የወጪ ንግዱን አትራፊና ተወዳዳሪ እንደሚያደርግ የታመነበት ማሻሻያ

በቅርቡ ወደ ሙሉ ትግበራ የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ስለመሆኑ መንግሥትም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም አስታውቀዋል። በተለይም በኢኮኖሚ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተንሰራፍቶ ለቆየው የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋትና መዛባት መፍትሔ እንደሚሆን ታምኖበታል። ማሻሻያውን ተከትሎ የወጣው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያም እንዲሁ በተለይ የግሉን ዘርፍ የበለጠ የሚያነቃቃ ስለመሆኑ እምነት ተጥሎበታል።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በርካታ አይነት የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ታገኛለች። ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ዋነኛ ምንጭ ከሆኑት የግብርና ምርቶች መካከልም ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች እና ቅመማቅመሞች ይገኙበታል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይ በወጪ ንግዱ ለተሰማሩ ወይም ለላኪዎች /ኤከስፓርተርስ/ መልካም እድል ይዞ መምጣቱን የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች እና ቅመማቅመም ላኪዎች ማህበር አመራሮች አስታውቀዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለዚህ ዘርፍ ምን ቱሩፋት ይዞ መጥቷል? የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያውስ ከወጪ ንግዱ ዘርፍ ጋር ያለው ተያያዥነት ምን ሊሆን ይችላል? ስንል የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች እና ቅመማቅመም ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኤዳኦ አብዲ፤ ማሻሻያው በተለይ ለወጪ ንግዱ ከፍተኛ ጉልበት እንደሚጨምርለት ገልጸዋል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት እንዳሉት፤ ማሻሻያው በውጭ ንግድ የተሰማራውን የንግዱን ማህበረሰብ በቀጥታ የሚመለከት ቢሆንም፤ የእያንዳንዱን ግለሰብ ሕይወትም ይነካል። በተለይ በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችን በቀጥታ የሚመለከት በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል።

በዋነኛነት የወጪ ንግዱ ከኪሳራ ይወጣል ሲሉ ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ባለፉት አስርት ዓመታትና ከዛም በላይ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ አብዛኛው ላኪ ምርቶቹን የሚሸጠው በኪሳራ እንደነበር አመልክተዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ወደ ውጭ ገበያ ኤክስፖርት የሚደረጉ የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ በዓለም ገበያ እጅግ በጣም ተፈላጊና ተመራጭ ናቸው። ሁሉም ምርቶች በዓለም ላይ ምርጥ ከሚባሉ ምርቶች መካከል የሚጠቀሱ ቢሆንም፤ አጠቃላይ የወጪ ንግዱ በኪሳራ ሲሠራ ነበር።

ላኪው ምርቱን በውድ ዋጋ ገዝቶ ወጪውን በማይሸፍን ዋጋ ሲልክ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በሚያገኘው የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በማምጣት የወጪ ንግድ ኪሳራውን በገቢ ንግድ ይደግፈው እንደነበር ተናግረዋል። ለዚህም ዋናው ምክንያት ሀገሪቷ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያለባት በመሆኑ ነው ብለዋል።

አሁን መንግሥት ያደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለዘርፉ ትልቅ ዕድል ይዞ መጥቷል። በተለይም የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲመራ መደረጉ ማንኛውም ነጋዴ የውጭ ምንዛሬውን ከባንክና ከተለያየ ቦታ ማግኘት የሚቻልበት ዕድል ይፈጠራል። ይህም በዋነኛነት ላኪውን ከኪሳራ በማውጣት ሥራውን የሚፈልጉት ብቻ መርጠውና ፈልገው እንዲሠሩት ዕድል ይሰጣል። በዚህም ላኪውና አስመጪው ተለይቶ እንዲመራ በማድረግ ዘርፉን ከፍ ያደርጋል።

በቀደመው ልምድ መሠረት ማንኛውም አስመጪ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ሲል ብቻ የተለያዩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የሚያገኘውን የውጭ ምንዛሬ ተጠቅሞ በተመሳሳይ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባል።

‹‹ይህ በሚሆንበት ጊዜ የጥራት ጥያቄ ይነሳል›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የምርት ጥራት ካልተጠበቀ ደግሞ ተወዳዳሪ መሆን እንደማይቻል አስታውቀዋል። ተወዳዳሪ መሆን ካልተቻለ ደግሞ ምርቶቹን በገበያ ዋጋ ተወዳድሮ መሸጥ ያስቸግራል። አስመጪው በኤክስፖርት የከሰረውን ወደ ሀገር ውስጥ በሚያስገባቸው ምርቶች በማካካስ የገቢ ንግዱ የወጪ ንግዱን ሲደግፈው በመቆየቱ ኅብረተሰቡ በእጅጉ ሲጎዳ መኖሩን አስረድተዋል።

ሌላው ነጋዴው ሥራውን ፈልጎት ሲሠራ በተለይም ለውጭ ገበያ በሚያቀርባቸው ምርቶች ላይ እሴት ወደ መጨመር ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ አብዛኛው ነጋዴ ለውጭ ምንዛሬ እንጂ ለእሴት ጭመራ ብዙ ቦታ እንደማይሰጥ ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረቱ ጥራጥሬዎች፣ የቅባት እህሎችና ቅመማቅመሞች በሙሉ እሴት ሳይጨመርባቸው በጥሬው ለውጭ ገበያ ሲቀርቡ ቆይተዋል። ይሁንና አሁን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በፈጠረው ዕድል ላኪው የውጭ ምንዛሬውን በቀላሉ ማግኘት ሲችል ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ጥራትን ጨምሮ የማምረትና እሴት የመጨመር ትልቅ አቅም ይፈጠርለታል።

ለአብነትም ኢትዮጵያ የምታመርተውን ሰሊጥ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ታንዛንያ፣ ናይጄሪያ፣ ቡርኪናፋሶና ሌሎችም ያመርቱታል። ስለዚህ ላኪው አሁን ተወዳዳሪ መሆን ይችላል። ከዚህ ቀደም የውጭ ምንዛሪውን ለማግኘት ሲል የቅባት እህሎችን ከሀገር ውስጥ አምራቾች በውድ ዋጋ ገዝቶ በኪሳራ ይሸጥ ነበር። ይሁንና በማሻሻያው አማካኝነት ኪሳራው ስለሚቀርለት በአካባቢው ካሉ ሀገራት ጋር ተወዳድሮ የመሸጥ እድሉ ከፍ ይላል።

ሌላው ሀገሪቷን እየጎዳ ያለው የኮንትሮባንድ ንግድ እንደሆነ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ከጠቅላላው የሀገሪቷ የወጪ/ኤክስፖርት/ ምርት 21 በመቶ ያህሉ በተለያዩ አጋጣሚዎች በኮንትሮባንድ እንደሚወጣ አመልክተዋል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኮንትሮባንድ ንግድን ጭምር በማስቀረት ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል። ለዚህም በባንክና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው የውጭ ምንዛሪ ልዩነት እየጠፋ ሲሄድ የኮንትሮባንድ ንግዱም እየጠፋ እንደሚሄድ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

እንደ አቶ ኤዳኦ ገለጻ፤ ኮንትሮባንድ ሲጠፋና ውድድሩ የተሻለ ሲሆን፤ ወደ ሀገር ውስጥ የሚመጣው የውጭ ምንዛሬ ከፍ እያለ ይመጣል። በአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የምርት ጥራት መጨመር፣ ምርታማ የመሆን፣ የወጪ ንግዱ ራሱን ችሎ መሄድ፣ የወጪና ገቢ ንግድ መስመሩ ተለያይቶ መጓዝ ለኢኮኖሚው ዕድገት ተስፋ የተጣለባቸው መልካም ዕድሎች ናቸው።

ማህበረሰቡ ተጠራጣሪና አዲስ ነገር ለመቀበል ዝግጁ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚሰሙ ስጋቶች እንዳሉም ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው፤ አሉ የተባሉ ስጋቶች በጊዜ ሂደት የሚፈቱ መሆናቸውንም ተናግረዋል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በርካታ ትሩፋቶችን ይዞ የመጣና በ30 ዓመት ታሪክ ውስጥ ታይቶ ያልታወቀ ገበያ መር የሆነ ተገቢነት ያለው እርምጃ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይም የውጭ ምንዛሪ ተመን ገበያ መር መሆኑ ኤክስፖርቱን ከማሳደግ ባለፈ ነጋዴው ተወዳዳሪ እንዲሆን ይጋብዛል ሲሉም ፕሬዚዳንቱ ተናግረው፤ ለእዚህ ግን ምርትና ምርታማነትን ከጥራት ጋር በማሳደግ ተወዳዳሪ መሆን የግድ እንደሆነ ነው ያስረዱት።

እሳቸው እንዳሉት፤ ነጋዴው ተወዳዳሪ መሆን ካልቻለ ሀገሪቷ የሌሎች ሀገራት ሸቀጥ ማራገፊያ ትሆናለች። ስለዚህ በጥራት ማምረትና ተወዳዳሪ መሆን ይጠበቃል። ያኔ ዋጋ ተቀባይ ሳይሆን ዋጋ ሰጪ መሆን ይቻላል። ለዚህም ማህበሩ ከወዲሁ የራሱን ድርሻ እየተወጣ ሲሆን፤ በተለይም ለላኪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ በመፍጠር የተሻለ ሚና መጫወት እንዲችሉ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።

የጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመም ላኪዎች ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ዘመዴ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች እና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር የወጪ ንግዱ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ እንደመሆኑ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በቀጥታ ይመለከተዋል ብለዋል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከዚህ ቀደም በዘርፉ ሲሰራበት የነበረውን አይነት ሥራና አካሄድ ሙሉ ለሙሉ የሚቀይርና ብዙ ተስፋ የተጣለበት ስለመሆኑም አብራርተዋል።

የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ምርቶች በተለይም የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ወደ ውጭ ገበያ ተልከው ሲሸጡ አክሳሪ ነበሩ። ከጥራጥሬና የቅባት እህሎች በተጨማሪም አብዛኞቹ የወጪ/ ኤክስፖርት/ ምርቶች በኢትዮጵያ የወጣባቸውን ወጪ የሚሸፍኑ አልነበሩም። ለዚህም ዋናው ምክንያት በሀገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ነው። ይህም ለላኪው እጅግ ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል።

መንግሥት አሁን ያደረገው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ እነዚህን ችግሮች በመፍታት ኢኮኖሚው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል። ከማሻሻያው ጋር ተያይዞ የሚመጣው የመጀመሪያው ጉዳይ በተለይም የውጭ ምንዛሪ በሚፈለገው መጠን ማግኘት መቻሉ ነው፤ ይህም ተስፋ ተጥሎበታል። በመሆኑም ላኪው ገበያ ለማፈላለግ የሚያስችለውን የውጭ ምንዛሪ አግኝቶ ወደ ውጭ ሀገራት መንቀሳቀስ ያስችለዋል። በወጪ ንግድ ዘርፍ የተሰማራ ነጋዴ የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ ማግኘት መቻሉ ለዘርፉ ትልቅ እፎይታን ይሰጣል። አለፍ ሲልም ዘርፉ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በኪሳራ እንዳይቀጥል ማድረግ ያስችላል፤ ብሎም አትራፊ እንዲሆን በር ይከፍታል።

‹‹የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለዘርፉ የሚኖረው አበርክቶ ወጪ ከመሸፈን ባለፈ ትርፋማ ሊያደርገው ይችላል›› ያሉት አቶ ዘላለም፤ ዘርፉን ከኪሳራ አውጥቶ ትርፋማ ለማድረግ በዋነኛነት ጥራት ላይ መሥራትና ተወዳዳሪ መሆን የግድ ስለመሆኑም እሳቸውም አስታውቀዋል። ለውጡ ያመጣውን ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም በአጭር ጊዜ የምርት ጥራትና የሥራ ጥራት ጨምሮ ተወዳዳሪ በመሆን ዘርፉን ውጤታማ የማድረግ የቤት ሥራ ከሁሉም ይጠበቃል ሲሉም አስገንዝበዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከዚህ ቀደም የነበሩ የዘርፉን ማነቆዎች የፈታ ነው። ይሁን እንጂ፤ ተያይዘው የሚሰሩ የቤት ሥራዎች በርካታ ናቸው የሚሉት አቶ ዘላለም፤ በተለይም በዘርፉ የሚስተዋሉ የጥራት ችግሮችን በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍታት እንዲሁም ዘርፉን አትራፊና ተወዳዳሪ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ገበያው ሙሉ ለሙሉ በነጻ ውድድር ላይ ሲመሰረት ማንኛውም ከአምራቹ ጀምሮ በንግድ ሥራ ውስጥ የተሰማራ አካል በንግድ ሥርዓት ውስጥ መቆየት የሚችለው ተወዳድሮ ነው። ‹‹ተወዳዳሪ መሆን ማለት ደግሞ በእያንዳንዱ ስፍራ የሚሠራ ሥራ ጥራትና ምክንያታዊ የሆነ ዋጋ ሊኖረው ይገባል። ተወዳዳሪነት ሲባል አንደኛው የምርት ጥራት ሲሆን፤ ሁለተኛው በዋጋ ደረጃ ሊገዛ የሚችል ምርት ማቅረብና ተወዳዳሪ መሆን ነው›› በማለት ያስረዱት አቶ ዘላለም፤ ይህም የላኪዎችን ጥረት ብቻ የሚጠይቅ እንዳልሆነም አስገንዝበዋል። ከታች ከአምራቹ ጀምሮ በዘርፉ ተዋናይ የሆኑ የተለያዩ ተቋማትን ጥረት እንደሚጠይቅ ተናግረው፤ የሁሉንም አካላት በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

አቶ ዘላለም እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማቅመም ላኪዎች ማህበር የድርሻውን ለመወጣት ለአባላቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ይሠራል፤ በዚህ ላይ ሌሎች አካላትም በጋራ መሥራት አለባቸው። ለዚህም ማህበሩ ለአባላቱ የተለያዩ መድረኮችን እያዘጋጀ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየሠራ ነው።

ማሻሻያው አጠቃላይ በሀገሪቱ ያሉትን እንቅስቃሴዎች ማቀናጀትን በዋናነት የሚጠይቅና የግድ የሚል ጉዳይ መሆኑንም ጠቅሰው፤ የዘርፉ ተዋናዮች በሙሉ በቅንጅት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ከቅንጅቱ ባለፈ በጥራት ማምረትና ተወዳዳሪ መሆን ትልቅ ትኩረት የሚያሻቸው ጉዳይ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ሥራ አስኪያጁ እንደተናገሩት፤ ማሻሻያው ጥራት ጠብቆ ማምረትን የሚያስገድድ በመሆኑ በጥራት ማምረትና ተወዳዳሪ መሆን ከተቻለ ዘርፉ አትራፊ ይሆናል። የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያዎች እጅግ ተፈላጊና ተመራጭ ናቸው። በተለይም በአሁኑ ወቅት የግብርና ምርቶች በዓለም ላይ ከፍተኛ እጥረት በመኖሩ እንዲሁም የኢትዮጵያ ምርቶች በጣዕማቸው የተለዩና ተመራጭ በመሆናቸው ትልቅ ዕድል ነው።

ይህን ትልቅ ዕድል ወደ ድል ለመቀየር የምርት ጥራትን ማስጠበቅ ትልቁ የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል፤ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ መጠቀም የቤት ሥራውን መሥራትና ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ ለነገ የሚተው ተግባር አይደለም።

‹‹የኢትዮጵያ ምርቶች በተለይም የቅባት እህሎቹ እንደ ሰሊጥ ያሉት ወደ እስራኤል፣ አውሮፓ ሀገራት፣ ሩሲያ፣ ጀርመንና ሌሎች አገራትም በስፋት ይላካሉ›› ያሉት አቶ ዘላለም፤ የጥራጥሬ ምርቶች ደግሞ በዋናነት ህንድ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ ፓኪስታንና ሌሎች ሀገራትም እንደሚላኩ አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅትም ቻይናን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ሰፊ የገበያ ዕድል እንዳለ ጠቁመው፤ የገበያ ዕድሉን አሟጦ ለመጠቀምም ብዙ መሥራት ይገባል ብለዋል።

አሁን ምርቶቹ ወደ ውጭ ገበያ የሚላኩት በጥሬው ነው፤ እሴት ጭመራ ላይ አልተሠራም ያሉት አቶ ዘላለም፤ በጥሬው ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምሮ መላክ አዋጭና ተመራጭ ስለመሆኑም ገልጸዋል። እሴት ጭመራ ላይ ያልተሠራው በርካታ ማነቆዎች በመኖራቸው ምክንያት መሆኑንም ጠቁመዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በርካታ ማነቆዎችን እንደሚፈታና በርካታ ዕድሎችንም እንደሚፈጥር አስታውቀው፤ ላኪዎች ወደ እሴት ጭመራ መግባት የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠርና ዘርፉ ከኪሳራ ወደ ትርፍ እንደሚሸጋገርም አመላክተዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You