ወይዘሮ ሃና አርአያሥላሴ-የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር
ሀገሮች ለኢንቨስትመንታቸው በእጅጉ ከሚያስፈ ልጓቸው መሠረተ ልማቶች መካከል የኢነርጂው መሠረተ ልማት አንዱ ነው። ይህን ታሳቢ በማድረግም በኢነርጂ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ላይ በስፋት እንደሚሰሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የኢነርጂ መሠረተ ልማት ታዳሽና ታዳሽ ያልሆነ በሚል በሁለት ይከፈላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ታዳሽ ያልሆነው የኢነርጂ መሠረተ ልማት በአየር ንብረት ላይ እያስከተለ በመጣው አሉታዊ ተጽዕኖ ሳቢያ የኢነርጂ መሠረተ ልማት እንደ ነዳጅ ያሉትን ከሚጠቀመው መሠረተ ልማት እንደ የውሃ ኃይል የመሳሰሉትን ወደሚጠቀመው ታዳሽ ኃይል መሠረተ ልማት ላይ እየጠየቀ መጥቷል። የኢነርጂ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ዓለምን ከገጠማት የአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የኃይል ልማት ኢንቨስትመንቱ በታዳሽ ኃይል ላይ ትኩረት ማድረግን እየጠየቀ ነው። በነዳጅ የሚመነጨው የኃይል አማራጭ አካባቢን ለብክለት እየዳረገ መሆኑ ኢንቨስትመንቱ ታዳሽ የኃይል ምንጭ ላይ እንዲሆን አድርጎታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ2023 የኢንቨስትመንት ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለውም ፤ የፓሪሱ ስምምነት ከተደረገ እእአ ከ2015 ጀምሮ በታዳሽ ኃይል ላይ የሚደረገው ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት በሶስት እጥፍ እድገት አሳይቷል። ፍላጎቱ ከዚህም በላይ መሆኑንም እየተጠቀመ ነው። ይሁንና ይህ ኢንቨስትመንት በአብዛኛው የተደረገው በበለጸጉት ሀገሮች ነው። በማደግ ላይ በሚገኙት ከ30 በላይ ሀገሮች በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ በሚሰራው ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት በኩል እስከ አሁን አንድም የታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንት አላሳዩም። በእነዚህ ሀገሮች የታዳሽ ኃይል ማስፋፊያዎች፣ ኃይል ማመንጫ ግሪዶች፣ ማስተላለፊያና ማከማቻዎች ላይ ኢንቨስት የማድረግ ከፍተኛ ፍላጎቶች እንዳሉ መረጃው አመላክቷል።
በማደግ ላይ በሚገኙት ሀገሮች የኃይል ልማትን ለማካሄድ የሚያስፈልገው ሀብት ከፍተኛ ነው። ይህን ልማት የሚያስፈልገውን ወጪ ለመቀነስ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ከመንግሥታት እንዲሁም ከፋይናንስ ተቋማት ጋር የሚሰሩበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ሰነዱ አመላክቷል። በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገሮች በራሳቸው አቅም በኃይል ልማት ላይ ለውጥ ለማምጣት እየሰሩ መሆናቸውንም ጠቁሟል፤፤
በተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ልማት ኤጀንሲ ሲኒየር የኢኮኖሚ ባለሙያ ዶክተር ስቴፋኒያ ቦኒላ በኢነርጂ ማስፋፋት በኩል ያለውን ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት አስመልክተው ሲያብራሩ በተለይ በአፍሪካ በአጠቃላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት እየቀነሰ መምጣቱን ጠቅሰው፣ በአንጻሩ በአህጉሪቱ የውስጥ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።
ዘላቂ ታዳሽ ኃይልን ለሁሉም ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ያለው ኢንቨስትመንት ሲታይ የዓለም አቀፍ ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን እንደሚጠቁም ጠቅሰው፣ በዚህ በኩል ታዳጊ ሀገራት ወደ ኋላ እየቀሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። በ2030 ዘላቂ እድገት ለማምጣት በተያዘው ዓለም አቀፍ እቅድ የታዳሽ የኃይል አቅርቦት ዋነኛ አጀንዳ መሆኑን ጠቅሰው፣ የታዳሽ ኃይል በአደጉት ሀገራት በሁለት ነጥብ አምስት በመቶ እንዲሁም በታዳጊ ሀገራት 25 በመቶ ማሳደግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም ከዚህ አኳያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችሉ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እና አሰራሮች ላይ ለውጥ በማድረግ እየሰራ ነው። በተለይ በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲጨምር በማድረግ አሁን ያለውን የኃይል አቅርቦት ወደ 100 በመቶ በማድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከሰሞኑም በኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንት ላይ ያተኮረ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ኢንቨስትመንትን እና ፋይናንስን በታዳሽ ኃይል እንዴት ማስፋፋት እንደሚገባ የሚመክር አውደ ጥናት ተካሂዷል። በአውደ ጥናቱ በኢትዮጵያ መንግሥታዊ ባለድርሻዎች እና በግል ዘርፉ ተዋናዮች መካከል ምክክር ተደርጎበታል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ወይዘሮ ሃና አርአያሥላሴ በተለይ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ በታዳሽ ኃይል ልማቱ የውጭ ባለሀብቶች ተሳትፎ የሚያደርጉበትን ሁኔታ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ ያለውን እድል አመልክተዋል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቅሰው፣ እስከ ዛሬ የኢንቨስትመንት ስበትን ለመጨመር በሚደረገው ጥረት ከውጭ ከሚመጡ ኢንቨስተሮች ጋር በሚደረገው ውይይት በተግዳሮትነት ሲጠቀሱ ከቆዩት መካከል አንዱ የውጭ ምንዛሪ እንደሚመለከት ተናግረዋል።
አሁን ወደ ትግበራ የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ሀገሪቱ እንዲመጡ “በማድረግ በኩል ትልቅ ዜና መሆኑን ጠቅሰዋል። ባለፉት ዓመታት እንደ አዲስ በተከፈቱ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ተጨማሪ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በስፋት ወደ ሀገሪቱ ይመጣል ተብሎ ተስፋ መደረጉንም አመላክተዋል።
ዋና ኮሚሽነሯ ‹‹ አንድ ሀገር የትኛውንም ዓይነት የኢኮኖሚ እቅድ ሲያወጣ የኃይል ዘርፉ ቁልፍ ሚና አለው። ኃይል በሌለበት ስለኢንዱሰትሪያላይዜሽን፣ ስለማምረቻ ዘርፍ እድገት መነጋገር አይቻልም።›› ሲሉ የኃይል ዘርፉን ወሳኝነት አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ታዳሽ ኃይል ለማልማት ያላትን እምቅ አቅም በማልማት ወደ ሥራ ለማስገባት ያካሄደቻቸው ኢንቨስትመንቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ መንግሥት በዘርፉ ከፍተኛ የሚባለውን ኢንቨስትመንት ማድረጉን አስታውቀዋል። “በቀጣይም በኃይል ልማት ዘርፉ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ እየተሰራ ነው” ብለዋል።
የኢትዮጵያን የኃይል ምርት አቅም ለማሳደግ በተደረገው ጥረት አሁን ወደ አምስት ሺህ 400 ጊጋ ዋት አካባቢ ኃይል እየተመረተ መሆኑን ለማወቅ እንደተቻለ ጠቅሰው፣ ይሄም በውሃ ኃይል ማመንጫዎች ልማት ላይ መንግሥት ባደረጋቸው ኢንቨስትመንቶች የመጣ መሆኑን ገልጸዋል። አዲሱ የ10 ዓመት እቅድ ሲወጣ እና የኢትዮጵያ 2030 የኃይል ዘርፍ ራዕይ ሲቀመጥ አንዱ ትልቁ ታሳቢ የተደረገው መንግሥታዊ ኢንቨስትመንቱ እንዳለ ሆኖ የግል ዘርፉ ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር አለበት የሚለው መሆኑንም ተናግረዋል።
እስከ አሁን የተካሄደው የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ሥራ በጣም ጉልህ ለውጥ አምጥቷል ሲሉ ጠቅሰው፣ አሁንም ማስተላለፊያዎች እና ማሰራጫዎች ላይ በርካታ ኢንቨስትመንቶች ያስፈልጋሉ ብለዋል። እስካሁን ለሕዝቡ መድረስ የቻለው የኤሌክትሪክ ኃይል 54 በመቶ ብቻ መሆኑንም ጠቁመው፣ በ2030 ይህን አሀዝ 100 በመቶ ማድረስ የሚል እቅድ መያዙንም አስታውቀዋል።
ዋና ኮሚሽነሯ እንዳስረዱት፤ ይሄንን ለማድረግ የመጀመሪያው ሥራ አሁን ያለውን ኃይል የማመንጨት አቅም በአራት እጥፍ ማሳደግ ያስፈልጋል። የኃይል አቅሙን በአራት እጥፍ ለመጨመር ደግሞ የመንግሥት የዘርፉ ኢንቨስትመንት ብቻውን በቂ አይደለም፤ የግል ዘርፉን ማሳተፍ ይገባል የሚል እምነትም በመንግሥት በኩልም አለ።
ይሄንን እቅድ ለማሳካትም እንደ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እምነት በዋነኛነት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ ላይ እንደሚሰራ አስታውቀው፣ በኃይል ዘርፉ ላይ እስከዛሬ የነበሩ ጥረቶች እንዳሉ ሆነው በቀጣይም ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጠው አመልክተዋል። ምክንያቱም በአጠቃላይ የሀገር እድገትን በተለይ ደግሞ የኢንዱስትሪያላይዜሽን እና የማምረቻ ዘርፉን ሚና ለማሳደግ የግል ዘርፉም ኃይል ልማት ላይ እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል ብለዋል። ይህን መፍጠር ካልተቻለ የተፈለገውን የኃይል አቅርቦት ማሳካት እንደማይቻል ተናግረው፣ በወርክሾፑም በቀጣይ የተሻለ የኃይል ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ ምክክር መደረጉን አስታውቀዋል።
ዋና ኮሚሽነሯ እንዳስታወቁት፤ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በሀገሪቱ እንዲጨምር ከሚደረግባቸው መንገዶች አንደኛው የኢንቨስትመንት ፖሊሲን ማሻሻል ነው። ይህም ሲባል ኢንቨስትመንቱን ለመሳብ ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮችን በየጊዜው በመለየት ፖሊሲዎች እና ሕጎች ተሻሽለው እንዲወጡ ማድረግ ነው።
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን የመቅረጽ ሥራዎች ተሰርተዋል። ሀገራዊ የኢነርጂ ፖሊሲ ማውጣትን ጨምሮ ብዙ ሕጎች ተሻሽለዋል። የግል ዘርፉን ከኢንቨስትመንቱ ይገድቡ የነበሩ ብዙ ነገሮች ተስተካክለዋል። ታዳሽ ኃይልን ጨምሮ በሌሎች ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎች የኢትዮጵያ መንግሥት ማበረታቻዎችን ያደርጋል። የገቢ ግብር እፎይታ፣ ከቀረጥ ነፃ እቃዎች ማስገባት ለዘርፉ የተፈጠሩ አስቻይ ሁኔታዎች ናቸው።
ሁለተኛውም በሀገሪቱ ያሉትን የኢንቨስትመንት እድሎች ማስተዋወቅ ነው። የኢነርጂ ዘርፉ ለታዳሽ ኃይል ልማት ቅድሚያ የሚሰጥ ቢሆንም፣ ዘርፉና ልማቱ በበቂ ሁኔታ አልተዋወቀም። እንደ ሀገር የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦችን ጨምሮ በሶላር፣ በንፋስ፣ በጂኦተርማል እና በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያሉ እድሎች ምንድናቸው በሚሉት ላይ በጣም ማስተዋወቅ ይገባል።
ለዚህም በሀገር ውስጥ በኢነርጂ ዘርፍ ላይ ዋና ዋና ተዋናይ የሚባሉ ተቋማት እንዳሉ ጠቅሰው፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን እንዲሁም በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የግልና የመንግሥት አጋርነት እና ፕሮግራም በሚባሉት አብዛኛዎቹ ኢንቨስትመንቶች እንደሚመጡ ገልጸዋል።
ዋና ኮሚሽነሯ እንደገለፁት፤ አውደ ጥናቱም በተለያዩ ተቋማት በዘርፉ የሚደረጉ ጥረቶችን አንድ ላይ በማሰባሰብ እንደ ሀገር ያለውን የኢነርጂ ሀብት ማስተዋወቅ ላይ የተሻለ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ሁኔታን ይፈጥራል። ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ንግድና ልማት ኤጀንሲ ጋር በመሆን የተካሄደውን ወርክሾፕ ተከትሎ የሶስት ዓመት ፕሮጀክት የተጀመረበት መሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን ለዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች በተሻለ ለማስተዋወቅ የሚያስችል ተግባራዊ የሚሆኑ እቅዶች እንደሚወጡ አመላክተዋል።
ኢነርጂ እንደ ዘርፍ ሲተዋወቅ ቢቆይም፣ ይሄኛው ፕሮጀክት ሲጀመር ግን እንደ ሃሳብ በአንድ በኩል ትልልቅ እድሎች አሉ ሲሉ አመልክተው፣ ተሻሽለው የወጡ ፖሊሲዎች እና ሕጎች እንዳሉም ተናግረዋል። አንድ የውጭ ባለሀብት ኢትዮጵያ ውስጥ የኃይል ፕሮጀክት ለመጀመር ቢያስብ ፋይናንስ ማግኘት በሚያስችለው ደረጃ ተጨባጭ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ቀርፀን ያንን መሸጥ ላይ ለመሰማራት ነው። በመሆኑም እስከዛሬ ኢነርጂ ሴክተሩን ስናስተዋውቅ ጠቅለል ያለ ሀገሪቱ ይሄ እድሎች አሏት በሚል ደረጃ ብቻ ነው። ይሄንንም በሚገባ በማስረዳት በተጨባጭ ምን ዘርፍ ላይ የትኛው የታዳሽ ኃይል ላይ ምን አይነት ፕሮጀክት ማምጣት ይቻላል የሚለውን ለመሥራት የሚያስችል ጥናት የሚሰራበት ፕሮጀክት መሆኑን አመላክተዋል።
ኢንቨስትመንት ኮሚሽኑ የአምራች ዘርፉን ኢንቨስተሮች መሳብ ላይ ያስመዘገበው ስኬት በዘላቂነት መቀጠል እንዲችል የኃይል ዘርፉ ታዳሽ ኃይሎችን ማምረት ላይ ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን ማምጣት እንደሚገባው አመልክተዋል። በዚህ በኩል የእስካሁኑ ትኩረት እንዳለ ሆኖ በተያዘው በጀት ዓመት ተጨባጭ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ዲዛይን በማድረግ የኃይል ዘርፉ ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ኢንቨስትመንቶች ለመሳብ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያን ውሜን ኢን ኢነርጂ አሶሲዬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ሊንዳ ላጵሶ ድሌቦ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ተቋሙ ሴቶች በኢነርጂ ዘርፍ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ እና በሙያቸው ታዳሽ ኃይልን ማስፋፋት ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ላይ ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት ጋር ይሰራል።
ማህበሩ ከተቋቋመ አምስት ዓመት እንደሆነው ምክትል ፕሬዚዳንቷ ጠቅሰው፣ በሀገሪቱ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በከተማም ሆነ ከከተማ ውጭ ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው ብለዋል። ኃይል ወደሌለበት ቦታ ግሪዶችን በማስፋት ኃይል እንዳይቋረጥ ለማድረግም እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፣ ኤሌክትሪሲቲ በማይደርስባቸው ቦታዎች ደግሞ በኦፍግሪድ ሥራዎች እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ዋጋው ተመጣጣኝ በሆነ እና ተደራሽነቱንም ፈጣን ባደረገ መንገድ የኤሌክትሪክ ኃይል የማዳረስ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በመንግሥት በኩል በታዳሽ የኃይል ልማት ላይ የተሰማራውን የግል ዘርፍ ለማገዝ እንዲሁም ወደዚህ ገበያ ለመግባት ያሉ ተግዳሮቶችም የሚፈቱባቸውን መንገዶች የሚያመላክቱ የውይይት መድረኮች እንደሚካሄዱም አመላክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በኃይል ልማት ዘርፉ ከውጭ በሚገቡ አቅርቦቶች ላይ፣ ከቀረጥ ነፃ፣ ፈቃድ ከማግኘት፣ እቃው ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ በኋላም ወደ ማሰራጫ ቦታዎች እንዲደርስ ከማድረግ፣ ከደረሰም በኋላ ብቃት ያላቸው ሠራተኞች በሥራው ላይ ተሳትፈው የገቡትን እቃዎች በመግጠም ተጠቃሚው ጥሩ አገልግሎት እንዲያገኝ ከማድረግ አኳያ ይሰራል።
በዚህም መንግሥት ለፕሮጀክቱ ለረጅም ጊዜ የሚሆኑ ከአቅርቦት ሰንሰለቱ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። ማህበሩ አሁን በተለይ ክልል አካባቢ ባሉ ቦታዎች ላይ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት፣ የተጠቃሚዎችን ችግሮች በጥናት በመለየት፣ የፍላጎት ዳሰሳ ጥናትም በማድረግ መፍትሔ ይዞ ለመሄድ እና መፍትሔውንም ለማሳወቅ የፀጥታ ችግር ተግዳሮት መሆኑን አመላክተዋል። ይህ ችግር ባለፉት አንድ እና ሁለት ዓመታት ሥራዎችን ወደኋላ መጎተቱን ጠቁመዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይ እቃዎችን ከውጭ ማስገባት ላይ ያጋጥም የነበረውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመፍታት እገዛ ሊያደርግ እንደሚችል ጠቅሰዋል። በማክሮ ደረጃ ኢኮኖሚው የተረጋጋ ሲሆን ከውጭ የሚመጣው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመሰማራት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርለት ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ ገበያ የተረጋጋ ነው፣ ክፍት ነው፣ ዝግጁ ነው የሚለውን ለማየት ያስችላቸዋል። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱ ወደ ሀገሪቱ እንዲመጣ እና ታዳሽ ኃይልን ጨምሮ በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ መዋዕለ ነዋዩን ሥራ ላይ እንዲያውል እንደሚያስችላቸው አመላክተዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም