ቀደም ባሉት ጊዜያት ሆነ ዛሬ የትግራይ ሕዝብ ፍላጎት እንደ ሌሎች የሀገሪቱ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ሰላም እና ልማት ፤ ፍትህ እና ዴሞክራሲ የሰፈነበት ሀገር ተመስርቶ ማየት ነው ። ከዚሕ ያለፈ ጥያቄ ሆነ ፍላጎት የለውም ፤ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት እንደ አንድ ማኅበረሰብ የሄደባቸው የትግል መንገዶችም ሆኑ መንገዶቹ ያስከፈሉት ዋጋ ይህንን እውነታ ታሳቢ ያደረገ ነው።
የትግራይ ሕዝብ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በሀገረ መንግሥት ምስረታ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ የነበረው፣ ሀገረ መንግሥቱን በማጽናት እና በማስቀጠል ሂደትም ከፍ ያለ አበርክቶ ያበረከተ ነው ። ስለሀገሩ በጎ ከማሰብ ባለፈ ፣ ሀገር በችግር ውስጥ በሆነችባቸው ጊዜያት የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል፤ የሀገር ፍቅሩን፤ በተጨባጭ ማሳየት የቻለም ነው።
እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለነፃነት እና ለፍትህ ቀናኢ የሆነ ፤ ለነዚህ ትላልቅ ማህበራዊ እሴቶቹ የትኛውንም አይነት ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ የሆነ ነው። እነዚህን የትግራይ ሕዝብ ፍላጎቶች አውቆ ማክበር ይህንን ሕዝብ እወክላለሁ ከሚል ማንኛውም ቡድን የሚጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት ነው። የትኛውም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴው ለነዚህ እሴቶቹ የተገዛ ሊሆንም ይገባል።
በተለይም አሁን ላይ የዚህ ሕዝብ ተቆርቋሪ ነኝ የሚሉ ሁሉ ሕዝቡ በቀደሙት ጊዜያት ለሰላም እና ለልማት ፤ ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የከፈለውን እና አሁን ላይ በተጨባጭ ያለበትን እውነታ ታሳቢ በማድረግ ፤ ከፖለቲካ ዲስኩር ባለፈ ለሕዝቡ ፍላጎቶች ራሳቸውን ተገዥ ማድረግ ፤ ለዚህ የሚሆን ዝግጁነት እና ቁርጠኝነት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ።
በርግጥ የትግራይ ሕዝብ እንዳንዶች እንደሚሉት “ጦርነትን ባህላዊ ጨወታው አድርጎ ፤ ልጆቹን ለመገበር የተዘጋጀ ሕዝብ አይደለም” ፤ ሕዝቡ ከማንም ይልቅ የጦርነትን አስከፊነት በውስጡ ኖሮ ያየ፣ ለዚህም ህያው ምስክር የሆነ ነው ። በጦርነት፣ በጦርነት ዲስኩር እና ከበሮ በብዙ ተስፋ ያደረጋቸውን ልጆቹን የተነጠቀ ፤ ትናንቶቹን ከማጣት ባለፈ ዛሬውም ታማሚ የሆነበት ሕዝብ ነው።
ትናንት ስለ ዴሞክራሲ እና ፍትህ ብዙ ዋጋ ከፍሎ ዛሬ ላይ ራሱ የዴሞክራሲ እና የፍትህ ያለህ ባይ ሆኗል። ከብዙ የሕይወት መስዋዕትነት በኋላ የራሱን ዕጣ ፈንታ የሚወስንበትን እድል አጥቶ ፣ ሌሎች በሱ ጉዳይ አልፋ እና ኦሜጋ ሆነው መሠረታዊ የሚባለውን ፍላጎቱን እንኳን ሊያሟላ የሚችልበትን እድል አጥቶ፤ እጁን ለተመጽዋችነት ለመዘርጋት የተገደደ ነው።
የትግራይ እናቶች ተስፋ ያደረጉት የዛሬው ትውልድ ፤ ነገዎቹ ጨልመውበት ፤ ለስደት እና ለተስፋ መቁረጥ ተዳርጓል ፤ በዚህም በማኅበረሰቡ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መንገድ ሕገወጥነት ፣ ማንአለብኝነት እና ደንታ ቢስነት በስፋት እየተስተዋሉ ናቸው። በዚህም የሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት በፈተናዎች ከተሞላ ውሎ አድሯል።
ይህ ተጨባጭ እውነታ የትግራይን ሕዝብ እንደ ሕዝብ እየተፈታተነው ባለበት አሁናዊ እውነታ ፤ ሕዝቡን በብቸኝነት እንወክላለን ፤ ያለኛ ህልውናው ስጋት ላይ ነው የሚሉ ኃይሎች እየሄዱበት ያለው መንገድ የቀደመውን ትውልድ ብዙ ያልተገባ ዋጋ ያስከፈለ ፤ ከዚያም ባለፈ አሁን ካለው ትውልድ የፖለቲካ አስተሳሰብ ጋር የማይጣጣም ፤ የትግራይ ሕዝብ ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ የከፈለውን መስዋእትነት የሚያሳንስ ነው። አሁን ያለውን ትውልድ ራሱን የመሆን ነጻነት የሚገዳደር ነው።
ከዚህም ባለፈ እንደ ትናንቱ ፤ በሀገር ሰላም ፤ አጠቃላይ በሆነው የሕዝባችን የለውጥ ፍላጎት እና የመልማት መነሳሳት ላይ ሊያሳድር የሚችለው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍ ያለ ነው። ከትግራይ ሕዝብ ባለፈም እንደ ሀገር ሊያስከፍለን የሚችለው ዋጋ ከትናንቶች የከፋ ስለመሆኑም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።
የትግራይ ሕዝብ ፤ በተለይም አዲሱ ትውልዱ የራሱን እድል በራሱ ለመወሰን የሚያስችል በቂ የፖለቲካ አቅም እና መነቃቃት ያለው ነው ፤ የቀደመው ትውልድ በብዙ መራራ ትግል እና መስዋዕትነት ሰማእት ሆኖ ያለፈው ይህ ትውልዱ የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን የሚያስችለውን መብቱን ተጨባጭ ለማድረግ ነው። ይህን አምኖ መቀበል እና መተግበር ለትግራይ ሕዝብ ውግንና አለን የሚሉ ኃይሎች የተልዕኮ ጅማሪም ፍጻሜም ሊሆን ይገባል!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም