ተቋማት ለምርት እና ምርታማነት ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው ሊንቀሳቀሱ ይገባል !

እንደ ሀገር ከሚፈታተነን የኑሮ ውድነት/ሸቀጥ ዋጋ መናር ለዘለቄታው ለመውጣት ምርት እና ምርታማነት ማሳደግ ትልቁ የቤት ሥራችን ነው። ለዚህ ደግሞ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በተለይም በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ምርታማነት ከችግሩ በአጭር ጊዜ መውጣት እንደምንችል ተስፋ ሰጭ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።

ሰው ሠራሽ ከሆኑ ችግሮች ውጪ፤ የሸቀጦች ዋጋ ንረቱ፤ በገበያ ላይ ካለ የፍላጎት እና የአቅርቦት አለመጣጣም የሚመነጭ ስለመሆኑ ብዙም የሚያነጋግር አይደለም። ይህ ችግር ለዘለቄታው ሊፈታ የሚችለውም በገበያው ላይ ከፍላጎት ጋር የሚመጣጣም ምርት ማቅረብ ሲቻል ብቻ ነው።

ከዚህ አንጻር ሀገራችን በተለይ ለግብርናው ዘርፍ ካላት ተስማሚ የአየር ሁኔታ፤ የሚታረስ መሬት፣ የውሀ እና የሰው ሀብት አኳያ፣ እነዚህን አቅሞች ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ አቀናጅቶ መጓዝ ከተቻለ፤ በሀገሪቱ በግብርና ሸቀጦች ዙሪያ የሚስተዋለውን እጥረት በማስወገድ ገበያውን የሚሸከም ምርት ማምረት የሚከብድ አይሆንም።

ከዚህም ባለፈ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለውን አሁናዊ እና ሀገራዊ አቅም በማቀናጀት፤ ከውጪ የሚመጡ ምርቶችን በመተካት፤ በሸቀጦቹ ዙሪያ የሚፈጠረውን እጥረትም ሆነ እሱን ተከትሎ የሚከሰተውን የዋጋ ንረት መቆጣጠር ይቻላል ። ለዚህም የሚሆን ሀገራዊ አቅም ስለመኖሩም በቅርቡ “ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል መሪ ቃል ዘርፉን ለማነቃቃት የተደረገው ጥረት ያስገኛቸው ውጤቶች ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው።

አሁን ላይ በሀገሪቱ ተግባራዊ እየሆነ ላለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ስኬታማነት ተግዳሮት ሆነው ከሚጠቀሱት ፈተናዎች አንዱ ይሄው በሀገሪቱ ሊከሰት የሚችለው የምርቶች የዋጋ ንረት ነው። ችግሩ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በማሻሻያው ትግበራ ላይ መንገራገጮች መፍጠሩ የማይቀር ነው።

በተለይም የሀገሪቱ የንግድ ሥርዓት ከመጣበት ያልተገራ መንገድ አኳያ፤ ተጠባቂው ችግር ማሻሻያው ተግባራዊ ከሆነበት ቀን ማግስት ጀምሮ እየተስተዋለ ይገኛልና። መንግሥትም እየወሰደ ያለው እርምጃ ሕገወጥነትን ከመከላከል አኳያ ሊያመጣ የሚችለው ውጤት ቢኖረውም ችግሩን ለዘለቄታው መፍታት ግን ብቻውን በቂ አይደለም።

ከዚህ አኳያ የሚመለከታቸው አካላት ሀገራዊ ምርታማነትን በሁለንተናዊ መልኩ ማሳደግ የሚያስችል ስትራቴጂ ነድፈው ለተፈጻሚነቱ በጠንካራ ዲሲፕሊን እና ከፍ ባለ የአመራር ተነሳሽነት ሊሠሩ ይገባል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሀገራዊ ምርታማነትን ለማሳደግ ይዞት የመጣውን መልካም ዕድል ተረድቶ ፈጥኖ መንቀሳቀስንም ይጠይቃል።

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ፤ በኩታ ገጠም እርሻ፤ በሌማት ትሩፋት፤ በበጋ የመስኖ ስንዴ እርሻ፣ በሩዝ እና በቡና…ወዘተ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ የተገኙ ውጤቶች በርግጥም ሀገራዊ ምርታማነትን ተጨባጭ በማድረግ በገበያ ላይ የሚታየውን የፍላጎት እና የአቅርቦት አለመጣጣምን ማጥበብ እንደሚቻል አመላካች ነው።

ይህ ደግሞ ሕዝባችን በተለይም በግብርናው ዘርፍ ካለው የምርታማነት ችግር አኳያ፣ ለረጅም ጊዜያት ሲያጋጥመው ከቆየው የዋጋ መናር መጥቶ፣ ምርቶቹን በፍላጎቱ መጠን አቅሙን ባማከለ ሁኔታ የሚያገኝበትን ዕድል የሚፈጥር ይሆናል ። ከዚህም አልፉ በምግብ እህል እራስን በመቻል ከተመፅዋችነት መውጣት የሚያስችለን ነው።

በስንዴ ልማት እንደታየውም፤ በጥቃት ዓመታት ውስጥ በግብርና ምርቶች ዓለም አቀፍ ገበያ በመቀላቀል፤ ሃገር ከዘርፉ የተሻለ ተጠቃሚ ልትሆን የምትችልበትን ተጨባጭ ሁኔታ በመፍጠር፤ ለጀመርነው የብልፅግና ጎዳና ስኬት የሚሆን ተጨማሪ አቅም መፍጠር ያስችለናል።

ምርት እና ምርታማነትን በግብርናው ዘርፍ መፍጠር መቻላችን በራሱ፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለጀመርነው መነቃቃት ትልቅ ግብዓት የሚሆን፤ በግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ሰፋፊ የሥራ ዕድል እና ትርጉም ያለው የውጪ ምንዛሪ መፍጠር የሚያስችል ነው ።

ምርታማነት በዓይነትም በጥራትም የማሳደጉ እውነታ እንደ ሀገር ለጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ጉዞ ወሳኝ አቅም ከመሆኑ አንጻር፤ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ለቴክኖሎጂ ለግብዓት እና ለእውቀት ሽግግር ተገቢውን ትኩረት ሰጥተን ልንቀሳቀስ ይገባል። ለዚህ ደግሞ የሚመለከታቸው ተቋማት በተለይም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርምር እና ጥናት ራሳቸውን በአግባቡ ሊያዘጋጁ ይገባል!

አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You