን የሚያጠናክር የንግድ ሳምንት

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የአገሪቱን የንግድ ስርዓት ጤናማ በሆነ መንገድ ለመምራት የተለያዩ ተልዕኮዎችን አንግቦ የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአገር ውስጥ ንግድን ማዘመን፣ የንግድ ስርዓቱን ቀልጣፋና ፍትሐዊ ማድረግ፣ የንግድ ፈቃድ የቁጥጥር ሥራ መስራት፣ ቀልጣፋና ምቹ በሆነ መንገድ የምርት ዝውውር እንዲፈጠር እንዲሁም የንግድ ሰንሰለቱ አጭር ቀልጣፋና የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን ያከናውናል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እነዚህንና መሰል ተግባራትን በመከወን ሕገወጥ ንግድን የመቆጣጠርና የመከላከል እርምጃ እየወሰደ ነው። በተለይም በቅርቡ ተግባራዊ የሆነውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተገን በማድረግ በንግዱ ማኅበረሰብ የተፈጠረውን ውዥንብር በመከታተል ቁጥጥር ሲያደርግ ቆይቷል። በመሆኑም በተለያዩ የምግብ ሸቀጦች ላይ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉና ምርት በደበቁ ነጋዴዎች ላይ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ እንደቻለ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በአሁን ወቅትም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የንግድ ስርዓቱን ለማዘመንና ጤናማ የንግድ ስርዓት እንዲፈጠር ሥራዎች እየሰራ ይገኛል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚሰራቸውን ሥራዎችም ዜጎች እንዲያውቁትና መረዳት እንዲችሉ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው። በተለይም ግልጸኝነትን ከመፍጠር አኳያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚሰራቸውን ሥራዎች ለማኅበረሰቡ ለማቅረብና ለማስተዋወቅ በሚል በተቋሙ ቅጥር ግቢ ውስጥ የንግድ ሳምንት አዘጋጅቷል።

‹‹የኢትዮጵያን ይግዙ›› በሚል መሪ ቃል በመስሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የንግድ ሳምንት እና በተቋሙ ውስጥ የተገነባው የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ማሳያ ማዕከል ነሐሴ 19 ቀን 2016 ዓ.ም የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በይፋ ተከፍቷል። በንግድ ሳምንቱ የተለያዩ ሁነቶች የተከናወኑ ሲሆን፤ በቀጣይም የሚከናወን ይሆናል።

በንግድ ሳምንቱ በዋናነት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የሚሰራቸውን ሥራዎች የሚያስተዋውቅበት መድረክ ተፈጥሯል። በተቋሙ የተከፈተው የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ማሳያ ማዕከል ለማኅበረሰቡ ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል። ከዚህ ባለፈም የንግዱ ማኅበረሰብ እርስ በእርስ የመተዋወቅና የመወያየት ዕድል የሚያገኝበት እንዲሁም ከመንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክርበት መድረክ እንደሚሆን ተመላክቷል።

ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው ይህ አገር አቀፍ የንግድ ሳምንት በየዓመቱ ቀጣይነት ባለው መንገድ የሚካሄድ ይሆናል። ያሉት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶክተር) ናቸው። እሳቸው እንዳሉት፤ ‹‹የኢትዮጵያን ይግዙ›› በሚል መሪ ሃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው አገር አቀፍ የንግድ ሳምንት ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች ያሉት ሲሆን፤ አንደኛው የአገር ውስጥ አምራቾችን በማበረታታ ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት ነው። ሁለተኛው የውጭው ዓለም አገር በቀል የሆነና ጥራቱን የጠበቀ ምርት ኢትዮጵያ አምርታ ለዓለም አቀፍ ገበያ እያቀረበች በመሆኑ የኢትዮጵያን ምርት እንዲገዙ ለማበረታታት ያለመ ነው።

በአገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የንግድ ሳምንት የተለያዩ መርሃ ግብሮችን አሰናድቶ እያቀረበ ይገኛል። በዋናነትም ኢትዮጵያ በኤክስፖርት ምርት አስተዋፆ ቢኖራትም የወጪ ንግድ ምርቶቿን የምታስተዋውቅበት የኤግዚቢሽን ማዕከል አልነበራትም። የአገር ውስጥ ንግዱ በተለያየ ጊዜ በሚዘጋጁ ባዛርና ኤግዚቢሽኖች የማስተዋወቅ ሙከራዎች ቢኖሩም ቋሚ የሆነ የወጪ ንግድ ኤግዚቢሽን ማዕከል አልነበረም። በመሆኑም ከውጭ የሚመጣ ገዢ አገር ሁሉንም ምርቶች በአንድ ማዕከል የሚያገኝበት ዕድል ይፈጠራል። ለዚህም ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ባለፈው አንድ ዓመት ይህንኑ ሲሰራ ቆይቷል። ያሉት ሚኒስትሩ ከመንግሥት ካዝና አንድ ብር ሳይወጣ በግልና በመንግሥት አጋርነት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አንደኛ ፎቅ ላይ 730 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ቋሚ ኤግዚቢሽን ማዕከል ተገንብቷል።

ቋሚ ኤግዚቢሽኑ የሁሉም ወጪ ንግድ ምርቶች የሚወከልበት ሲሆን፤ በኤግዚቢሽኑ ውስጥም የኢትዮጵያ ምርቶች በፎቶና በተንቀሳቃሽ ምስል ተካትቶ ቀርቧል። በኤግዚብሽን ማዕከሉ ከ14 በላይ ስክሪኖች በአንድ ጊዜ ይታያሉ። ከቡና ጀምሮ ጫት፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች፣ ቅመማ ቅመም፣ ምግብና መጠጥ፣ አልባሳት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ስጋና የስጋ ውጤቶች፣ የቁም እንስሳት፣ የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች፣ በማዕድን ወርቅና ታንታለምን ጨምሮ ናሙናዎችን በማቅረብ የኢትዮጵያን አቅም ማሳየት ያስችላል።

ለከተማው ማኅበረሰብና ለተለያዩ ተቋማት ክፍት በሆነው ኤግዚቢሽን የንግድ ሳምንቱን መነሻ በማድረግ በአገሪቱ የሚገኙ ከ10ሺህ 66 በላይ የሆኑ የእሁድ ገበያዎችም ተሳታፊ እንደሆኑ ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የእሁድ ገበያዎቹ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ምርቶቻቸውን ለማኅበረሰቡ ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጸዋል። በንግድ ሳምንቱ ማኅበረሰቡ ኤግዚቢሽኑን እየጎበኘ እግረ መንገዱን የተለያዩ ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት እንደሚችልና በተለይም መሰረታዊና ዕለት ተዕለት የሚጠቀማቸው የምግብ ሸቀጦች ለማኅበረሰቡ ቀርቦ ማኅበረሰቡም የሚሸምት ይሆናል።

በንግድ ሳምንቱ የፓናል ውይይት የተከናወነ ሲሆን፤ በተለይም በአገር ውስጥ ንግድ የታዩ ለውጦች፣ የሚስተዋሉ ችግሮችና በቀጣይ ትኩረት ሊደረግባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል። ውይይቱም ከአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን የሁሉም ድምጽ የተሰማበት ነው። በዚህም መንግሥትን ጨምሮ ነጋዴው፣ ሸማቹ፣ አምራቹ፣ አቅራቢውና ምሁራን ጭምር ተሳታፊ ሆነዋል። በተመሳሳይ ወጪ ንግዱን በተመለከተ በተገኙ ውጤቶችና ችግሮች ዙሪያ መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የፓናል ውይይት አድርጓል።

ከዚህ በተጨማሪም በጥራት መሰረተ ልማት ዘርፍ የፓናል ውይይት በማድረግ በዚህም የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ስነ-ልክ ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ተሳታፊ ይሆናሉ። እነዚህ ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት አስመልክቶ የፓናል ውይይት በተያዘው ሳምንት የሚደረግ እንደሆነም ተመላክቷል።

በንግድ ሳምንቱ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የንግድ ሳምንቱ ማጠቃለያ አንዱ እንደሆነ ያነሱት ሚኒስትሩ፤ በማጠቃለያው ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች የሚስተናገዱ እንደሆነ ነው ያስረዱት። እሳቸው እንዳሉት፤ የመጀመሪያው ጉዳይ በንግድና ዘርፍ ማኅበራት ነባር አዋጅ እና አሁን ዲዛይን በተደረገው አዋጅ ላይ የግሉ ዘርፍና መንግሥት የሚመካከሩ ይሆናል። ይህ አይነቱ አካሄድ እስካሁን በነበረው ሂደት በተደራጀና ተቋማዊ በሆነ መንገድ የአሰራር ስርዓት ኖሮት ሲመራ አልነበረም። ስለሆነም አሁን ላይ በመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ሁሉም ሚኒስትሮች በተገኙበት ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ በመሆን በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ሰፊ ውይይት ይካሄዳል።

በውይይቱም የግሉ ዘርፍ አሉኝ የሚላቸውን ጥያቄዎች ለመንግሥት አቅርቦ ከመንግሥት ጋር ምክክር ያደርጋል። በመሆኑም ለተፈጻሚነቱ በጋራ የሚረባረብበትና የአስተሳሰብ እንዲሁም የተግባር አንድነት የሚረጋገጥበት መድረክ ይሆናል። መድረኩ እንደ ንግድ ሳምንቱ ሁሉ ከዚህ በኋላ ቀጣይነት የሚኖረው ሲሆን፤ የአሰራር ስርዓት ተዘርግቶለት በዓመት አንድ አልያም ሁለት ጊዜ የሚካሄድ ይሆናል። ይህም በግሉ ዘርፍና በመንግሥት መካከል የሚፈጠሩ የሀሳብ ልዩነቶችን በማጥበብ የጋራ አገርን በጋራ ለማሳደግ ትልቅ ዕድል የሚፈጥርና ሁሉም የጋራና የተናጥል ኃላፊነቱን የሚወጣበት መድረክ ይሆናል።

ሁለተኛው መርሃ ግብር ዕውቅናና ሽልማት የሚሰጥበት እንደሆነ ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር መቅጣት ብቻ ሳይሆን ሽልማትም የሚሰጥ እንደሆነ ገልጸው፤ በንግድ ሳምንቱ ማጠቃለያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት 124 የሚደርሱ የተለያዩ ሽልማቶችን የሚሰጥ እንደሆነ ተናግረዋል። የሽልማት አይነቶቹም የተለያዩ ሲሆን፤ ላኪዎች በተለያዩ ዘርፎች ባስገኙት የውጭ ምንዛሪ መጠን መሰረት የሚሸለሙ ይሆናል። ከላኪዎች መካከልም ባስገኙት የውጭ ምንዛሪ መጠን ከሁሉም ዘርፎች የአሸናፊዎች አሸናፊ ተመርጦ የሚሸለም ይሆናል።

ከላኪዎች በተጨማሪ አስመጪዎችም በተመሳሳይ የሚሸለሙ ሲሆን፤ በተለይም በአገር ውስጥ የምርት እጥረት እንዳያጋጥም ምርቶችን በስፋት በማቅረብ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት እንዲሁም የትርፍ እዳጋቸውን ተመጣጣኝ በማድረግ የኅብረተሰቡን ኑሮ መታደግ የቻሉ አስመጪዎች የሚሸለሙ ይሆናል። ሽልማቱ በተቀመጠለት ግልጽ የመወዳደሪያ መስፈርት መሰረት ከአንድ እስከ ሶስት የወጡ አስመጪዎችን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚሸልም ይሆናል።

ሶስተኛው ሽልማት የሰንበት ገበያዎችን የሚመለከት ሲሆን፤ በአገሪቱ የሚገኙ 10ሺህ 66 የእሁድ ገበያዎች በክልል ደረጃ ተወዳድረው አንደኛ የሚወጡት በአገር አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ይሰጣቸዋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ አራተኛው የሽልማት አይነት ሱፐርማርኬቶች እንደሆነ ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ሱፐርማርኬቶች በተለይም መካከለኛ ገቢ ላለው የማኅበረሰብ ክፍል ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ አይተኬ ሚና አላቸው። ይሁንና እስከዛሬ ድረስ እነዚህ ተቋማት የተረሱና ክትትል የማይደረግባቸው ነበሩ። በመሆኑም እንደ ሰንበት ገበያዎች ሁሉ በሁሉም ክልል የሚገኙ ሱፐርማርኬቶች ተወዳድረው በአገር አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የሚሰጣቸው ይሆናል ብለዋል።

ከጥራት አንጻርም እንዲሁ በጥራት የተሻሉ የሆኑ አምራች ድርጅቶች ተወዳድረው በተመሳሳይ መልኩ ሽልማት የሚሰጣቸው ይሆናል። ሌላው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የውጭውን ብቻ መሸለም ሳይሆን የውስጡንም መሸለምና ማጠናከር ያለበት በመሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ከየዘርፉ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ምርጥ ፈጻሚዎች የሚሸልም ይሆናል። ሽልማትና ዕውቅናው ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት በቂ ሥራ በመሰራቱ ብቻ አይደለም። ያሉት ሚኒስትሩ፤ በቂ ሥራ ለመስራት ሰው ላይ መስራት፣ ለሰዎች ዕውቅና መስጠትና ለተገኘው ውጤት በጋራ ማክበር ከተቻለ በቀጣይ ለአገሩ አገልግሎት የሚሰጥና በስነ ምግባሩ የታነጸ ትውልድ መፍጠርና ለቀጣይ ጊዜ አደራ መስጠት ይቻላል ብለዋል።

በንግድ ሳምንቱ የተዘጋጀው ኤግዚቢሽን መንግሥት ያዘጋጀውና ለአገልግሎት ክፍት ያድረገው ቢሆንም ተጠቃሚው መላው የኅብረተሰብ ክፍል ነው። ያሉት ሚኒስትሩ፤ በማንኛውም ጊዜ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ኤግዚቢሽኑ ክፍት በመሆኑ እየገባ የራሱን ኤግዚቢሽን መጎብኘት ቢፈልግ ሊከለከል አይገባም ብለዋል። ማንኛውም ሰው ገብቶ ጎብኝቶ አስተያየት ሰጥቶ መሄድ ይችላል። በሌላ በኩል ላኪዎች ከውጭ ከሚመጡ አስመጪዎች ጋር ወደ ኤግዚብሽኑ በመምጣት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስጎብኚዎች አማካኝነት ከአስመጪዎች ጋር የሚወያዩበትና ዋጋ ተነጋግረውና ተስማምተው መፈራረም የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ስለመኖሩም አመላክተዋል።

ይህን አግልግሎት ለማሳለጥ ስድስት የሚደርሱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለሙያዎች በተለያዩ ቋንቋዎች አገልግሎት የሚሰጡ እንደሆነም ተገልጿል። ባለሙያዎቹ ስልጠና ወስደው ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል። ያም ቢሆን ታድያ ሁሉም ነገር አስጎብኚ የሚፈልግ አይደለም። ለዚህም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በኤሌክትሮኒክ ማስታወቂያ የሚለቀቅ አሰራር አለ። በመሆኑም በኤሌክትሮኒክ በተያያዘ ማስታወቂያ አንድ ሰው በራሱ ጊዜ እየጎበኘ የሚወጣበት ዕድል ስለመኖሩም ተመላክተዋል።

በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነባው የውጪ ምርቶች ማሳያ ቋሚ የኢግዚቢሽን ማዕከል በአገሪቱ ያለውን የንግድ ስርዓት ለማዘመንና ለማጠናከር ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ በዘርፉ የአሰራር ማነቆ የሆኑ የፖሊሲ፣ የሕግ ማዕቀፎችን በጥናት በመለየት ማሻሻያ በማድረግ ለንግዱ ዘርፍ መዘመንና መጠናከር ተግባራዊ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ተናግረዋል። በሀገር ውስጥ ንግድ ዘርፉ መሠረታዊ ለውጥ እያመጡ ካሉ ሥራዎች የነዳጅ ዲጂታል ግብይት እና የኦንላይን የንግድ ፈቃድና ምዝገባ ዋነኛ መሆናቸውንም አመላክተዋል። የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኙ አንድ ሺህ 66 የሚሆኑ የቅዳሜና እሁድ ገበያ ማዕከላት አደረጃጀትና ግብይትን የማዘመን ሥራ መሰራቱንም ገልጸዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You