የዲጂታል ሎቶሪ እጣ አወጣጥን ተዓማኒ ለማድረግ መተግበሪያ እየተገነባ ነው

አዲስ አበባ፡– የዲጂታል ሎተሪ እጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓቱን ተዓማኒ ለማድረግ መተግበሪያ እየተገነባ መሆኑን የብሔራዊ ሎቶሪ አስተዳደር ገለጸ።

በብሔራዊ ሎቶሪ አስተዳደር የኮሚኔኬሽን ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ነዋይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የዲጂታል ሎቶሪ አማራጭ የሆነውን የአድማስ ሎቶሪ የእጣ አወጣጥ ታማኝ ለማድረግ መተግበሪያ እየተሠራ ነው።

በተጨማሪም ዳይሬክተሩ የእጣውን ውጤት በ ‹‹ዩ. ኤስ .ኤስ .ዲ ኮድ›› ለማሳወቅ እየተሠራ ነው ሲሉ አስረድተዋል። የእጣ አወጣጡ የሎተሪው እጣ ቁጥር በተቆረጠበት መንገድ አለመታወቁ እንደ ችግር የሚወሰድ መሆኑን በመግለጽ፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ የወጣውን እጣ ለሁሉም ሎተሪውን ለቆረጡ ደንበኞች ለማሳወቅ በ‹‹ዩ.ኤስ. ኤስ ዲ›› አማራጭ ለማሳወቅ እየተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በ2017 ዓ.ም ሌላ የድጅታል ሎቶሪ የሚጀመር መሆኑን የተናገሩት አቶ ቴዎድሮስ ፤ በዚህም ደንበኞች ሎተሪ እንዲቆርጡ እና የወጣውን እጣ ለማሳወቅ መተግበሪያ እየተገነባ ነው ሲሉ ገልጸዋል። እጣው ሲወጣ ለሁሉም ደንበኞች በስልክ መልዕክት ለማሳወቅ አይመችም የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በምክንያትነት የገለጹት፤ ሎተሪውን የሚቆርጡት በርካቶች በመሆናቸው የተሞከረ ቢሆንም እንዳል ተቻለ አስረድተዋል።

አድማስ ሎቶሪ ከተጀመረ ሁለት ዓመት የሞላው ሲሆን፤ በርካታ ሰዎችም እየቆረጡ ይገኛል። ሎተሪው በተጀመረ ወቅት ለተወሰነ ዙር በቴሌቪዥን በቀጥታ ስርጭት ሲተላለፍ ነበር። ማህበረሰቡ የሎተሪውን አወጣጥ እያወቀ ሲመጣ ከወጪም አንጻር ሌሎች የማሳወቂያ አማራጮች መጠቀም ተጀምሯል ብለዋል።

አቶ ቴዎድሮስ እንደተናገሩት፤ የእጣ አወጣጡ በመጀመሪያ የሎተሪዎች ቁጥር ቅደም ተከትል በኮምፒውተር ከተለየ በኋላ፤ እንደ ወረቀት ሎተሪው አወጣጥ በማሽን የሚከናወን ነው። እጣው በሚወጣበት ወቅት፤ በቲክቶክ እና ቴሌግራም በቀጥታ ስርጭት ይተላለፋል። የእጣ አወጣጡ ተቀርጾ በዋልታ ዩቱብ ምሽት ላይ ይተላለፋል። በተጨማሪም የቲክቶክ እና የፌስቡክ ደንበኞች የሚያጋሩበት ሁኔታ አለ ሲሉ አስረድተዋል።

ዳይሬክተሩ እንደተናገሩቱ የዲጂታል ሎቶሪ አማራጭ ለመጠቀም የተፈለገው፤ በወረቀት የሚታተሙ ሎተሪዎች የማሳተሚያ ወጪያቸው እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት እንደሆነ አንስተዋል። ዲጂታል ሎተሪው ከዚህ በፊት የነበረውን እንግልት ቀንሷል። ሎተሪን ተደራሽ ከማድረግ ረገድ እቤት ተቀምጦ መቁረጥ የሚቻል ስለሆነ ገጠር አካባቢዎች ለማድረስ እድል ፈጥሯል ሲሉ አብራርተዋል።

እጣው ከወጣ በኋላ ለሁሉም ባለ እድለኞች ደውሎ የማሳወቅ ሥራ ይሠራል። የዝናብ ሁኔታው ካላስቸገረ በስተቀር ተሸላሚዎች ከብሔራዊ ሎተሪ አጥር ግቢ ውጭ እንዲሸለሙ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You