የሀገራቱ ሕዝቦች የሚሻላቸውን እና የሚበጃቸውን ራሳቸው ያውቃሉ!

በድህነት እና በኋላ ቀርነት ፤ በጦርነት እና በግጭት ውስጥ ዓመታትን እያስቆጠረ ላለው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ችግር ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ ፤ የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ከሆኑት የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች በላይ ባለ ጉዳይ ሊሆን የሚችል ማንም የለም። ባለጉዳይ ሆኖ ለመቅረብ የሚደረግ ጥረትም በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት የሚኖረው አይሆንም።

የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች በታሪክ ፣ በባህል ፣ በሃይማኖት እና በቋንቋ ሰፊ መስተጋብር ያላቸው ናቸው፤ ይህ ዘመናት ያስቆጠረው መስተጋብራቸው በየወቅቱ ከውስጥም ከውጪም በሚፈጠሩ ፈተናዎች ብዙ መንገጫገጮች ቢያጋጥመውም ፤ ዛሬም በሕዝቦቹ መካከል ያለው የወንድማማችነት መንፈስ የተጠበቀ ነው።

የሀገራቱ ሕዝቦች የመልማት ጥያቄ ፤ ድህነት እና ኋላ ቀርነትን አሸንፎ የመውጣት የዘመናት መሻት፤ በአካባቢው ለልማት የሚሆን ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት የማስፈን ጥረት ፤ ይህንን የሀገራቱን ሕዝቦች የረጅም ዘመን የግንኙነት መስተጋብር በአግባቡ ከማወቅ እና ከመረዳት ፤ ለዚህ የሚሆን ዝግጁነት ከመፍጠር ሊነሳ ይገባል።

በተለይም የሀገራቱ ሕዝቦች ድህነት እና ኋላ ቀርነትን አሸንፈው ፤ ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ ስትራቴጂክ ግንኙነት ላይ የተመሠረተ ፤ ያላቸውን አቅም በአግባቡ ተረድተው፤ በሁለንተናዊ መልኩ አቀናጅተው መንቀሳቀስ ሲችሉ እንደሆነ ይታመናል።

ላለፉት ስድስት አስርቶች በአካባቢው የሚስተዋለው የሰላም እጦት በአንድም ይሁን በሌላ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ፍላጎት አይደለም ፤ እስካሁን በተጨባጭ እየታየ እንዳለውም የግጭቱ ተጠቃሚ የሆነ ሀገር እና ሕዝብ የለም። ግጭቶቹ የአካባቢውን ሀገራት ሕዝቦች ለከፋ ሠብዓዊ ቀውስ ፣ ጥፋት እና የሀብት ውድነት ዳርገዋል።

አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጡ ማግስት ጀምሮ በአህጉሪቱ የተደመጡ ፤ የተለያዩ የጥፋት ትርክቶች፤ በሀገራት ጣልቃ ገብነት እና ዓለም አቀፍ ሴራዎች አቅም ገዝተው አፍሪካውያንን ፤ ከትግል ወቅት ተስፋ እና ምኞታቸው የነጠላቸው የግጭት አዙሪት ውስጥ እንዲወድቁ ሆነዋል ፤ በዚህም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት እና ሕዝቦች ተፈትነዋል።

የአህጉሪቱ ሕዝቦች ከፓን አፍሪካኒዝም /አፍሪካዊ ወንድማማችነት ወጥተው ፤ ልዩነቶችን በሚያቀነቅኑ ግለሰቦች እና ቡድኖች ማቆሚያ ወዳጣ ግጭት ገብተዋል። ከግጭቶቹ ለመውጣት የሚያደርጓቸው ጥረቶችም፤ በሌሎች ፍላጎቶች እየተጠለፉ ፤ ለራሳቸው ችግር የመፍትሄ አካል መሆን የሚችሉበትን አቅም አጥተው ቆይተዋል።

ይህ ሁኔታ ዛሬም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ዘላቂ ሰላም በማምጣት ፤ አካባቢውን ከግጭት ቀጣናነት ወደ ልማት ኮሪደርነት ለመለወጥ የሚደረገውን የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች መነሳሳት በዋናነት እየተፈታተነው ይገኛል። የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች አቅማቸውን አቀናጅተው ለመልማት ለሚያደርጉት ጥረት ተግዳሮት ሆኗል።

የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ብሩህ የሆነው እጣ ፈንታቸው የሚወሰነው ፤ በተናጠል በሚያደርጉት የመልማት ጥረት ወይም ፤ በሴራ ላይ በተመሠረተው አሮጌ የዜሮ ብዜት ፖለቲካ አይደለም ። ይህ በቀደሙት ጊዜያት ተሞክሮ አትራፊ አለመሆኑ በተጨባጭ ታይቷል። አካባቢውን የግጭት እና ያለመረጋጋት ቀጣና ከማድረግ ያለፈ ያመጣው ነገር የለም።

ዓለም ወደ አንድ መንደርነት እየተለወጠች ባለችበት በዚህ ዘመን ፤ የድህነት እና የኋላቀርነትን ቀንበር ተሸክሞ፤ በዚህ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ውስጥ በተናጠል / በራስ ለመቆም መሞከር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው። በተለይም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ካሉበት ተጨባጭ እውነታ አኳያ ለበለጠ አደጋ እራሳቸውን የሚያጋልጥ ነው።

የነዚህ ሀገራት ብሩህ ነገዎች የሚወሰኑት ሀገራት ያላቸውን አቅም አቀናጅተው በጋራ መንቀሳቀስ ሲችሉ ነው። ይህ ከቀደሙት የአህጉሪቱ የነጻነት አባቶች ከወረስነው የፓን አፍሪካኒዝም /አፍሪካዊ ወንድማማችነት የሚቀዳ ፤ ዘላቂ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሰፍን ፤ የጋራ ዕጣ ፈንታን ከመጋራት የሚመነጭ ነው።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ እና በሶማሌ ላንድ ሆነ በአካባቢው ሀገራት መካከል የሚታየው ፤ አቅሞችን ለጋራ ተጠቃሚነት አቀናጅቶ የመንቀሳቀስ ጥረት ፤ የአካባቢው ሕዝቦች የመልማትን ጥያቄ ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ መመለስ ፤ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ማስፈን የሚያስችል ነው።

ይህን የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦችን ፍላጎት እና ከባለቤቶቹ በላይ ይመለከተኛል በሚል የተገለጠ ሴራ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች እና ሀገራት ከዚህ ካልተገባ ተግባራቸው ሊቆጠቡ ይገባል ። የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ለነሱ ጊዜ ያለፈበት አጀንዳ ዋጋ መክፈል የሚገደዱበት መጋረድ ውስጥ አይደሉም። የሚሻላቸውን እና የሚበጃቸውን ከማንም በላይ እራሳቸው ያውቃሉ!

አዲስ ዘመን ሐሙስ ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You