
ዜና ትንታኔ
በተለያየ መንገድ ከሃገራቸው የወጡ ዲያስፖራዎች ተመልሰው ሃገራቸውን በገንዘብ፣ በእውቀት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ማገዝ የተለመደ ነው። ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎችም መጠኑ ይለያይ እንጂ በተለያየ መልኩ ለሃገራቸው ድጋፍ ያደርጋሉ።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ከተጀመረ ጀምሮ እስከ 2016 በጀት ዓመት መጨረሻ አንድ ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በቦንድ ግዢ እና በስጦታ ከዲያስፖራው መገኘቱ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ዲያስፖራው ለሃገሩ ልማት በገንዘብ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር ያደጉ ሃገራትን ልምድ እና እውቀት በማምጣት እደረገ ያለው ድጋፍ ምን ይመስላል? የሚያደርገው ድጋፍስ እንዴት ማደግ አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ የዲያስፖራ ማኅበሩን እና የሚመለከታቸውን አነጋግረናል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደመቀ ነጋሳ እንደሚሉት ዲያስፖራው በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሁም በማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ትልቅ ተሳትፎ ያደርጋል።
በዚህም ሃገሩን ጠቅሞ እራሱም ተጠቃሚ እንደሆነ የሚገልጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ በመሠረተ ልማቶች ግንባታ፣ ሆስፒታሎችን በመደገፍ የራሳቸውን ዐሻራ እያኖሩ እንደሆነ ይገልጻሉ። በቅርቡም ምሥራቅ ሐረርጌ ላይ ዲያስፖራዎች በርካታ የሕክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ እንዳደረጉም በአብነት ይናገራሉ።
ብዙ ዲያስፖራዎች በአደጉት ሃገራት በመማራቸው እና በመሥራታቸው እውቀት እና ልምድ ማካበታቸውን የሚገልጹት አቶ ደነቀ፤ ይህንን ልምድ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ሃገር ተጠቃሚ ትሆናለች ይላሉ። አንዳንድ ጊዜ በሚያጋጥሙ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ድጋፍ ማድረግ በሚችሉት መጠን የማያደርጉ ዲያስፖራዎች መኖራቸውን ተናግረው፤ አገር ሁልጊዜም ሃገር በመሆኗ የፖለቲካ ልዩነቶችን ትቶ ለሃገር የሚችሉትን ማድረግ እንደሚያስፈልግም ይገልጻሉ።
በእርሻ እና በሕክምና ዘርፍ እንዲሁም በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሠማሩ ዲያስፖራዎች መኖራቸውን የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ ሌሎቹም ዲያስፖራዎች ወደ ሃገራቸው በመምጣት በተለያዩ ዘርፎች በማልማት እና የሥራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም በእውቀት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ሃገራቸውን ማገዝ እንደሚችሉ ይናገራሉ።
የዲያስፖራ ማኅበሩ በርካታ ችግሮችን መፍታቱን የሚናገሩት አቶ ደመቀ፤ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር ለዲያስፖራው ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሥራዎች በማኅበሩ በኩል እንደሚሠሩም ይገልጻሉ።
ማኅበሩ አባላቶቹን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የማበረታታት ሥራዎችን እንደሚሠራ የሚናገሩት አቶ ደመቀ፤ ዲያስፖራው ወደ ሃገሩ ለእረፍት ሲመጣ ካለው ጊዜ አብቃቅቶ ለአጭር ጊዜ የሚመጣ በመሆኑ በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤቶች ያለው አገልግሎት አሰጣጥ ብዙዎች ችግር እንዳለበት የሚያነሱት በመሆኑ አገልግሎት አሰጣጡ መሻሻል እንዳለበትም ይጠቁማሉ።
በርካታ ሃገራት በዲያስፖራዎቻቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን አውስተው፤ ኢትዮጵያ በዲስፖራዎቿ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን ዲያስፖራውን በሚፈለገው መጠን ማሳተፍ ያስፈልጋል ይላሉ። ዲያስፖራው በተደጋጋሚ የሚጠይቀው የሁለት አገር ዜግነት ሕግ ተሻሽሎ በሚፈልገው ልክ እንዲሳተፍ ቢደረግ መልካም መሆኑንም ይናገራሉ።
የዲያስፖራ ማኅበሩ የቦርድ አማካሪ አቶ ኤርሚያስ መኮንን በበኩላቸው እንደሚሉት ዲያስፖራው ሃገሩን በእውቀት እንዲሁም በኢንቨስትመንት ማገዝ ይችላል። ኢትዮጵያ ጥሩ የአየር ንብረት፣ ባሕል እንዲሁም ሰፊ የሕዝብ ቁጥር ያለባት ሃገር በመሆኗ ዲያስፖራዎች መጥተው ኢንቨስት ቢያደርጉ ሃገራቸውንም ጠቅመው እራሳቸውም እንደሚጠቀሙም ይናገራሉ።
ዲያስፖራው ፖለቲካዊ ልዩነቶች እንዳሉ ሆነው ሃገርን የሚረዳበትንና የሚያሳድግበትን መንገድ በማሰብ የሞራል ግዴታም ጭምር በመሆኑ በእውቀታቸው እና በገንዘብ ለሃገር ልማት ድጋፍ በማድረግ ሃገር መለወጥ ላይ መሳተፍ አለብን ይላሉ።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ወንደሰን ግርማ እንደሚሉትም የዲያስፖራው ተሳትፎ ዘርፈ ብዙ ነው። በእውቀት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በኢንቨስትመንት እና በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዲያስፖራው ለሃገሩ ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ እንደሆነም ይገልጻሉ።
ባለፉት አምስት ወይም ስድስት ዓመታት በኢንቨስትመንት 30 ቢሊዮን ብር በላይ ያስመዘገቡ ከ500 በላይ የሚሆኑ የዲያስፖራ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ገብተው በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸው ያወሳሉ።
አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ የዲያስፖራው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተው፤ ከሃገር እድገት ጋር በቀጥታ ከሚገናኙት እውቀት፣ ክህሎት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ዲያስፖራው የሚታይ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ይናገራሉ። ባለፉት ስድስት ዓመታት ከ700 በላይ የሚሆኑ የዲያስፖራ አደረጃጀቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በተለያዩ መስኮች ሥልጠናዎችን መስጠታቸውንም ይገልጻሉ።
በጤና፣ በትምህርት፣ በሰው ሀብት አስተዳደር እና በመሳሰሉት ሥልጠና እንደሚሰጡ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ የሕክምና መሣሪያዎችም ድጋፍም መደረጉን ያወሳሉ። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥም የሦስተኛ እና የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በማማከር እና ኮርሶችን በጋራ በመስጠት ዲያስፖራው ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ ነው ይላሉ። በዲጂታል ዲፕሎማሲውም በኩል ለሃገር ትልቅ እገዛ እንደሚያደርጉም ይናገራሉ።
በሪሚታንሱ ዘርፍም ዲያስፖራው ትልቅ ተሳትፎ የሚያደርግበት ዘርፍ ነው የሚሉት አቶ ወንደሰን፤ ኢትዮጵያ በየዓመቱ በአማካኝ ከ4 እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር በሪሚታንስ እንደምታገኝ ይናገራሉ። ይህም ኢትዮጵያ ከውጭ ንግድ ከምታገኘው ገቢ እንደሚበልጥም ይገልጻሉ።
የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረው፤ ሪሚታንሱም እየጨመረ መምጣቱን ይናገራሉ። የዲያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደ ሃገር መሠራት ያለባቸው ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመው፤ የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ለዲያስፖራው ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱን ይገልጻሉ። ዲያስፖራው በሚኖርባቸው ሃገራት ኢንቨስተሮችን ይዞ መጥቶ በሽርክና እንዲሁም በራሱ በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሳተፍ ትልቅ እድል ከፍቷል ይላሉ።
እንደ ሃገር ከዲያስፖራው መጠቀም በሚፈለገው መጠን ጥቅም እየተገኘ እንዳልሆነ የሚናገሩት አቶ ወንደሰን፤ ኢትዮጵያ ከዲያስፖራው ማግኘት የሚገባትን እንድታገኝም ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንም ይገልጻሉ።
ዲያስፖራው በእውቀት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በገንዘብ ለሃገሩ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ እሙን ነው። እየተደረገ ያለው ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ቢሆንም ግን በሚጠበቀው መጠን እንዳልሆነም ተገልጿል። መንግሥት በቅርቡ ያደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለዲያስፖራው በርካታ ዕድሎችን ይዞ የመጣ በመሆኑ የዲያስፖራው ተሳትፎ እንደሚጨምር እንደሚጠበቅም ባለሙያዎቹ ሀሳባቸውን ሰጥተውበታል።
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2016 ዓ.ም