የአዲሱ ትምህርት ዘመን የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች

የ2017 ዓም የትምህርት ዘመን ሊጀመር ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ ብቻ ይቀረዋል። በዚህ ወር እንደተለመደው የትምህርት ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ይከናወናሉ። ከነዚህ ውስጥ ተማሪዎችን መመዝገብ፣ የትምህርት ቤቶችን ምድረ ግቢ ማፅዳትና አመቺ የማድረግ፣ የመማሪያ ክፍሎችን ማደስና ለመማር ማስተማር ሂደት ወሳኝ የሆኑ ግብዓቶችን የማሟላት ሥራዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ። ይህ ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ሂደት ምቹ የማድረግ ሥራ ከዚህ ቀደምም የነበረና አሁንም እየተሠራ ያለ ነው። ይሁንና ይህ ሥራ በፊት ከነበረው ልዩ የሚያደርገው የትምህርት ቤት ማደስ ሥራው ባለሀብቶችንና የትምህርት ቤት ማኅበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ መከናወኑ ነው።

በተለይ ባለሀብቶች በትምህርት ቤቶች ማደስ ሥራ መሳተፋቸው ትምህርት ቤቶች ከዚህ በፊት ከነበራቸው ይዞታ የተሻለ ገፅታ እንዲላበሱና ለመማር ማስተማር ሂደት ይበልጥ አመቺ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ለዚህ ሥራ ደግሞ በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለሀብቶችንና የትምህርት ቤት ማኅበረሰቡን በማስተባበር ትልቁን ድርሻ ወስዷል። የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮም የትምህርት አመራሮችን፣ መምህራንን፣ የትምህርት ቤት ርእሰ መምህራንን፣ ወላጆችንና ተማሪዎችን በማሳመንና በማስተባበር የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል።

በትምህርት ቅድመ ዝግጅት ሥራ ትምህርት ቤቶችን ከማደስና ለመማር ማስተማር ሂደቱ አመቺ ከማድረግ በዘለለ ለአካል ጉዳተኞችና ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላትና ለእነርሱ አመቺ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሥራዎችም በስፋት ተከናውነዋል። ለልዩ ፍላጎትና አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በትምህርት ቤቶች ውስጥ አመቺ የመማር ማስተማር ምሕዳር በመፈጠሩ በትምህርት ውጤታቸው ላይ ለውጥ መምጣት ችሏል። ይህንንም የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የ2016 ዓ.ም አፈፃፀምን ለከተማው ምክር ቤት ሪፖርት ባደረገበት ወቅት አስታውቋል።

በሌላ አባባል ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር አመቺ ማድረግ ለአካል ጉዳተኞችና ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለመደበኛ ተማሪዎች ውጤት መሻሻልም አይነተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው ያመለክታል። ትምህርት ቤቶችን ውብ፣ ማራኪና ለመማር ማስተማር አመቺ የማድረጉ ሥራ በተማሪዎች ውጤት መሻሻል ላይ ከሚኖረው በጎ ተፅዕኖ ባለፈ በመንግሥትና በግል ትምህርት ቤቶች መካከል ያለውን ፈርጀ ብዙ ልዩነት በማጥበብ ረገድም ሚናው የጎላ ነው። በተጨማሪም በትምህርት ቤቶቹ መካከል የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የሚደረገውን የፉክክር መንፈስ ያሳድጋል።

ከዚህ ባሻገር ከዚህ በፊት የነበረውን የትምህርት ቤቶች ደረጃ በማሳደግ ለዘመኑ የሚመጥኑ ትምህርት ቤቶችን ለመፍጠርና የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ ትልቅ ሚና አለው። ይህ ብቻ ሳይሆን ትምህርት ቤቶችን በዚህ ደረጃ መሥራት ከዚህ ቀደም በማኅበረሰቡ በኩል የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የወረዱና በተገቢው ልክ ትምህርት የማይሰጥባቸው እንደሆኑ የሚቆጠሩበትን የተሳሳተ አመለካከት በመቀየር ረገድ ትልቅ አስተዋፅዖ አለው።

ወላጆችም በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ያላቸው አመኔታ እንዲጨምርና ልጆቻቸውን ወደትምህርት ገበታ እንዲልኩ ይበልጥ መነሳሳትን ይፈጥርላቸዋል። ትምህርት ቤቶቹ በአከባቢው ማኅበረሰብና ባለሀብቶች ደረጃቸውን ጠብቀው መገንባታቸውና መታደሳቸው ደግሞ ወላጆች የባለቤትነት ስሜት እንዲላበሱ ያደርጋል።

እንዲያም ሆኖ ትምህርት ቤቶችን አዲስ ገፅታ የማላበስና ለመማር ማስተማር አመቺ የማድረግ ሥራ ወረትና የአንድ ወቅት ሥራ ብቻ እንዳይሆን የብዙዎች ስጋት ነው። ስለዚህ ሥራው የወረትና የአንድ ሰሞን ብቻ እንዳይሆን ከከተማ አስተዳደሩ፣ ከከተማው ትምህርት ቢሮ፣ ከትምህርት ቤቶች፣ ከመምህራን፣ ከተማሪዎችና ከወላጆች ብዙ ይጠበቃል ።

የከተማ አስተዳደሩ የጀመረው ሥራ በተማሪዎች ውጤትና ትምህርት ጥራት ላይ ተግባራዊ ለውጥ ማምጣቱን በመገንዘብ ትምህርት ቤቶችን የማደስና ለመማር ማስተማር ሂደት አመቺ የማድረግ ሥራ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በተለይ ባለሀብቶችና የትምህርት ማኅበረሰቡ የጀመሩትን ትምህርት ቤቶችን የማደስና አመቺ የማድረግ ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ከእነርሱ ጋር በቅንጅትና በተግባቦት ብሎም ሁለንተናዊ ድጋፍ በመድረግ ሊሠራ ይገባል።

የከተማው ትምህርት ቢሮ አመራሮችም ቢሆኑ ይህ ሥራ ከዚህ በተሻለ ሁኔታ እንዲቀጥል ታች ድረስ ወርደው የወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤቶችንና ትምህርት ቤቶችን መደገፍና ክትትል ማድረግ እንዲሁም ለዚህ ሥራ በንቃት እንዲሳተፉ መቀስቀስ ይጠበቅባቸዋል። በዋናነት ከነባሮቹ በተጨማሪ ሌሎች ባለሀብቶችን በማፈላለግ በትምህርት ቤቶች እድሳትና አመቺ የማድረግ ሥራ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። የትምህርት ማኅበረሰቡም በዚሁ ሥራ ልክ እንደባለሀብቱ ሁሉ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን አመራሮቹ ግፊት ማድረግ አለባቸው።

ትምህርት ቤቶች በተለይ መምህራንና ርዕሰ መምህራን በዚህ ሥራ ዋና ተዋንያን እንደመሆናቸው ደረጃቸውን ጠብቀው የተገነቡ፣ መልሰው የታደሱና ለመማር ማስተማር ሁኔታ አመቺ ተደርገው የተሠሩ ትምህርት ቤቶችን እንዳይጎዱ የመጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ለዚህ ደግሞ በተለይ ተማሪዎችን የማሳመንና ትምህርት ቤቶቹን እንደራሳቸው ንብረት እንዲጠብቁ የማስተማር ግዴታ አለባቸው።

ትምህርት ቤቶች መጪው ትውልድም ጭምር የሚማርባቸው እንደመሆናቸው ደረጃቸውን ጠብቀው ረጅም ግዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ተማሪዎች በባለቤትነት ስሜት የትምህርት ቤቶችን ንብረት መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ወላጆችም ይህን አውቀው ልጆቻቸውን ትምህርት ቤቶቻቸውን እንዲጠብቁና ትምህርት ቤቶችን ንብረት በአግባቡ እንዲጠቀሙ መገሰፅና መምከር አለባቸው። ስለዚህ ከከተማ አስተዳደሩ ጀምሮ ሁሉም የትምህርት ቤት ማኅበረሰብ የሚጠበቅበትን ድርሻ ሲወጣ ተማሪዎች በደረጃቸውን በጠበቁና በተሻሉ ትምህርት ቤት ተምረው ውጤታቸውን ማሻሻል ይችላሉ። የትምህርት ጥራትም ይረጋገጣል።

ትምህርት ቤቶችን ከማደስና ለመማር ማስተማር ምቹ ከማደረግ ባለፈ በትምህርት ቅድመ ዝግጅት ሥራው ከወዲሁ እየተከናወኑ ካሉ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ትምህርት ቤቶች በቴክኖሎጂ እንዲዘምኑ የማድረግ ሥራ ነው። በዚሁ መነሻነት የ2017 ዓ.ም የተማሪዎች ምዝገባ በሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ኦንላይን እንደሚካሄድ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ከሳምንታት በፊት አስታውቋል። ትምህርት ቤቶችም ይህን አውቀው ከወዲሁ በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባቸው ቢሮው ገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልማትና ማስፋት ዳይሬክቶሬት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን የተማሪዎችን ምዝገባ ኦን ላይን ለማካሄድ በለማው የኢ ስኩል ቴክኖሎጂ ዙሪያ ለርዕሳነ መምህራን ጨምሮ ለአይ ሲቲ እና መረጃ ባለሙያዎች በዙር ሥልጠና ሰጥቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ኡመር በሥልጠናው ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ቢሮው ላለፉት ሁለት ዓመታት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን የ ‹‹ኢ ስኩል›› ፕሮጀክትን በመቅረጽ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልፀዋል። በዚህ ቴክኖሎጂ አማካይነት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ የተማሪዎች ምዝገባን በሲስተሙ አማካይነት ኦን ላይን ማካሄድ እንደመሆኑ ሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ኦንላይን በመመዝገብ ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ትምህርት ቤቶች ለምዝገባው የሚያስፈልጉ ኮምፒውተሮችን ጨምሮ የኢንተርኔት መሠረተ ልማቶችን ከወዲሁ ዝግጁ በማድረግ የምዝገባው ሂደት ስኬታማ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንደሚገባቸውም ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።

የ ‹‹ኢ ስኩል›› ፕሮጀክት የመማር ማስተማር ሂደቱን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ከማድረጉ ባሻገር ፖሊሲ አውጪዎችም ሆኑ በጀት መዳቢ አካላት ከትምህርት ጋር የተገናኙ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ የሚያስችል ሲስተም መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ዮናስ ተገኝ ጠቁመዋል። ምዝገባው በትምህርት ቤት መረጃ አስተዳደር ሲስተም (school information management system) አማካይነት የሚካሄድ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በመጀመሪያው ዙር ቂርቆስ ልደታ እና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ርዕሳነ መምህራን እንዲሁም የአይ ሲቲ እና መረጃ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን በቀጣይ ለቀሪ ክፍለ ከተሞችም ተመሳሳይ ሥልጠና እንደሚሰጥ ታውቋል። ይህም ለትምህርት ቤቶች አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን በበቂ ሁኔታ ከሟሟላት ባሻገር በቴክኖሎጂ እንዲዘምኑ በከተማ አስተዳደሩ በኩል የሚደረገውን ጥረት ያሳያል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከትምህርት ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የ2017 የትምህርት ዘመን የትምህርት ጊዜ ሰሌዳ ይፋ ተደርጓል። በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በከተማ አስተዳደሩ ስር ባሉ የመንግሥት፣ የግልና በሌሎች የተያዙ ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛ፣ መካከለኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ወጥነት ያለው የትምህርት አተገባበር በማስፈለጉ የትምህርት ጊዜ ሰሌዳ /የትምህርት ካላንደር/ እንደተዘጋጀም ነው የተጠቆመው።

በዚሁ መሠረት ከሰኔ 24 እስከ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የነባር ተማሪዎች ምዝገባ እና የመጽሐፍት ስርጭት እንደሚካሄድ፣ ከነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ መምህራን በትምህርት ቤታቸው ተገኝተው ሪፖርት በማድረግ አጠቃላይ የመምህራን ጉባኤ እንደሚደረግ፣ ከነሐሴ 21-30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የ7ተኛ እና የ9ኛ ክፍል ተማሪዎች ምዝገባ እንደሚከናወን ተገልጿል።

ከጳጉሜ 1 እስከ ጳጉሜ 5 ቀን ድረስ አስፈላጊውን መረጃ አሟልተው የሚመጡ አዲስ የተማሪዎች ምዝገባ እንደሚካሄድ ፣መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም ለተማሪዎች ስለ ትምህርት ቤቶች ሕገ ደንብና ተያያዥ ጉዳይ ላይ ገለጻ እንደሚሰጥ፣ መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም መደበኛ ትምህርት እንደሚጀመር፣ መስከረም 13 ቀን 2017 ዓ.ም ትምህርት በሬዲዮ ስርጭት እንደሚጀምር ተጠቁሟል።

ከኅዳር 16-18 ቀን 2017 ዓ.ም አንደኛ ወሰነ ትምህርት አጋማሽ ፈተና እንደሚሰጥ፣ ከጥር 7-9 ቀን 2017 ዓ.ም ለ6ኛ፣ ለ8ኛ እና ለ12ኛ ክፍል ሞዴል ፈተና እንደሚሰጥ፣ ከጥር 19-23 ቀን 2017 ዓ.ም አንደኛ ወሰነ ትምህርት ማጠቃለያ ፈተና እንደሚካሄድ፣ ከጥር 26-29 ቀን 2017 ዓ.ም መምህራን ፈተና የሚያርሙበት እና ውጤት ማጠናቀሪያ ሳምንት እንደሆነ፣ ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም መምህራን የተማሪዎችን የፈተና ውጤት የሚያሳውቁበት መሆኑ ተነግሯል።

የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም የሁለተኛ ወሰነ ትምህርት እንደሚጀመር፣ ሚያዚያ 6-8 ቀን 2017 ዓ.ም የሁለተኛ ወሰነ ትምህርት አጋማሽ ፈተና እንደሚሰጥ፣ ግንቦት 19-22 ቀን 2017 ለ6ኛ፣ ለ8ኛ እና ለ12ኛ ክፍል ሞዴል ፈተና እንደሚሰጥ፣ ከሰኔ 3-4 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ መልቀቂያ ፈተና እንደሚካሄድ፣ ከሰኔ 9-11 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና እንደሚሰጥ፣ ከሰኔ 16-20 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ሁለተኛ ወሰነ ትምህርት ማጠቃለያ ፈተና እንደሚከናወን፣ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ መምህራን የተማሪዎችን የፈተና ውጤት የሚያሳውቁበት እንደሚሆንና ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም የውጤት መግለጫ ካርድ በመስጠት የዓመቱ ትምህርት እንደሚጠናቀቅ ታውቋል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You