
አዲስ አበባ፡- ህብረተሰቡ ቆሻሻን አላግባብ ከመጣል ተቆጥቦ ለራሱም ሆነ ለመላው ህብረተሰብ ጤናና ለንጹህ አካባቢ መፈጠር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ ቀረበ፡፡ ያለአግባብ ቆሻሻን ከመጣል ጋር ተያይዞ በተሻሻሉ ደንቦች ዙሪያ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ እየተሰጠ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ የምስራች ግርማ እንደገለፁት አለአግባብ ቆሻሻን በማስወገድ ዙሪያ የተሻሻሉ ደንቦች ተግባራዊ መደረግ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ከፅዳት አስተዳደር ጋር በጋራ በመሆን ለሚዲያዎች መግለጫ ከመስጠት ጀምሮ በየክፍለ ከተማውና በየወረዳው የንቅናቄ መድረክ በመፍጠርና ማህበረሰብ አንቂዎችን በማሳተፍ ግንዛቤ እየተሰጠ እንዳለ ገልፀዋል፡፡
እንደርሳቸው ገለፃ፤ ግንዛቤ የመስጠት ሂደቱ አልቋል የሚባል ሳይሆን ቀስ በቀስ የሚቀጥል እንደሚሆንና ርምጃ መውሰዱ ግን ደንቡ እስከፀደቀ ድረስ ተፈፃሚ እየተደረገ እንዳለ አብራርተዋል፡፡
ባለሥልጣኑ ባለው ሃይል የቁጥጥር ሥራውን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ነገር ግን የደንብ ማስከበር ባለሙያዎች መቶ አስራ ዘጠኙንም ወረዳዎች ያዳርሳሉ ማለት ስለሚከብድ ህብረተሰቡ የፅዳት ጠቀሜታው ለራሱ መሆኑን አውቆ ቢያግዝ፣ ቢተባበርና ጥቆማ ቢሰጥ የተሻለ ነው ብለዋል፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተካልኝ በሻ በበኩላቸው በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ ደንቡ የወጣው የኮሪደር ልማቱን ደህንነት ከማስጠበቅ አንፃር ብቻ እንደሆነ የማሰብ ዝንባሌ እንዳለ ገልፀው ነገር ግን በከተማዋ በሚገኙ የትኛውም ቦታዎች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ስለመሆኑ በክፍለ ከተማው ባሉ ወረዳዎች ግንዛቤ እየተሰጠ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም ደንቡ ቆሻሻ በመጣል እንጂ ኮሪደር ልማት ላይ ቆሻሻ በመጣል የሚል እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባልም ብለዋል፡፡
ከዛ ውጪ በክፍለ ከተማው ከቆሻሻ አያያዝና አሰባሰብ ጀምሮ እስከ አወጋገድ ድረስ ቤት ለቤት ግንዛቤ እንደሚሰጥ ገልፀው በስምንቱም ወረዳዎች ባለሙያዎች ተመድበው ግንዛቤ የመፍጠር ሥራን እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡
ማንኛውም ሰው ያመነጨውን ደረቅ ቆሻሻ ላለመቀጣት ብቻ ሳይሆን የራሱን ጤናና የአካባቢው ገፅታ ከመጠበቅ አንፃር ለይቶ በአግባቡ መያዝ እንዳለበት ጠቅሰው መረጃው ላልደረሰውና ላልተረዳ አካልም ግንዛቤውን መስጠት የሁላችንም ኃላፊነት መሆን አለበት ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ነፃነት አለሙ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም