ኢትዮጵያ ከፍ ያለ የደን ሽፋን አላቸው ከሚባሉ ሀገራት አንዷ ነበረች ይባላል። ይሄ ታሪክ አለፍ ሲልም ተረክ ነው። ምክንያቱም ይሄ ብሂል በተግባር የሚገለጥ የዛሬ ማንነቷን አመላካች አይደለምና። እናም ታሪክ የሚተረክ ብቻ ሳይሆን የሚኖር እውነት መሆን ስላለበት፤ ኢትዮጵያውያን የትናንት ታሪካቸውን ከመተረክ ያለፈ ዛሬን ለመኖር የሚያስችላቸውን ሥራ ጀምረዋል።
በዚህ ረገድ በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት ሲከናወን በቆየው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ተግባራት ወደ ሦስት በመቶ አሽቆልቁሎ የነበረውን የደን ሽፋን ወደ 23 በመቶ ማድረስ ተችሏል። ይሄ ታሪክ አይደለም፤ የሚገለጥ የሚጨበጥ እውነት እንጂ። ይህ እንዲሆን በየዓመቱ በአማካይ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ብርድና ቁር፣ ብሎም ዝናብና ጭቃ ሳይበግራቸው ከ32 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከላቸው ነው።
ዘንድሮም ይሄው ተግባር ቀጥሎ፣ ለስድስት ተከታታይ ዓመታት በቢሊዮኖች ችግኞችን እየተከሉ የእቅድ ግብን፤ በአንድ ጀንበር በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ክብረ ወሰንን እያሻሻሉ የዘለቁበትን እውነት ከታሪክነት ወደ ተጨባጭ እውነትነት ለመግለጥ ከጫፍ ደርሰዋል።
በዚህ በስድስተኛው ዙር መርሃ ግብር በትንሹ ከሰባት ነጥብ ከስድስት ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ከተቀመጠው ግብ በላይ ማሳካት ብቻ ሳይሆን፤ በስድስት ዓመታት ውስጥ የተተከሉ ችግኞችን 40 ቢሊዮን የማድረስ ግብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቀመጠ አቅጣጫም፣ ግብም ሆኗል።
በሌላ በኩል፣ በየዓመቱ አዳዲስ ክብረ ወሰኖች እየተመዘገቡ የተጓዘበትን የአንድ ጀንበር በመቶ ሚሊዮኖች ችግኝ የመትከል ግብ፣ በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ከፍ ያለ የማድረግ አቅምን ለዓለም ሕዝብ ለመግለጥ ከፍ ያለ ሥራ ሲከናወን የቆየበት ነው። በዚህ ረገድ ሁለት ነገሮች አሉ። አንዱ ሀገራዊ አቅምን መግለጫ የሆነው የ600 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀንበር ተክሎ የመግለጥ ነው።
ሌላኛው ግን በጂኦ ሪፈርንሻል መረጃ ተደግፎ እና በሳተላይት መረጃ ታግዞ ለዓለም የክብረወሰን መዝጋቢ አካላት ብቻ ታሳቢ ተደርጎ የሚከናወነው እና የ600 ሚሊዮኑ አንድ አካል የሆነው የ150 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ነው። ይሄ ከኢትዮጵያውያን ከአቅም በታች የሆነ ተግባር መሆኑ እሙን ነው። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያውያን የማድረግ አቅም በልኩ ያልገባቸው አካላት ዛሬም ለሥራቸው በሚገባቸው ልክ እውቅናን ከመስጠት አኳያ ላለባቸው ብዥታ መልስ ለመስጠት ተብሎ የሚከናወን ተግባር ስለመሆኑ መገንዘቡ ተገቢ ነው።
የኢትዮጵያውያን ልክ በዓመት ስምንት ቢሊዮን ችግኞችን፤ በአንድ ጀንበርም ከ600 ሚሊዮን የላቁ ችግኞችን መትከል ነው። ይሄ ደግሞ በታሪክ ትርክት አልያም በምኞት የሚሆን አይደለም። ይልቁንም በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት፣ የተባበረ ክንድና ልቆ የመገለጥ ልዕልና ውስጥ የሚወለድ እውነት ነው።
ለዚህም ነው የዛሬዋ ዕለት ለኢትዮጵያውያን የዚህ ታሪክ መጻፊያ ትክክለኛዋም፤ ልዩዋም ዕለት የምትሆነው። ምክንያቱም፣ ኢትዮጵያውያን ዛሬ በአንድ በኩል በክረምቱ ወራት ለመትከል ያቀዱትን የሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ከዕቅድ በላይ በማሳካት በድል የሚደመድሙበት እንደሚሆን ስለሚታመን ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ፤ አንድም ዓለም ኢትዮጵያውያንን በድንቃድንቅ መዝገቡ እንዲያሰፍራቸው የሚገደድበትን የ150 ሚሊዮን ችግኝ የአንድ ጀንበር ተግባር የሚፈጽሙበት። በሌላ በኩል፣ የአምናውን በአንድ ጀንበር ከ566 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተክለው የተገኙበትን ክብረ ወሰን የሚያሻሽሉበትን ከ600 ሚሊዮን በላይ የላቁ ችግኞችን የሚተክሉበት በመሆኑ ነው።
ለዚህ ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተዘጋጅቷል፤ የሚተከሉ ችግኞች በመጠንም በዓይነትም ተለይተው ቀኑን በመጠባበቅ ላይ ቆይተዋል። ችግኞችን መትከያ የሚሆኑ ስፍራዎች ተለይተውና ጉድጓዶችም ተቆፍረው ዛሬን በጉጉት ሲጠብቁ ከርመዋል። ሁሉም ኢትዮጵያውያን፣ 40 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል እቅድ ግብ አካል፤ የ150 ሚሊዮን የድንቃድንቅ መዝገብን ገጽ ማስያዣ እንዲሁም የ600 ሚሊዮን የሀገራዊ ክብረወሰን ማሻሻያ አቅም ለመሆኑም ዛሬን ናፍቀዋል። ይሄንን እውን ለማድረግም በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ሰፊ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።
እናም ዛሬ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽት 12 ሰዓት የሚከናወነው ተግባር ለኢትዮጵያውያን ልዩ ትርጉም አለው። ምክንያቱም ይሄ ዕለት ኢትዮጵያውያን መተባበር እና ተባብሮ፣ ታሪክ መሥራት እንደሚችሉ የሚገልጡበትን ሌላ ዕድል ይዞ የመጣ ነውና። ኢትዮጵያውያን በታሪክ ከሚነገርላቸውም በላይ፣ ከሚተረክላቸውም በላቀ ዛሬን ታሪክ ሠርተው ለማለፍ የሚተጉ፤ ተባብረው ለመፈጸምና ከነገሮች ሁሉ ልቀው ለመውጣት የሚታትሩ፤ ለህልውናቸው፣ ለክብርና አብሮነታቸው ጊዜና ሁኔታ የማይገድባቸው መሆኑ አንድ ማሳያ ነው። ለዚህም ነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ ውጥንም፣ የአንድ ጀንበር ክብረወሰን ጉዞውም እውን እንዲሆን እኛ ኢትዮጵያውያን ዛሬን ልንጠቀም፤ በጋራ ተሰልፈን የተለመደ ተአምራዊ ተግባራችንን ልንፈጽም ይገባናል፡፡
አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም