እንኳን ደስ አለን!

ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር ከችግኝ መትከል ጋር የተያያዘ የረጅም ዘመን ታሪክ ባለቤት ያላቸው ሕዝቦች ናቸው ። ሀገራቱን በየዘመኑ ያስተዳደሩ ነገሥታትም ቢሆኑ ከችግኝ ተከላ ጋር የተያያዘ የራሳቸውን ዐሻራ አሳርፈው ያለፉ ናቸው፤ ይህም ሆኖ ግን የችግኝ ተከላው ዘላቂነት ያለው ባለመሆኑና ከሚቆረጠውም ጋር ባለመጣጣሙም ሀገሪቱ ከፍተኛ ለሆነ የደን መራቆት ተዳርጋለች። ይህም ሀገሪቱን ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ተጋላጭ አድርጓታል።

ችግሩ በተለይም ሀገሪቱን በከፋ መልኩ ለድርቅ አደጋ ተጋላጭ አድርጓታል ፤በየአሥር ዓመቱ እና ከዚያም ባነሱ ዓመታት በሀገሪቱ በሚከሰቱ የድርቅ አደጋዎች ብዛት ያላቸው ዜጎች ለከፋ የረሀብ አደጋ ተጋላጭ ሆነዋል ፤ችግሩ ከዚህም ባለፈ በሀገሪቱ በረሀማ አካባቢዎችን በማስፋት የአየር ንብረት ተጋላጭነቱን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” አድርጎታል።

ችግሩን ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ ለዘለቄታው ለመሻገር የመጀመሪያው ዙር የመጀመሪያው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር በለውጡ ማግስት በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ተደርጓል። በወቅቱ አንድ ሰው 40 ችግኞችን እንዲተክል ተሰልቶ በድምሩ አራት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ተግባራዊ ሆኗል። በወቅቱ በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ 354 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከልም ድንቅ ድል የተመዘገበበትን ታሪካዊ አጋጣሚ መፍጠር ችለናል፡፡

ሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለምን እየፈተነ ባለበት በ2012 ዓ.ም ተግባራዊ ሆኗል። “ርቀታችንን ጠብቀን፣ በግለሰብና በቤተሰብ ደረጃ፣ ከንክኪና ትፍፍግ ርቀን አረንጓዴ ዐሻራ እናሳርፍ፤ ራሳችንን ከኮሮና ምድራችንን ከአየር መዛባት እንታደግ” በሚል መሪ ቃል ጥንቃቄን እና ችግኝ ተከላን ባቀናጀ ርብርብ ተካሂዷል፡፡ ከቀደመው ዓመት በአንድ ቢሊዮን ብልጫ ያለው ችግኝ በመትከል ለችግኝ ተከላ የነበረን ቁርጠኝነት በጊዜያዊ ችግር እንደማይደናቀፍ ለዓለም አሳይተናል ፡፡

በ2013 ዓ.ም ሦስተኛው ዙር አረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር «ኢትዮጵያን እናልብሳት» በሚል መሪ ሃሳብ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥን ታሳቢ ባደረገ መንገድ ፣ ከስድስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን በላይ የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን ችግኞች ተክለናል፡፡ ሦስተኛው አረንጓዴ ዐሻራ ለጎረቤት ሀገራት ችግኞችን በመስጠት ኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ አርዓያ እንድትሆን አስችሏል፡፡

በዚህ ልማት ከዓመት ዓመት ዕድገት እየታየ በሦስተኛው ዙር ስድስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከዕቅድ በላይ ማከናወን ተችሏል፡፡ አራተኛው ዙር ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም «እተክላለሁ፤ እመርጣለሁ» በሚል ሃሳብ ሚሊዮኖች የአረንጓዴም የዴሞክራሲም ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡ በአጠቃላይ በመጀመሪያው ምዕራፍ የችግኝ ተከላ 25 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ዓለም አቀፍ ትኩረትን የሳበ ስኬት ማስመዝገብ ችለናል፡፡

የሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ሃሳብ እንደ ሀገር በ2015 ዓ.ም ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል አቅደን ከዕቅዱ በላይ ማሳካት ችለናል፡፡ በዓመቱም በአንድ ጀንበር ለመትከል ከታቀደው 500 ሚሊዮን ችግኞች በላቀ 566 ሚሊዮን 971 ሺህ 600 ችግኞችን በመትከል የተጨማሪ ዓለም አቀፍ ሪከርድ ባለቤት መሆን ችለን ነበር፡፡

በ2016 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ መትከል ችለናል፡፡ በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ ከተተከሉት ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞች 56 በመቶ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው 44 በመቶ የደንና የውበት ችግኞች ናቸው፡፡

ቀደም ባሉት የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብሮች በአንድ ጀንበር በተከታታይ የዓለም ሪከርዶችን መስበር ችለናል፡፡ ዘንድሮም የቀደመውን የራሳችንን ክብረወሰን በመስበር፣ በትናትናው ዕለት 29 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በአንድ ጀንበር 615 ነጥብ 7 ሚሊዮን ችግኞችን ተክለዋል፤ በዚህም ችግኝ መትከል የሕዝባችን ሆነ የመጪው ትውልድ ባህል ማድረግ ያስቻለ የታሪክ ባለቤት መሆን ችለናል።

መላው ሕዝባችን የችግኝ መትከልን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ በተጨባጭ ተረድቶ በነቂስ በመውጣት በትናንትናው ዕለት ለተሠራው ተጨማሪ አዲስ ታሪክ እንኳን ደስ ያለን እያልን፤ ይህ ተሞክሯችን በይቻላል መንፈስ በኅብረት መንቀሳቀስ ከቻልን ልናሳካው የማንችለው ነገር እንደማይኖር ያሳየ፣ ወደሌሎች የማንቃርምበት ዓለምን ያስደመመ ተሞክሯችን ነው!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

Recommended For You