በሀገራችን በዘመናት መካከል የብዙ ትውልዶችን ትኩረት ከሳቡ ሀገራዊ አጀንዳዎች ዋነኛው የዓባይ ወንዝ ውሃ ነው። የወንዙን ውሃ በመጠቀም ሀገርን የማልማት እሳቤዎች በብዙ ቁጭት ከትውልድ ትውልድ እየተላለፉ ዛሬ ላይ ስለመድረሳቸው የታሪክ መዛግብ በስፋት ያትታሉ።
በሀገሪቱ ዘላቂ ልማት ማምጣት የሚያስችል ሰላም አለመኖር ፣ የወንዙን ውሃ ለማልማት የሚያስፈልገውን ሀብት የማፈላለግ ጥረቶች በሴራዎች እና በዓለም አቀፍ ጫናዎች ምክንያት ውጤታማ አለመሆናቸው የፈጠሩት ተግዳሮት ፣ የብዙ ትውልዶች መሻት የሆነውን ወንዙን የማልማት ፍላጎት ወደ ተግባር ሳይለወጥ ዘመናት ተቆጥረዋል።
የሕዝባችን ወንዙን የማልማት መሻት ተከትሎም በየወቅቱ በሚፈጠሩ አካባቢያዊና ዓለም አቀፍ ሴራዎች፣ ሀገር ለብዙ ፈተናዎች ተጋልጣለች፤ ከእያንዳንዱ ፈተና በስተጀርባ በግልጽም ይሁን በስውር የሚስተዋሉ እጆች፤ በአንድም ይሁን በሌላ ወንዙን ለማልማት ካለን ፍላጎት ጋር የተቆራኙ ስለመሆኑም የአደባባይ ምስጢር ነው።
በዚህም የዛሬውን ትውልድ ጨምሮ በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች ብዙ ዋጋ ለመክፈል ተገድደዋል። እንደ ሀገር በግጭት አዙሪት ውስጥ አልፈናል፤ የብዙ የመልማት አቅም እና ተስፋ ባለቤቶች ሆነን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኋላቀር እና ተመጽዋች ለመሆን ተገድደናል።
ይህንን በብዙ የሴራ ትርክት ፣ ተጠላልፎ ከዘፈን ስንኝ ማሳመሪያነት ሳያልፍ ዘመናት ያስቆጠረውን የወንዙን ውሃ የማልማት ትውልዳዊ መነሳሳት አሁን ላይ በሕዝባችን ውስጥ በተፈጠረው ቁጭት ቁጭቱ በፈጠረው የይቻላል መንፈስ እና ከፍ ባለ የአመራር ቁርጠኝነት ዓለም ወደ አስደማሚ ታሪካዊ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
“አይችሉትም ፣ አይሳካላቸውም” ባሉ እና ይህንንም አፋቸውን ሞልተው በየአደባባዩ ሲያወሩ እና ሲያስወሩ በነበሩ ኃይሎች ፊት ፣ የወንዙን ውሃ የማልማት ጅሬሪ የሆነውን የዓባይ ግድብ ግንባታ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ እየተገነባ አሁን ላይ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል።
የግድቡ የግንባታ ምዕራፍ ከትናንሽ የማጠናቀቂያ ሥራዎች ውጪ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተጠናቋል፤ ቀደም ሲል ወደ ሥራ ከገቡት ሁለት ተርባይኖች ውጪ ከትናንት በስቲያ ተጨማሪ ሁለት ተርባይኖች ወደ ሥራ ገብተዋል፤ የግድቡ ግንባታም ሙሉ በሙሉ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።
መላው ሕዝባችን ከዕለት ጉርሱ ከዓመት ልብሱ ቆጥቦ ፣ አብዛኛው ሕዝባችን ከጉድለቱ ላይ በማዋጣት በራሱ አቅም ወደ ፍጻሜ ያደረሰው የዓባይ ግድብ ፣ ለግንባታው የሚያስፈልገውን ሀብት እንዳናገኝ የተደረገውን በሴራ የተሞላ መንገድ በመቁረጥ፣ ጠባቂነትን መስበር ያስቻለ ትልቅ ስኬታማ ሀገራዊ ተሞክሮ ሆኗል።
ሕዝባችን በአንድነት በመቆም ታላላቅ ታሪክ የመሥራት የቀደመ ተሞክሮ፣ በዚህ ትውልድ መድገም ያስቻለ፤ በአንድነት ከቆምን ባለን ነገር ያሰብነውም ማሳካት እንደምንችል በተጨባጭ ያሳየ ነው። ለዚህ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለመጪዎቹ ትውልዶች የይቻላል መንፈስ ህያው ማሳያ ሆኖ የሚወሰድ ነው።
እንደ ሀገር በሰላም ወቅት ብቻ ሳይሆን በችግር ወቅት ፣ በዓለም አቀፍ ትብብር ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ጫና ውስጥም ሆነን፣ በጋራ መንቀሳቀስ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ከቻልን፣ ከችግሮች እና ከጫናዎች በላይ ሆነን መጓዝ እንደምንችል ያሳየ የስኬታማነት እና የጽናት ማሳያ ነው።
በተባበረ ክንዳችን ዛሬ ላይ የግድቡን ግንባታ ፍጻሜ ላይ ማድረሳችን፤ የቀደሙት አባቶቻችን ታላቅ በሆነ የሀገር ፍቅር ፣ በብዙ መስዋዕትነት ሀገራዊ ኩራት የሆነውን የዓድዋን ድል ያበሰሩበት ያ መንፈስ አሁንም በዚህ ትውልድ ውስጥ ህያው ሆኖ የሀገር ብልጽግና፣ ከብልጽግና የሚመነጭ ሀገራዊ ኩራት እየሆነ ስለመሆኑም መገለጫ ነው።
መላው ሕዝባችን እና በዚህ ግንባታ ተባባሪ የሆኑ ወዳጆቻችን በብዙ ፈተናዎች ዘመናትን አቋርጦ ዛሬ ላይ ለትውልዱ የኩራት ምንጭ የሆነው የዓባይ ግድብ የፍጻሜ ምዕራፍ ላይ በመድረሱ እንኳን ደስ አላችሁ እንላለን፤ በቀጣይ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የወንዙን ውሃ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ አልምቶ የብልጽግናችን አቅም ለማድረግ በሚደረጉ ጥረቶች የዛሬ አንድነታችን ፣ የቁጭት ተሳትፏችን እና ቁርጠኝነታቸን ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እንላለን!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21/2016 ዓ.ም