በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ቻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ ኢትዮጵያን የወከሉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ኢትዮጵያ ቡና የወንዶች እግር ኳስ ክለቦች በሜዳቸው ወሳኝ የመልስ ጨዋታቸውን ዛሬና ነገ ያደርጋሉ፡፡ ክለቦቹ በመጀመሪያ ዙር ጨዋታቸው ከሜዳቸው ውጪ ነጥብ አስጠብቀው የተመለሱ ሲሆን፤ ይህንን እድል ተጠቅመው ወደ ቀጣዩ ዙር እንደሚያልፉም ይጠበቃል፡፡
በውድድር ዓመቱ በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድሮች የመጀመሪያ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ባለፈው ሳምንት ቅዳሜና እሁድ ሲካሄዱ፤ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ኢትዮጵያ ቡና የመልሱን ጨዋታ በሜዳና ደጋፊያቸው ፊት የሚያደርጉ ይሆናል፡፡ በዚህም መሰረት በቻምፒዮንስ ሊጉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዩጋንዳው ኤስሲ ቪላን ዛሬ 9፡ 00 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታድየም ይገጥማል። የመጀመሪያው የሁለቱ ክለቦች ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ በካምፓላ ኔልሰን ማንዴላ ስታድየም ተከናውኖ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2 ለ 1 በሆነ ጠባብ ውጤት ማሸነፉ አይዘነጋም። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን ወክሎ በመድረኩ የሚሳተፍ ሲሆን፤ ውጤቱን አስጠብቆ በመውጣት ቀጣዩን ዙር ለመቀላቀል ዛሬ በሜዳው ጠንካራ ፉክክር ያደርጋል፡፡
የዩጋንዳው ክለብ የሀገሩን ሊግ ለ17 ጊዜያት ማንሳት ሲችል፤ ንግድ ባንክ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማሳካት ችሏል፡፡ ኤስሲ ቪላን ሶስት የሴካፋ ክለብ ዋንጫን በማንሳት የቻለ ሲሆን፤ በአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮና 6 ጊዜ የመሳተፍ ታሪክ አለው፡ ፡ እአአ በ1991 የፍጻሜ ተፋላሚ የሆነበት ውጤቱም ተጠቃሽ ነው፡፡ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የክለቦች ዋንጫ አንድ ጊዜ ተሳትፎ በመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ከውድድር ውጪ የሆነበት ታክም አለው፡፡ በቻምፒዮንስ ሊግ መድረክ ደግሞ 7 ጊዜ ተሳትፎ ያስመዘገበው ትልቅ ውጤት ከሁለተኛ ዙር የማጣሪያ የዘለለ አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ የመድረኩን የመጀመሪያ ተሳትፎ የሚያደርግና ልምድ የሌለው ክለብ ቢሆንም አምና በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያሳየው ድንቅ አቋም ዛሬ የመልሱን ጨዋታ አሸንፎ ወይም ውጤቱን አስጠብቆ ወደ ቀጣዩ ዙር ይቀላቀላል ተብሎ እንዲገመት አድርጓል፡፡ በቻምፒዮንስ ሊጉ በቅድመ ማጣሪያ 54 ክለቦች ተሳትፈው 16ቱ ውስጥ በመግባት የምድብ ማጣሪያ ጨዋታቸውን በተለያዩ የአህጉሪቱ ክፍሎች የሚያካሂዱ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዛሬውን ጨዋታ በድምር ውጤት አሸንፎ የሚያልፍ ከሆነም በሁለተኛው ዙር፣ ከታንዛኒያው ያንግ አፍሪካ እና ከቡሩንዲው ቪታሎ ክለብ አሸናፊ ጋር ይጫወታል፡፡
በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያን ክለቦች በተሳትፎና የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ቀዳሚው ክለብ ነው። ፈረሰኞቹ 9 ጊዜ የመድረኩን ተሳትፎ በማድረግ በአብዛኛው ከቅድመ ማጣሪያና ከመጀመሪያ ዙሮች ቢሰናበቱም አንድ ጊዜ የምድብ ማጣሪያን በመቀላቀል ታሪክ አስመዝግበዋል፡፡
በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን የወከለው ኢትዮጵያ ቡና የመልስ ጨዋታውን ነገ በተመሳሳይ ሰዓትና ስታድየም የኬንያ ፖሊስን ያስተናግዳል፡፡ ባለፈው ሳምንት በናይሮቢ የተካሄደው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ያለምን ግብ መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ከሜዳው ውጪ ጎል ሳያስተናግድ መመለሱ ዛሬ በሜዳውና ደጋፊው ፊት በሚያደርገው ጨዋታ ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ የተሻለ እድልን ይፈጥሮለታል፡፡ የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊው ክለብ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ብዙ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች ማጣቱ ቢታወቅም በወጣት ተጫዋቾቹ የቅድመ ማጣሪያውን ዙር ይሻገራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ ቡና አንድ ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ያነሳ ሲሆን፤ በአፍሪካ መድረክም ተሳትፎ በማድረግ ከንግድ ባንክ የተሻለ ልምድ አለው፡፡ ክለቡ በአፍሪካ መድረክ በአጠቃላይ 7 ጊዜ ተሳታፊ መሆን ሲችል የዘንድሮው ለ8ኛ ጊዜ ነው፡፡ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ እአአ በ1998 እና 2012 ተካፍሎ ከቅድመ ማጣሪያው ማለፍ ሳይችል ቀርቷል። የካፍ ክለቦች ዋንጫ ላይም ለሶስት ጊዜያት ተሳትፎ በጊዜ የተሰናበተበት ታሪኩ ይታወሳል፡፡ አሁን በተካፈለበት የክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ሁለት የተሳትፎ ታሪክ ቢኖረውም በተመሳሳይ በመጀመሪያ ዙር ከውድድሩ ሊወጣ ችሏል። ቡናማዎቹ ከዛሬ ተጋጣሚያቸው አንጻር መድረኩ የተሻለ የተሳትፎ ልምድ ያላቸው በመሆኑ ከናይሮቢውን የአቻ ውጤት የተሻለ በሜዳቸው አስመዝግበው ቀጣዩን ዙር ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በኮንፌዴሬሽን ዋንጫው ቅድመ ማጣሪያ 40 ክለቦች ውድድራቸውን እያደረጉ ሲሆን 20 ቡድኖች ሁለተኛውን ዙር በመቀላቀል፣ የተሻለ ደረጃ ካላቸው 12 ቡድኖች የእርስ በርስ ግጥሚያ በማድረግ በ16 ቡድኖች መካከል የሚካሄደውን የምድብ ማጣሪያ ያደርጋሉ፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም