ኢትዮጵያ ባህል እያደረገች በመጣችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር የችግኝ ተከላ ባለፉት ዓመታት ባከናወነቻቸው ተግባራት በስኬት ላይ ስኬትን ደርባለች፡፡ መርሀ ግብሩ በተጀመረበት በ2011 ዓ/ም አራት ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የተጀመረው ይህ የችግኝ ተከላ፣ ዘንድሮም ከሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተፈጸመ ይገኛል፡፡
በአራት ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ፣ 25 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል የቻለች ናት፡፡ ባለፈው ዓመት መተግበር በተጀመረው ሁለተኛው ምእራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር የመጀመሪያው ዓመት የችግኝ ተከላ ይህን አሃዝ ወደ 32 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ለማድረስ ተችሏል፡፡ ይህን አሃዝ ዘንድሮ 40 ቢሊዮን ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ዘንድሮ ለመትከል ከታቀደው አብዛኛውን መትከል ተችሏል፡፡
ሀገሪቱ በየዓመቱ የምትተክላቸውን ችግኞች ብዛት እየጨመረች መጥታለች፡፡ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በተጀመረበት በ2011 ዓ.ም አራት ቢሊዮን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ ይህ አሃዝ ዘንድሮ ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ደርሷል፡፡
ሀገሪቱ ዘንድሮ ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ብታቅድም፣ ከስምንት ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለተከላው ተዘጋጅተዋል፤ ከታቀደው በላይ ሊተከል የሚችልበት ሁኔታ እንደሚኖር ካለፉት ዓመታት ተሞክሮ በመነሳት መናገር ይቻላል፡፡
ሀገሪቱ በየዓመቱ የምትክላቸውን ችግኞች ብዛት ብቻ አይደለም እየጨመረች የመጣችው፡፡ በአንድ ጀምበር በመቶ ሚሊየኖች ችግኞችን ለመትከል እያቀደች ከዕቅድ በላይ እየተከለች መጥታለች፡፡ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግበሩ የመጀመሪያ ዓመት በ2011 በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል በማቀድ 350 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል፡፡
ባለፈው ዓመትም በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ከዕቅድ በላይ 566 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡ በዚህም ሀገሪቱ ባለፈው ዓመት በራሷ የያዘችውን በእንድ ጀንበር 350 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ክብረ ወሰን መስበር ያስቻለ ሆኗል፡፡
ዘንድሮም በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል፡፡ ከእዚህ ውስጥ ደግሞ 150 ሚሊዮኑ ችግኞች ሀገሪቱ በአንድ ጀንበር የምትተክላቸው ችግኞች በሚል በዓለም አቀፍ ደረጃ በክብረወሰንነት እንዲመዘገቡ ለማድረግ ታቅዶና አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ እየተሠራ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ይህን ሁሉ መፈጸምም ይችላሉ፡፡ ባለፉት ዓመታት በችግኝ ተከላው ያስመዘገቧቸው ስኬታማ ተግባራትም ይህንንም ማሳካት እንደሚቻል ያመላክታሉ፡፡ የችግኝ ተከላን ባህል ማድረግ ለቻለ ሕዝብ በአንድ ጀንበር እንዲተክል የሚጠበቅበትን 600 ሚሊዮን ችግኞች እና ከዚህም በላይ መትከል ታሪኩ ላደረገ ሕዝብ ይህ እቅድ በእርግጠኝነት እንደሚሳካ ከወዲሁ መናገር ይቻላል፡፡
እ.እ.አ በ2026 የምትተክላቸውን ችግኞቹ ብዛት 50 ቢሊዮን ለማድረስ አቅዳ እየሠራች ላለች ሀገር ፣ ከዚህም ዘንድሮ 40 ቢሊዮኑ ላይ ለመድረስ ተከላውን ጫፍ ላይ ላደረሰች ሀገር፣ በችግኝ ተከላው በተገኘው ስኬት ክፉኛ ተመናምኖ የነበረውን የደን ሽፋኗን መመለስ ለጀመረችው ኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ መትከል እንደምትችል በእርግጠኝነትና በኩራትም መናገር ይቻላል፡፡
ይህንን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ይህ በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል የተያዘው እቅድ እንዲሳካ ሰሞኑን ለኢትዮጵያውያን ያስተላለፉት ጥሪ ደግሞ ለችግኝ ተከላው ሌላ ጉልበት በመሆን ያገልግላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያውያን በአንድነት የመንቀሳቀስ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን አመልክተው፣ ኢትዮጵያውያን አንድ ላይ ሲሆኑ ይበልጥ ስኬታማ እንደሚሆኑም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹እንድ ከሆንን፣ የበለጠ መሥራት እንችላለን ፤ በአንድ ስሜት ተንቀሳቅሰን፣ በመላ ኢትዮጵያ ዐሻራችንን እናኑር ብለዋል፡፡ እያንዳንዱ ጎልማሳና ወጣት ለመጪው ትውልድ ዐሻራውን ለማቆየት በችግኝ ተከላው ሰፊ ተሳትፎ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አንድ ሆኖ ታሪክ በመሥራት የሚታወቀው መላው ሕዝብ በችግኝ ተከላው መሳተፉ አንድ ሆኖ መሳተፉ እንደተጠበቀ፣ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በእዚህ የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ የትውልድ አደራ ተሰጥቷቸዋል፡፡ አደራውን ለመወጣት ደግሞ አቅሙም፣ ልምዱም እንዳላቸው ይታመናል፤ በእዚህ ላይ ደግሞ አደራ ተጥሎባቸዋል፡፡ ይህን አደራ ለመወጣት ነሀሴ 17 መገናኘት ብቻ ነው የሚያስፈልገው!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም