የኢትዮጵያ ብልጽግና የሚረጋገጠው ኢንዱስትሪዎች ሲያመርቱ ዜጎችም ሲሸምቱ ነው!

ሀገራት የኢኮኖሚ እድገታቸውን ማረጋገጥ የሚችሉት ኢንዱስትሪዎች በቂ ምርት ማምረት ሲችሉና ዜጎችም የራሳቸውን ምርት መጠቀም ሲችሉ ነው። በቂ ምርት ማምረት የማይችሉ፤ የራሳቸውን ምርት የማይጠቀሙና በራሳቸው ምርት የማይኮሩ ሀገራት በኢኮኖሚ እድገታቸው ወደኋላ ከመቅረታቸውም በላይ በውጭ ሀገራት ተፅዕኖ ስር መውደቃቸው አይቀሬ ነው።

በራስ ምርት መኩራት የሀገር ውስጥ አምራቾችን ከማበረታታት ባሻገር ለሀገርም ትልቅ ክብርና ኩራት የሚያጎናጽፍ ነው። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያም ኢንዱስትሪዎቿ በቂ ምርት እንዲያመርቱና ዜጓቿም እንዲሸምቱ ለማስቻል በርካታ የማነቃቂያ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ትገኛለች።

የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና እድሎች እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህንም እድሎች ለመጠቀምም መንግሥት ከግብርናው ዘርፍ ባልተናነሰ መልኩ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቷል።

መንግሥት በቀየሰው የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርታማ እንዲሆኑና ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ትኩረት አድርጓል። በዚህም ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት 40 በመቶ የሚሆነውን ፍላጎቷን በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን ችላለች።

ይህም ሆኖ ከሀገራዊ ፍላጎት አንጻር ይህ ቁጥር ወደ 80 በመቶ ማደግ የሚገባው በመሆኑ መንግሥት ይህንን ትልም ለማሳካት የሚያስችለውን ስትራቴጂ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በተለይም የኢንዱስትሪ ዘርፉ ምርትና ምርታማነትን ሊጨምሩ የሚችሉ ግብዓቶችን በማቅረብና የኃይል እርቅቦትን ተደራሽ በማድረግ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ለጥቅል ሀገራዊ ምርት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ላይ ይገኛል።

በዚህም የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም እያደገ መጥቷል። በአማካኝም የኢንዱስትሪዎች የማምረት እቅም 56 በመቶ ደርሷል። እስከ 70 በመቶ ድረስ አቅማቸውን የሚጠቀሙ አምራች ኢንዱስትሪዎችም ተፈጥረዋል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አብዛኞቹ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ናቸው።

በተለይም በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ የተደረገው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን ስለሚበረታታ የማምረት ሥራቸውን እንዲያስፋፉና የገበያ ድርሻቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል። በኢንዱስትሪና በፍጆታ ዕቃዎች ምርት ዘርፎች የተሠማሩ ተኪ ኢንዱስትሪዎች፣ ያለባቸውን ችግሮች አስወግደው በቂ ምርት እንዲያምርቱ ዕድል ይሰጣል።

በተለይም በዘርፉ የሚስተዋሉ ፤ የፋይናንስ አቅርቦት ውስንነቶች ፣ የሃይል አቅርቦት መቆራረጦች፣ የጸጥታ ችግሮች ለአምራች ኢንዱስትሪያዊ ፈተና ሆነው እንዳይቀጥሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይጠበቅበታል።

በሌላም በኩል በዘርፉ ያለውን የሥራ ባህል ማሻሻልና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሳደግ ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚሳተፉ ባለሀብቶችና አምራቾች ሚና ሊሆን ይገባል። ኢንቨስትመንትን ለማቀላጠፍ የሚያስችለውን የአንድ መስኮት አገልግሎት በአግባቡ መስጠትና የተንዛዛ እና ውጣ ውረድ የበዛበትን አገልግሎት ማስወገድ ደግሞ የተቋማት ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።

ኢትዮጵያውያንም በሀገራቸው ምርት በመኩራት ሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎች ያመረቱትን ምርት መሸመት የዜግነት ግዴታችን መሆኑን መረዳት ይጠበቅብናል። ይህ ሲሆን ሀገራዊ የማምረት አቅም ይጎለብታል፤ የኑሮ ውድነትን ይቀንሳል፤ ተጨማሪ የሥራ እድሎች ይፈጠራሉ፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ይቃለላል፤ ተወዳዳሪ ሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ለመገንባት ያስችላል።

ኢትዮጵያም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶችን አምርታ ለመሸጥ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ያስችላታል። ይህም የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ የምታደርገውን ጥረት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚያሻግር ይሆናል። የኢትዮጵያም ብልጽግና ይረጋገጣል።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You