የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ካለው ስትራቴጂክ ጠቀሜታ አኳያ የብዙዎችን ቀልብ የሚስብ ነው። ይህንን ተከትሎም በየወቅቱ በሚፈጠሩ ዓለም አቀፍ የፍላጎት ተቃርኖዎች አካባቢው ለግጭት እና ለአለመረጋጋት ፣ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦችም ለድህነት እና ለኋላ ቀርነት የተጋለጡ እና በዚህም ብዙ ዋጋ እንዲከፍሉ ያስገደደ ነው።
በተለይም የቀዝቃዛውን ጦርነት ተከትሎ በአካባቢው የተፈጠረው የኃያላኑ ሽኩቻ ፣በአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን ወንድማማችነት ፣ ተቻችሎ እና ተስማምቶ በጋራ የመኖር እሴቶችን በመሸርሸር ፣አካባቢው ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በግጭት እና በአለመረጋጋት እንዲታመስ አድርጎታል።
ይህ በአብዛኛው ከአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች እውነተኛ ፍላጎት የማይነሳ ፣ በአብዛኛው ቅኝ ገዥዎች ቀደም ባለው የአገዛዝ ዘመናቸው ፈጥረውት ከሄዱት የልዩነት ትርክት የሚቀዳው የአንድ ሃይማኖት ፣ባህል እና ማህበራዊ እሴት ባለቤት የሆኑ ሕዝቦችን ሳይቀር ተቃርኖ ውስጥ በመክተት ብዙ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ ያደረገ ነው።
ለዚህ ደግሞ ከነጻነት ማግስት ጀምሮ በአካባቢው የተከሰቱ እና ዛሬም ድረስ ለአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ሰላም እና አለመረጋጋት ምንጭ የሆኑ ችግሮች ፣ ከትናንት የልዩነት ትርክቶች የመነጩ፤ ትርክቶቹ ተጠቃሚ ያደርገናል ብለው በሚያስቡ ኃይሎች አቅም ገዝተው ፣ጉልበት አግኝተው የዘለቁ ናቸው።
ዛሬም የአካባቢው ሀገራት በቀጣናው የተሻለ ሰላም እና መረጋጋት ለመፍጠር የሚያደርጓቸው ጥረቶች ፤አካባቢው ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ፍላጎት ባላቸው ኃይሎች ትርጉም ያለው ውጤት እንዳያመጣ ፤ከዚያም አልፎ አካባቢው የአሸባሪዎች መፈልፈያ እንዲሆን አድርጎታል።
ለዚህ በሶማሊያ መሠረት ያደረገውን እና በዓለም አቀፍ አሸባሪነት የተፈረጀውን አልሸባብን ውልደት እና እድገት ማየት ይቻላል። ይህ ጽንፈኛ ቡድን በሶማሊያ እንደሀገር የልዩነት ትርክት የፈጠረውን የሀገረ መንግሥት ክፍተት በመጠቀም ፣የሀገሪቱን ሕዝቦች በጽንፈኛ አመለካከቱ ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ድንበር ተሻግሮም በአካባቢው ሀገራት ሰላም እና ደህንነት ላይ ስጋት ሆኗል።
የአካባቢው ሀገራት በአፍሪካ ኅብረት በኩል ሆነ በተናጠል ፣ቡድኑ በሶማሊያ ሕዝብ ላይ ሆነ በአካባቢው ሀገራት ላይ የፈጠረውን የሽብር ስጋት ለመቀልበስ ተንቀሳቅሰዋል። በተለይም የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ወንድም ለሆነው የሶማሊያ ሕዝብ ሰላም እና ደህንነት ከማንም በላይ ዋጋ በመክፈል ለሕዝቡ ያላቸውን አጋርነት በሕይወት መስዋዕትነት በተጨባጭ አሳይተዋል።
ለበለጠ ድጋፍና ከንፈር ከመምጠጥ ባለፈ፤ ከአልሸባብ ጋር ፊት ለፊት በመግጠም ዛሬ ላይ የሶማሊያ ሕዝብ ላገኘው አንጻራዊ ሰላም እና መረጋጋት በታሪክ ውስጥ ገዝፎ የሚታይ የመስዋእትነት ታሪክ ጽፈዋል። በዚህም ለሶማሊያ ሕዝብ ያላቸውን ክብር እና ወንድማዊ ፍቅር በደም አረጋግጠዋል።
በርግጥ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያውያን በላይ ለሶማሊያ ሕዝብ ሊቀርብ እና ሊቆረቆር የሚችል የለም ፤ይኖራል ብሎ ማሰብ የዋህነት ብቻ ሳይሆን ለትዝብት የሚጥልም ነው። የነዚህ ሀገራት ሕዝቦች ከባህል እና ከሃይማኖት ባለፈ እጣ ፈንታቸውን ብሩህ የሚያደርግ የጋራ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፍላጎቶች አሏቸው።
እነዚህ ፍላጎቶች፤ ከሁሉም በላይ አንዳቸው የአንዳቸውን ሰላም እና መረጋጋት አብዝተው እንዲያስቡ እና ለዚህ የሚሆን ዝግጁነት እንዲፈጥሩ አስችሏቸዋል፤ አንዳቸው የሌላኛውን ችግር የራሳቸው አድርገው በመውሰድ ራሳቸውን ዋነኛ የመፍትሔ አካል አድርገው እንዲያስቡና በተጨባጭም የመፍትሔ አካል ሆነው እንዲቀርቡ አድርጓቸዋል።
ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ከማንም በላይ ለሶማሊያ ሰላም እና መረጋጋት ብዙ ዋጋ የከፈለው ፤በከፈለው ዋጋም ለሕዝቡ አሁናዊ እፎይታ መፍጠር የቻለው። ይህንን እውነታ በየትኛውም መልኩ አለመቀበል ፤ ወይም አሳንሶ ለማየት መሞከር የሶማሊያ ሕዝብ በአሸባሪዎች የደረሰበትን እና እየደረሰበት ያለውን መከራና ስቃይ የመደገፍና የማስቀጠል ያህል የሚቆጠር ነው።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር አለመጣጣሞች የገጠማት ሲመስላቸው በቀቢጸ ተስፋ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ሀገራት ለሶማሊያውያን ተቆርቋሪ በመምስል ኢትዮጵያ ላይ ችግር ለመፍጠር ድብቅ አጀንዳ ቢያራምዱም ሃሳባቸውና እቅዳቸው ቀቢጸ ተስፋ እና ከንቱ ምኞት ከመሆን አያልፍም!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም