በክረምት የሚበረታው የአደጋ ተጋላጭነት

ዜና ሐተታ

በዓለም ዙሪያ የብዙዎችን ንብረት ከማውደም ጀምሮ ከባድ የአካል ጉዳት አለፍ ሲልም ሕይወትን እስከማሳጣት የሚያደርሱ የትራፊክ አደጋዎች በተደጋጋሚ ይሰማሉ፡፡

በኢትዮጵያም በአዲስ አበባ ብቻ በ2016 በጀት ዓመት ከ300 በላይ ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል፡፡ ይህ የትራፊክ አደጋ ምንም እንኳን ጊዜ እና ቦታ የማይመርጥ ቢሆንም በክረምት ወራት ግን በስፋት ይስተዋላል፡፡ ለመሆኑ ከክረምቱ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የትራፊክ አደጋ ለመከላከል ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ አለብን?

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ እንደሚገልጹት፤ የትራፊክ አደጋ ክረምትና በጋ የማይመርጥ ቢሆንም በክረምት ወራት የበዛ አደጋ ይስተዋላል፡፡ አሁን ላይ የክረምት ወራት በመገባደድ ላይ ቢሆንም የክረምቱ ሁኔታ እጅግ ከባድ እየሆነና በተለያዩ አካባቢዎችም ለአደጋ መከሰት ምክንያት እየሆነ ነው፡፡

በተለይም ከዝናቡ ጋር ተያይዞ የመሬቱ የእርጥበት ተከትሎም ከፍጥነት በላይ የሚያሽከረክሩና የትራፊክ መብራትን የማያከብሩም በርካታ አሽከርካሪዎች ፍሬን ለመያዝ የማይችሉበት ሁኔታ ይፈጠርና አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

በቀንም ሆነ በማታ በመስቀለኛ ቦታዎች ላይ በከፍተኛ ፍጥነት የሚያሽከርክሩ አሽከርካሪዎች ከፍተኛ አደጋ እያደረሱ ሲሆን በነዚህ ምክንያት የሚከሰት አደጋም ለሞት ወይም የከፋ አካል ጉዳት የሚያጋልጥ መሆኑን ያብራራሉ፡፡

እንዲሁም የማይሠራ የዝናብ መጥረጊያ፣ ጎማው ሊሾ የሆነ እና ያለቀ የፍሬን ሸራ የመሳሰሉት ቴክኒካል የሆኑ ጉዳዮች ያለው ተሽከርካሪ ማሽከርከር ከክረምቱ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የትራፊክ አደጋ እንዲባባስ ያደርጋሉ፡፡

በመሆኑም የሚሠራ የመኪና መስታወት መጥረጊያ፣ መብራት፣ ጎማ፣ ፍሬቻዎችና አንጸባራቂዎች የመሳሰሉት ማሟላት በክረምት የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ከመከላከል አንጻር ከፍተኛ ሚና ስላላቸው ተገቢውን ሰርቪስ ያደረገ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

አሽከርካሪዎችም ዋነኛ ትራፊክ የአደጋ ምክንያት ፍጥነት ስለሆነ ፍጥነትን ረገብ አድርጎ በተፈቀደው የፍጥነት ወሰን የማሽከርከርና እና የአየር ሁኔታን ግምት ውስጥ ያስገባ የማሽከርከር ክህሎት ሊኖራቸው እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ በተለይም የትራፊክ መብራቶችንና ምልክቶችን ማክበር እንደሚኖርባቸው ያመላክታሉ፡፡

በአጠቃላይ የተሽከርካሪዎችን ሁኔታ በምን መልኩ ነው መጠበቅ ያለበን፤ አደጋ ሊከሰትባቸው የሚችሉ ቦታዎች የትኞቹ ቦታዎች ናቸው፤ መከተል ያለብን የአነዳድ ስልት ምንድነው? የሚለውን ግምት ውስጥ ማስገባት የሚያስፈልግ መሆኑን ያብራራሉ፡፡

ኮማንደሩ እንደሚገልፁት፤ እግረኞች ብዙ ጊዜ የእግረኛ መንገዶች በውሀ ሲሞሉ ከጎርፍ ለመሸሽ በመኪና መንገድ ላይ ጀርባን ሰጥቶ የመሄድ፤ የትራፊክ መጨናነቅ ሲኖር ተሽሎክሉኮ ለማለፍ መሞከር፣ ዝናብን ለመሸሽ ግራና ቀኝ ሳያስተውሉ አስፋልት ማቋረጥ በስፋት ይስተዋላል፡፡

እራሳቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ እግረኞች መንገድን ከማቋረጣቸው በፊት በአሽከርካሪዎች መታየታቸውን እርግጠኛ መሆን፣ ግራኛ ቀኝ ማየት እና በእግረኛ ማቋረጫ ብቻ መጠቀም እንደሚኖርባቸው ይገልጻሉ፡፡

በክረምት ወራት አደጋ እንዳይበዛ እንደተቋም ልዩ የሦስት ወራት እቅድ በማውጣትም በክረምት ወቅት ሊደርሱ የሚችሉ የትራፊክ አደጋዎችን ከመቆጣጠር አንጻር፣ የአደጋ ስጋቶች የሆኑ አካባቢዎችን የመለየት እና የትኛውን የቁጥጥር ሥርዓት መጠቀም እንደሚያዋጣ በመለየት እየሠሩ መሆኑንም ያብራራሉ፡፡

የመንገድ ደኅንነት ባለሙያ እና አውቶሴፍቲ የሬዲዮ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ በበኩላቸው፤ የትራፊክ አደጋ በየትኛውም ወቅትና ሰዓት የሚከሰት ቢሆንም በክረምት ወቅት የሚኖር ዝናብ ምክንያት አደጋዎች እንደሚበዙ ይናገራሉ፡፡

ይህም በተፈጥሮ ዝናብን ተከትሎ የሚከሰት የመሬት እርጥበትና የመሬት አንሸራታችነት፣ በረዶ፣ ጎርፍ፣ የአየር ጭጋግና ጉም የመሳሰሉት ሁኔታዎች በአጠቃላይ ለሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች አባባሽ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም የአሽከርካሪ ብቃትና የተሽከርካሪ ቴክኒካል ጉዳይ ለአደጋው መበራከት መንስኤ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የተሽከርካሪዎችን ቴክኒካል ሁኔታዎች በጥንቃቄ ማወቅና ማሟላት የሚገባቸውን እንደ የተሽከርካሪ ጎማ፣ ፍሬን፣ የዝናብ መጥረጊያ የመሳሰሉት በቸልታ ሊታለፉ የሚገባቸው እንዳልሆኑ ያብራራሉ፡፡ የተጠቀሱት ነገሮች ላይ ክትትል አለማድረግ በክረምት ወትት ለአደጋ ያጋልጣሉ ይላሉ፡፡

ከተሽከርካሪ ቴክኒካል ሁኔታዎች በተጨማሪም አሽከርካሪዎች የአየር ፀባይ አለመገንዘብ እና የአካባቢን መልክዓ ምድር አለማወቅ፤ ብሎም በዝናብ ምክንያት አስፋልት በውሀ ሲሸፈን አማራጭ መንገዶችን አለመጠቀም በተለይም ሕዝብ ማመላለሻ የሚያሽከረክሩ ላይ የሚስተዋል ችግር መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

የአሽከርካሪዎች የማሽከርከር ስልት ሥልጠና የሚሰጠው በክፍል ውስጥ እና ዝናብ በሌለበት ቦታ ላይ በመሆኑ በዝናብ ወቅትና በጭቃ መንገድ ላይ የማሽከርከር ብቃትን ለማስተማርም ሆነ ለመለካት አዳጋች አድርጎታል ይላሉ፡፡

እግረኞች የመንገድ አጠቃቀም አስተሳሰብ ኋላቀር መሆኑን የሚጠቅሱት ኢንስፔክተር አሰፋ፤ ይህም ዝናብን በመሸሽ ወደ አስፋልት መግባት የተሳሳተ አካሄድን የሚከተሉ መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡ የትኛው የሚጎዳና ሕይወት የሚያጠፋ መሆኑን አለማገናዘብ በእግረኞች ላይ በስፋት የሚስተዋል መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የአንድን ተሽከርካሪ ፍጥነትን ጨምሮ ማሽከርከር የአሽከርካሪውን ዕይታ እንደሚቀንስ በማስገንዘብ፤ ይህም እግረኞች አሽከርካሪው ያያል በማለት እና በመዘናጋት የሚያደርጉት የመንገድ ማቋረጥ ሆነ በአስፋልት ላይ መራመድ ለሞት እንዲዳረጉ የሚያደርግ ምክንያት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

እንዲሁም ዕይታን የሚከልሉ አለባበሶችንና ጆሮ እንዳይሰማ የሚያደርግ ማዳመጫዎችን ማድረግ፣ ከመኪና ሲወርዱ ዝናብ ለማምለጥ በመሞከር ቀጥታ ወደ አስፋልት መግባት ሌሎች ለአደጋ አጋላጭ መንገዶች መሆናቸውን ያመላክታሉ፡፡

የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመከላከልም በዝናብ ወቅት እስኪያባራ ማሽከርከር ማቆም፣ ፍጥነትን መቀነስ፣ የመኪናውን ቴክኒካል ጉዳዮች በተለይም እይታን የሚጋርዱ ነገሮችን በማስወገድና የመስታወት መጥረጊያ በትክክል መርምሮ ማሟላት እንደሚያስፈልግ ያገናዝባሉ፡፡

ከተማው ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በአስፋልት ላይ ጎርፍ እየተስተዋለ መሆኑን አንስተው፤ ይህም የመንገዱን ሁኔታና ውሀውን የሚመጥን የውሀ ማፍሰሻ ቱቦ አለመኖር ምክንያት የሚፈጠር መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች በክረምት ወቅት ለሚደርሰው የከፋ የትራፊክ አደጋ ተጠቃሽ ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ያነሳሉ፡፡

መንገድ የሚሠሩ የመንገዶች ባለሥልጣን በክረምት ወቅት ውሃ የሚሞላ ቦታን ለይቶ በምልክት መገደብ ወይም እንዲስተካከል ማድረግ አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ፡፡

ማሕሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You