አርባ ሚሊዮን ዶላር ሊያወጣ ይችላል የተባለ እስካሁን በዓለም ላይ ከተገኙ ግዙፍ የአልማዝ ማዕድናት መካከል አንዱ የሆነው የአልማዝ ማዕድን ቦትስዋና ውስጥ ተገኘ።
ይህ 2492 ካራት ስቶን (498 ግራም) የሚመዝነው አልማዝ በግዝፈቱ በዓለማችን እስካሁን ከተገኙት ሁለተኛው ነው። ማዕድኑን ያገኘው የካናዳው ሉካራ ዳይመንድ የተሰኘው ማዕድን አውጪ ድርጅት ነው።
በአውሮፓውያኑ 1905 ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተገኘው 3106 ካራት ኩሊያን አልማዝ የዓለማችን ግዙፉ አልማዝ ሲሆን፤ ይህ አልማዝ ዘጠኝ ቦታ ተቆራርጦ በብሪታኒያ የንጉሣዊ ዘውድ ላይ ይገኛል።
አዲሱ አልማዝ የተገኘው ከቦትስዋና መዲና ጋቦሮን 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ካሮዌ በምትባለው ሥፍራ ካለ የማዕድን ማውጫ ነው።
የቦትስዋና መንግሥት አልማዙ በሀገሪቱ የተገኘ እጅግ ግዙፉ አልማዝ ነው ብሏል።
ከዚህ ቀደም በ2019 በተመሳሳይ ስፍራ 1758 ካራት የሚመዝን አልማዝ መገኘቱ የሚታወስ ነው።
ቦትስዋና ከዓለማችን አበይት የአልማዝ አምራቾች አንዷ ስትሆን ከዓለም አቀፍ የአልማዝ ምርት 20 በመቶ የሚሆነውን ትሸፍናለች።
ሉካራ የተሰኘው የካናዳ ኩባንያ ባወጣው መግለጫ የከበረው ድንጋይ “እስከዛሬ ከመሬት ውስጥ ከተገኙ ትላልቅ አልማዞች አንዱ ነው” ብሏል።
የሉካራ ኃላፊ ዊሊያም ላምብ “ይህ አስደናቂ 2492 ካራት የሚመዝን አልማዝ በማግኘታችን እጅግ በጣም ደስተኛ ነን” ብለዋል።
ኃላፊው አክለውም አልማዙ የተገኘው በኩባንያው ዘመናዊ የአልማዝ መፈለጊያ መሣሪያ አማካይነት መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ የማዕድን መፈለጊያ መሣሪያ ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ ጥቅም እየዋለ ሲሆን፣ እጅግ የከበሩ የሚባሉ አልማዞችን ለመፈለግ እና ሳይሰባበሩ ለማውጣት የሚያገለግል ነው።
ኩባንያው የአልማዙ ጥራት እንዴት ያለ ነው? አሊያም ዋጋው ምን ያክል ሊሆን ይችላል? ስለሚለው ጉዳይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
ነገር ግን የዩናይትድ ኪንግደሙ ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ ለኩካራ የውስጥ አዋቂዎች ከሆኑ ምንጮች አገኘሁት ባለው መረጃ መሠረት የአልማዙ ዋጋ 40 ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ዘግቧል።
በ2019 የተገኘው 1758 ካራት የሚመዝነውን አልማዝ ሉዊ ቪቶን የተሰኘው የፈረንሳይ የፋሽን ኩባንያ ይፋ ባልሆነ ዋጋ እንደገዛው ይታወሳል።
በዚሁ ተመሳሳይ ሥፍራ በ2016፤ 1109 ካራት የሚመዝን አልማዝ ተገኝቶ ግራፍ ዳይመንድስ የተባለው የለንደን ኩባንያ በ53 ሚሊዮን ዶላር ገዝቶታል።
በቦትስዋናዋ ካሮዌ የተገኘው የዓለማችን ሁለተኛው ግዙፉ አልማዝ ሙሉ በሙሉ የካናዳው ሉካራ ማዕድን አውጪ ድርጅት ንብረት ነው።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ የቦትስዋና መንግሥት አዲስ ያረቀቀው አዋጅ የማዕንድ አውጪ ኩባንያዎች ፈቃድ ከሰተጣቸው በኋላ መንግሥት የአክሲዮን ባለድርሻ እንዲሆን አሊያም ደግሞ የሚያገኙትን ማዕድን 24 በመቶ ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ የሚጠይቅ ነው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም