ኢትዮጵያን በዓለም ዙሪያ በበጎ እንድትታወቅ ያደረጋት እና በስፖርቱ የዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ተሳትፏችን በሚመዘገቡ ውጤቶች ከፍተኛውን ደስታና ኩራት እንድናጣጥም የሚያደርገን የአትሌቲክስ ስፖርት ነው። ይህ ልዩ መታወቂያችን የሆነ ስፖርት ከቅርብ ግዜ ወዲህ በገጠመው አስተዳደራዊ ብቃት ማነስ ችግር ሲንገላታ እየታየ ይገኛል።
በፓሪሱ ኦሊምፒክ የሚጠበቀውና የተለመደው የሜዳሊያ ቁጥር አለመገኘት ስፖርቱ በተሳሳተ ሐዲድ ላይ እየተጓዘ መሆኑን በግልፅ ያሳየ በመሆኑ ትኩረቱን የበለጠ አድርጎት ይሆናል። እርግጥ መለኪያው ውጤት እና ሜዳሊያ ነው። ይሁንና ከዚያ ጀርባ ለውጤቱ መውደቅ የመጣንበትን መንገድ መርሳት ግን ተገቢ አይሆንም። በአደረጃጀት እና ኃላፊነት ግን የታዩትን ችግሮች እንዴት እና ለምን የሚለውን ለይቶ ማየት ተገቢ ነው።
አንዱ ሌላው ላይ በመግለጫ ጋጋታና በማኅበራዊ ሚዲያው ከሚያደርገው ድንጋይ መወራወር መቆጠብ ያስፈልጋል። ስፖርቱ ከገባበት አዘቅት የሚወጣበትን መፍትሔ መፈለግ ብቻ ነው አዋጩ መንገድ። አሁን እየሄድንበት ያለው መንገድ የስፖርቱን የቁልቁለት ጉዞ ያፋጥነዋል እንጂ የከፍታ ስኬትን ማምጣት አይቻለውም። የሚያበሳጩና ስሜትን የሚጎዱ ነገሮች ስለሌሉ ሳይሆን ስህተት በሌላ ስህተት መታረም ስለሌለበት ለእያንዳንዱ ጉዳይ ከዚህ በኋላ ምን ይደረግ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ቀጥሎስ ምን ይደረግ? ማለትም ያስፈልጋል። ከስሜታዊነት በወጣ መልኩ በስክነት መራመድ ተገቢ የሚሆነውም ለዚህ ነው።
ስፖርቱ አሁን ካለበት የአስተዳደር ችግር ወጥቶ በተሻለ ሁኔታ የሚመራበት ግዜ አሁን ነው። ስፖርቱ የሰው ብቻ ሳይሆን የአሠራር ለውጥ ያስፈልገዋል፤ ተጠያቂነት ሰፍኖ በሥርዓት የሚመራ ተቋም ለመገንባት ጊዜው አሁን ነው።
የስፖርት አመራሮች ከማንኛውም አላስፈላጊ ተፅዕኖ ነፃ ሆነው ትኩረታቸውን ስፖርቱን በማስፋፋቱ እና ማሳደጉ ላይ አድርገው የሚሠሩ ስለስፖርቱም በቂ እውቀት እና ፍቅሩ ያላቸው ቢሆኑ መልካም ነው። ለቦታው በሚመጥን እና ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት በሚችል የስፖርት አመራር የሚመራ የስፖርት ተቋምን መገንባት በተመሳሳይ ሰዓት የሀገር ግንባታን የሚደግፉ ሦስት ነገሮችን ስኬታማ ያደርጋል። በስፖርት ጤናውን የሚጠብቅ ማኅበረሰብ በመፍጠር በጤናው ሴክተር ላይ የሚኖረውን ጫና ይቀንሳል፣ በሀገር ገፅታ ግንባታ እና በኢኮኖሚው ዕድገት ላይም የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋል።
አሁን የሀገራችንን የኦሊምፒክ ኮሚቴ እና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንን የሚመሩትን ሰዎች የሚመርጠው ጠቅላላ ጉባኤ ስብጥር እንዳለመታደል ሆኖ በዚህ ዓይነት የተዋቀረ አለመሆኑ ገሐድ ወጥቷል። በመሆኑም ተቋሞቹን ለመምራት የሚመረጡትን ሰዎች የሚሰይመው ጠቅላላ ጉባኤ በግዴለሾች የተሞላ እና በተሳሳተ መንገድ በሚጓዙ ግዜም ተጠያቂ የሚያደርጋቸው እንዳልሆነ ተደጋግሞ ታይቷል።
በቶኪዮ ኦሊምፒክ በትልቅ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ የሀገርን ክብር ዝቅ የሚያደርግ ጥፋት አጥፍተውም ደግሞ የሚመርጠው እነሱኑ መሆኑን ታዝበናል። በፓሪስ ኦሊምፒክ የዝግጅት ግዜ እንዲሁም በውድድሩ ወቅት የነበሩት አስተዳደራዊ ድክመቶች ተገምግመው በኦሊምፒክም ሆነ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ተጠያቂ የሚሆን አካል የሚኖርበት ሥርዓት ሊኖር ይገባል።
በኦሊምፒኩ ኢትዮጵያ በዋነኝነት የምትጠራበት አትሌቲክስ ነው። በአትሌቲክስ ጉዳዮች ደግሞ ለምስጋናውም ለተወቃሽነቱም ዋናው ተቋም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው። ኦሊምፒክ ኮሚቴ ላይ የሚነሱት ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም የራሱን ኃላፊነት እና ድርሻ መውሰድ አለበት። አጠቃላይ አደረጃጀቱ ራሱን የቻለ ፍተሻ የሚፈልግ ተቋምም ነው። መርሕ እውነታ እና ሀገር ከሆነ ዓላማው ሁሉንም ከሁሉም አቅጣጫ አንፃር መቃኘት አስፈላጊ ነው።
ሕዝቡ ቅሬታውን በስፋት አሰምቷል፤ ስፖርተኞችና አሠልጣኞች ቅሬታቸውን ተናግረዋል፤ ባለሙያዎች ችግሩንና መፍትሔውን እየጠቆሙ ይገኛሉ። አብዛኛው ሚዲያም ለለውጥ ታግሏል፤ ይህ መቀጠል አለበት። አሁን የዱላ ቅብብሎሹ መንግሥት ጋር ደርሷል፤ መንግሥት ስፖርቱ ላይ ጣልቃ አይገባም የሚለው ሽፋን በብልሃት ሊታይ ይገባል። የሀገሪቱ ሕግ ተጥሶ አይቶ እንዳላየ በዝምታ ከመቀጠል ይልቅ የመፍትሔ አካል ሆኖ ለውጥ እንዲመጣ ማገዝ ግድ ይላል።
የኦሊምፒክ ኮሚቴ እንደማንኛውም የስፖርት ተቋማት መንግሥታዊ ተቋም አይደለም። ለትርፍም የተቋቋመ ድርጅትም አይደለም። ይህ ማለት መንግሥት መሰል ተቋማትን በቀጥታ አያስተዳድራቸውም፣ በሁሉም እንቅስቃሴያቸው በቀጥታ አይገባም ማለት ነው። ነገር ግን በሁሉም ጉዳይ እጁን አጣጥፎ ይቀመጣል ማለት ደግሞ አይደለም።
መንግሥት ለዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምን ምን እየተደረገ እንዳለ እና ያሉት ሁኔታዎች ምን ይመስላሉ? የሚለውን እንዲታይለት የመጠየቅ የማስታወስ መብት አለው። እናም ይገባልም ይጠይቃልም ሲባል እንዴት? የሚለውን “አይ አይችልም” ሲባልም የት እና ምን ቦታ የሚለውን ለይቶ ማየት ከሁኔታዎች ጋር ማስተሳሰር ያስፈልጋል። የአካሄድ ቅደም ተከተሎች መዛባት ውስጥ መግባትም ራሱን የቻለ ችግር እንዳይሆን ግን ከስሜታዊነት መራቅ የግድ ነው!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2016 ዓ.ም