![](https://press.et/wp-content/uploads/2019/07/ታተተተ-2-11-2-1.png)
ስለ ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ስናነሳ ዋናው ማጠንጠኛ የተለያዩ ሀሳቦችን ከእነ ልዩነታቸው ማስተናገድ መቻላችን ነው፡፡ ይህን ልዩነት ለማስተናገድ ደግሞ መግባባት ቁልፍ ሚና አለው፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለየ ሁኔታ የሚነሳው ብሔራዊ መግባባት ነው፡ ፡
በአንድ ሀገር ብሔራዊ መግባባት ሊኖር የሚችለው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ የሆነ አቋምና አመለካከት ሲኖረን ነው። በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ግልፅና ነፃ ውይይት በማድረግ የጋራ ግንዛቤ ሊፈጠር ይገባል ማለት ነው።
ስለሆነም ብሔራዊ መግባባት እንዲኖር ዜጎች በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት የሚያደርጉበት፤ ሃሳብ የሚለዋወጡበት፣ እምነትና አመለካከታቸውን የሚያንፀባርቁበት፣ ያሏቸውን ጠቃሚ ልምዶች፥ እሴቶችና ባህሎች የሚጋሩበት…ወዘተ፣ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት የፀዳ የጋራ የሆነ መድረክ ሊኖራቸው ይገባል። ይህ ሲሆን በእርግጥም የዴሞክራሲ ስርዓትን መገንባት እንችላለን ማለት ነው፡፡
ይህ ካልሆነ ደግሞ በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ የሆነ ግንዛቤ በዜጎች ዘንድ መፍጠር አይቻልም። በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በቂ የሆነ ግንዛቤ የሌላቸው ዜጎች ብሔራዊ መግባባትን በሚያሳይ መልኩ የጋራ አቋምና አመለካከት እንዲያንፀባርቁ መጠበቅ “ላም ባልዋለበት…” ይሆንብናል።
ስለዚህ፣ በሀገራችን ብሔራዊ መግባባት ላለመኖሩ በዋና ምክንያትነት ሊጠቀስ የሚገባው ነገር ነፃና ገለልተኛ የሆነ የውይይት መድረክ አለመኖር ነው። የውይይት መድረኮች ደግሞ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትልቅ አቅምና ጉልበት መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡
በተመሣሣይ፣ እንደ ትምክህት፥ ጠባብነትና አክራሪነት ያሉ ፅንፈኛ አመለካከቶች በሀገሪቱ ውስጥ እንዲስፋፉ ያደረገው ነፃ የውይይት መድረክ በርክተው አለመኖራቸው አንዱ ምክንያት ነው። በተለይ በዚህ ረገድ የማይካደው ጉዳይ ስለ ብሔራዊ አንድነትና የቀድሞ ታሪክ የሚናገሩትን ወገኖች “ትምክህተኞች”፣ የብሔርተኝነትና እኩልነት ጥያቄ የሚያነሱትን ወገኖች ደግሞ “ጠባቦች”፣ እንዲሁም ስለ ሃይማኖትና እምነት ነፃነት የሚጠይቁትን “አክራሪዎች” ብሎ በጅምላ በመፈረጅ ያላቸውን የተለየ ሃሳብና አመለካከት በነፃነት እንዳያንፀባርቁ ገትቷል፤ ይህ መቆም አለበት፡፡
ማንኛውም ሀሳብ እንዲንሸራሸር እድል ያግኝ፤ ሀሳቡም እየተለየ እና ደጋፊ እያጣ እንዲከስም የሚደረገውም በውይይት ብቻ እንጂ በሀይል በመድፈቅ አይደለም፡፡ ይህ የዲሞክራሲ ስርዓት መርህ በመሆኑ ዞሮ ዞሮ ጥቅሙ ለሀገር ይሆናል፡፡ ይሕ ካልሆነ ግን ዲሞክራሲያችን ላይ ትልቅ አደጋ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
ዜጎች ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት የሚያንፀባርቁበት የጋራ መድረክ አለመኖሩ ወይም መነፈጋቸው ይበልጥ ፅንፈኛ እየሆኑ እንዲሄዱና ይህንንም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በማህበረሰቡ ውስጥ ለማስረፅ ጥረት እንዲያደርጉ አድርጓቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በውይይት ያልዳበረና በምክንያታዊ ዕውቀት ላይ ያልተመረኮዘ ግንዛቤ የሌለው ማህበረሰብ ለፅንፈኛ አመለካከቶች ተጋላጭ ቢሆን ሊገርመን አይገባም።
ስለዚህ፣ ከብሔራዊ መግባባት በተጨማሪ፣ ‹‹ለትምክህት፥ ጠባብነትና አክራሪነት›› አመለካከቶች በሀገሪቱ እንዲስፋፉ በዋና ምክንያትነት ሊጠቀስ የሚገባው ነገር ነፃና ገለልተኛ የሆነ የውይይት መድረክ አለመኖሩ ነው።
ከላይ በዝርዝር ለመጥቀስ እንደተሞከረው፣ ለብሔራዊ መግባባት መጥፋት እና ‹‹ለትምክህት፥ ጠባብነትና አክራሪነትን ፅንፈኝነት›› መፈጠር ዋና ምክንያቱ ነፃና ገለልተኛ የሆነ መድረክ አለመኖር ነው።
ነፃና ገለልተኛ የሆነ የውይይት መድረክ እንዲኖር ደግሞ በቅድሚያ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ያለ ምንም መሸራረፍ ሲከበር ነው፡፡ ይህን መብት ስንጠቀምም ሀሳቦቻችንና አስተያየቶቻችን ከዲሞክራሲ መርህ ውጭ ሆነው እውነት የለሽ ሊሆኑ አይገባም፡፡ ይህ ሲሆን ዲሞክራሲያችን ወደ ፊት ሳይሆን ወደ ኋላ ይጎተታል፡፡
ዜጎች ስለ ራሳቸው ችግር በግልፅ ለመናገር የሚፈሩ ከሆነ ስለ ሌሎች ጉዳዮችም ሆነ ስለ ሌሎች እህትና ወንድም ዜጎቻቸው ችግር ለመስማት ፍላጎት አይኖራቸውም፡፡ ስለ ራሱ መብትና ነፃነት መከበር በግልፅ ለመናገር ዕድል የሌለው ዜጋ ስለ ሀገር አንድነትና ልማት እንዲናገር መጠበቅ “የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች” የሚሉት ዓይነት ይሆናል።
በአጠቃላይ ይህ ወቅት ዴሞክራሲን የምንገነባበት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ይህን እድል በእርጋታ፣ በትዕግሥትና በአርቆ አሳቢነት ለመጠቀም የተለያዩ የውይይት መድረኮች ያስፈልጉናል፡፡
ከዚህ ውጭ በሰከነ መንገድ ተነጋግሮ ለችግሮች ሰላማዊ መፍትሔ ማመንጨት መለማመድ ሲቻል ግድያ ውስጥ ለምን እንገባለን? በግልጽ ተነጋግረን በሕዝብ መዳኘት ሲገባን አንዳችን ሌላውን ለምን እናጠፋለን? በዚህ ሁኔታስ የዘመናት የተከማቸ ችግራችን ማቆሚያው የት ነው? ወጣቱንስ ምን እያስተማርነው ነው? አገሪቱንስ ወዴት እየወሰድናት ነው? አገርን ከድጡ ወደ ማጡ ከመክተት በስክነትና በጨዋነት መነጋገር ይበጃል፡፡ ይህ ለማድረግም በየደረጃው በሃገራዊ ጉዳዮች ዙርያ ነጻ የውይይት መድረኮች ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2011