እንደ ጣዖት የሚያዩትን የዓባይን ወንዝ ውሃ ከምንጩ ለመቆጣጠር ግብፅን ጨምሮ ሀገሪቱን በተለያዩ ወቅቶች በቅኝ የገዙ ኃይሎች በግልጽ እና በስውር የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ ኢትዮጵያውያንም በየዘመኑ ብዙ ዋጋ በመክፈል ፍላጎቱ ከንቱ ሆኖ እንዲቀር አድርገዋል ።
ከግልጽ ጦርነት ጀምሮ በቅኝ ግዛት ዘመን በተለያዩ ወቅቶች በወንዙ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ የተደረሰባቸው ኢ-ፍትሐዊ ስምምነቶች የፋይዳ ቢሱ ፍላጎቶች ማሳያ ናቸው። በዚህም ዘመን በወንዙ ውሃ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችም ፍላጎቶች የቱን ያህል ዘመን ተሻጋሪ እንደሆኑ አመላካች ናቸው።
ፍትሐዊነት እና የጋራ ተጠቃሚነት ዓለም አቀፍ መርሕ በሆነበት ባለንበት ዘመን፤ የግብፅ መንግሥት ዘመን ያለፈባቸውን፤ በቅኝ ገዥዎች ፍላጎት ላይ የተመሠረቱ ስምምነቶችን መሠረት በማድረግ፤ የወንዙ ውሃ የወንድማማችነት እና የጋራ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ምንጭ እንዳይሆን መሰናክል ሆኗል።
በሀገሪቱ ወደ ሥልጣን የሚመጡ መንግሥታት የወንዙን ውሃ ባልተፈለገ መንገድ የፖለቲካ አጀንዳ በማድረግ፤ በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር ሊኖራቸው የሚችለውን ዘላቂ የጋራ ተጠቃሚነት ዕድል ትርጉም ወደሌለው የጠላትነት እና የግጭት መነሻ ለማድረግ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲንቀሳቀሱ ማየት የተለመደ ነው።
ይህ የተሳሳተ መንገዳቸው የግብፅ ሕዝብ አጠቃላይ ስለሆነው የወንዙ ውሃ እና ከውሃው ጋር በተያዙ አጀንዳዎች ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ እንዳይኖረው ከማድረግ ባለፈ፤ በሀገራቱ ሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ከመሸጋገር ይልቅ ወዳልተገባ የተቃርኖ መንገድ እንዲጓዝ ጫናዎችን እየፈጠሩ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ በዘመናት መካከል ከግብፅም ይሁን ከሌሎች ሀገራት እና ሕዝቦች ጋር ያላቸው ግንኙነት ወንድማማችነትን፣ መከባበርን እና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ነው። የቀደመውም ሆነ አሁናዊ ታሪካቸውም ይህንን እውነታ በተጨባጭ የሚያመላክት ነው።
ለጎረቤት ሀገራት ችግር ቀድሞ መድረስ፤ የሌሎችን ችግር የራስ አድርጎ መመልከት ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ከሚታወቁበት አንዱ መገለጫቸው ነው፤ ይህ ከእለት ተእለት ማኅበራዊ መስተጋብራቸው የሚመነጨው እሴታቸው፤ ድንበር በሚሻገረው ሀገራዊ የግንኙነት ምዕራፍም ጎልቶ የሚታይ ነው።
ለዚህም አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ለመውጣት ባደረጉት መራራ ትግል፤ የትግሉ አጋር የሆኑበት፤ ትግሉን በሥነልቦና፤ በሎጅስቲክ እና በሥልጠና በማገዝ፤ የሄዱበት ረጅም መንገድ፤ በዚህም የጻፉት ወንድማማችነት የዚህ እውነታ ማሳያ ነው። በሠላም ማስከበር ተልዕኮዎች ውስጥ ያበረከቱት ዓለም አቀፋዊ አስተዋፅዖም ከዚሁ ጋር የሚጠቀስ ነው።
በግብፅ በኩል ለዘመናት የተቃርኖ እና የግጭት ምንጭ የሆነውን የዓባይ ወንዝ ውሃ በፍትሐዊነት ለመጠቀም ይቻል ዘንድ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ የተፋሰሱን ሀገራት በማስተባበር እየሄደችበት ያለውም መንገድ፤ በሀገራት መካከል መተማመንን በመፍጠር የጋራ ተጠቃሚነትን ማስፈን የሚያስችል ነው።
በአሁኑ ወቅትም የአካባቢው ሀገራት የወደፊት ዕጣ ፈንታ /ብሩህ ነገዎች/ የሚወሰነው ሀገራቱ ያላቸውን አቅም አቀናጅተው ሲንቀሳቀሱ ብቻ ነው በሚል፤ አቅማቸውን አቀናጅተው መሄድ የሚችሉበትን ዕድል ለመፍጠር እየሄደችበት ያለው መንገድ፤ አካባቢው አዲስ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ኮሪደር ሊያደርገው እንደሚችል ይታመናል።
ከሶማሌ ላንድ ጋር የተደረሰበት ከወደብ ጋር የተያያዘ የመግባቢያ ስምምነት የዚሁ እውነታ አካል፤ ለአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚከፍት፤ አካባቢውን ከግጭት ቀጠናነት ወደ ልማት ኮሪደርነት የሚለውጠው ነው። ይህ ደግሞ የአካባቢው ሀገራት የዘመናት መሻት ነው።
የግብፅ መንግሥት በዓባይ ውሃ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ የተዘረጉ ሠላማዊ እጆችን ከመቀበል ይልቅ፤ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦችን የመልማት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገውን ይህንን የመግባቢያ ስምምነት እንደተለመደው የተቃርኖ እና የግጭት ምክንያት ለማድረግ መንቀሳቀስ ከጀመረ ውሎ አድሯል።
ለሶማሌ ሕዝብ ብዙ ዋጋ በመክፈል አሁን ላይ ላሉበት አንጻራዊ ሠላም ባለውለታ ከሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት በላይ ለሶማሊያ ሕዝብ አሳቢ በመሆን፤ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፤ ከዚህ ይልቅ በሶማሊያ ሕዝብ አብሮ የመልማት እና የማደር ፍላጎት ላይ በተቃርኖ የቆመ ነው።
ኢትዮጵያ ለሶማሌና ሶማሌያውያን ሠላምና መረጋጋት የከፈለችውን ዋጋ ለማሳነስ መሞከር የጥፋት መንገድ አካል ነው፤ ውጤቱም የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ያላቸውን አቅም አቀናጅተው የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው በመወሰን፤ እንደ አንድ ዘመናዊ ማኅበረሰብ ወደ ብልፅግና የሚያደርጉትን ጉዞ የሚጻረር ነው።
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም