ባለንበት ዘመን የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሕልውና የሚወሰነው ለሕግ እና ለሕጋዊ ሥርዓት ካለው ተገዥነት ነው። በተለይም በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ በሚገኙ ሀገራት ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሥርዓቱ ግንባታ ካላቸው የማይተካ አበርክቶ አኳያ ለሕግ እና ለሕጋዊ ሥርዓት የመገዛታቸው እውነታ አጠቃላይ ከሆነው የሀገር ዕጣ ፈንታ ጋር የሚቆራኝ ነው።
ይህንን እውነታ በአግባቡ ተረድቶ፤ እለታዊ በሆነው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ተፈጻሚ ማድረግ ያልቻለ የፖለቲካ ድርጅት፤ የትኛውም አይነት የሕዝብ ውክልና እንዳለው አድርጎ የማሰብ ዕድሉ ቢኖረውም፤ ውክልናው በሕዝብ ውስጥ ሕገወጥነትን ከማስፈን ባለፈ ሊያመጣው የሚችለው ሕዝባዊ ተጠቃሚነት አይኖርም።
ከሕግ የበላይነት ያፈነገጠ የፖለቲካ መስመር አንድም ራስን ከሕግ በላይ አድርጎ ከማሰብ ያልተገባ እብሪት፤ አለበለዚያም ሕገወጥነት በሚፈጥረው ሁከት እና ግርግር የራስን ድብቅ ፍላጎት ለማሳካት የሚደረግ ጊዜ ያለፈበት፤ የዘመኑን ትውልድ የማይመጥን፤ የሚያሳንስ እና ላልተገባ ችግር የሚያጋልጥ ነው።
በተለይም በድህነት እና በኋላ ቀርነት ውስጥ በሚኖሩ ሕዝቦች ውስጥ እንዲህ አይነቱ ችግር ተደጋግሞ የመከሰቱ እውነታ ፤ የሕዝቦቹን ዛሬን ከማበላሸት አልፎ፤ ነገዎቻቸውን የግጭት ጽልመት በማልበስ፤ ትውልዶች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው እንዳይወስኑ የሚያደርግ፤ የሚያስከፍላቸውም ዋጋ ተስፋቸውን እስከመናጠቅ የሚደርስ ነው ።
ይህ እውነታ እንደሀገር እኛ ኢትዮጵያውያንን ብዙ ያልተገባ ዋጋ እንድንከፍል ያስገደደን፤ ዛሬም ድረስ እንደ ጥላ እየተከተለን ላለው እና አንገታችንን ለሚያስደፋን ድህነት እና ኋላቀርነት በዋንኛነት ተጠቃሽ ነው፤ ነገን ተስፋ አድርገን ለጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ መነቃቃትም ፈተና የሆነ ነው።
በፖለቲካ ፓርቲ እና በነፃ አውጪነት ስም ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት እንደ ሀገር ብዙ ያልተገቡ ዋጋ ለመክፈል በተገደድንባቸው የግጭት አዙሪቶች ውስጥ አልፈናል። በዚህም የተለያዩ ትውልዶች እስከ ተስፋቸው ተገንዘው ተቀብረዋል። በመቃብራቸው ላይ የመሠረትነውም የፖለቲካ ሥርዓት የቀጣይ ትውልዶችን ተስፋ በልቷል።
በቅርቡ እንኳን የትግራይ ሕዝብ ብቸኛ ተወካይ ነኝ የሚለው ሕወሓት ከለውጡ ማግስት፤ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ሥልጣን ከመጣው መንግሥት ጋር የነበረውን ልዩነት በኃይል ለመፍታት የሄደበት ያልተገባ መንገድ ሀገርን፤ በተለይም የትግራይን ሕዝብ ያስከፈለው ዋጋ ምን ያህል የከፋ እንደሆነ ለማስታወስ አይከብድም።
ለራሱ፣ ለቤተሰቡ እና ለሀገር ተስፋ የነበረን ትውልድ ለሞት እና ለአካል መጉደል፤ ከፍተኛ መጠን ያለው የሀገር ሀብት ለውድመት ዳርጓል። መንግሥት ችግሩን ለዘለቄታው በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት በወሰደው ርምጃ ችግሩ በሠላም ስምምነት ባይፈታ ኖሮ ሊያስከትል ይችል የነበረውን ተጨማሪ ጥፋት መገመት ቀላል ነው።
ሕግ እና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓትን በማክበር ላይ የተመሠረተው የሠላም ስምምነቱ፤ ከሁሉም በላይ ለትግራይ ሕዝብ ሠላም ማስፈን ያስቻለ፤ ሕዝቡን ግጭት ከሚፈጥረው ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ ስደት እና የሥነልቦና ቀውስ የታደገ ነው። ሕዝቡ ስለ ልማት አስቦ እንዲንቀሳቀስ የተሻለ መነቃቃት የፈጠረም ነው።
የፌዴራል መንግሥት የሠላም ስምምነቱን ተከትሎ የወሰዳቸው ርምጃዎች፣ የትግራይ ሕዝብ ወደ ቀደመ ሕይወቱ እንዲመለስ ከማስቻል ባለፈ፣ ቀደምት ችግሮች ተመልሰው የግጭት ምንጭ እንዳይሆኑ ቀዳዳዎችን መድፈን ያስቻለ ነው። በሕወሓት በኩል የተስተዋሉ መጓተቶች እና ግጭት ቀስቃሽ ትንኮሳዎችን በሆደ ሰፊነት ያስተናገደም ነው ።
ለሠላም ካለው ቀናዒነት የመነጨው የፌደራል መንግሥት እንቅስቃሴ፤ ብዙ መጐረባበጦችን ለማለፍ የተገደደ ቢሆንም ፤ በተጨባጭ የትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ፍላጎት የሆነውን የሠላም እና የልማት ጥያቄ በመመለስ ሂደት ውስጥ የጎላ አስተዋፅዖ አበርክቷል። በሕዝቡም ዘንድ አዎንታዊ ምላሽ አግኝቷል ።
ይህም ሆኖ ግን ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በላይ የትግራይ ሕዝብ ብቸኛ ተጠሪ አድርጎ ራሱን የሚቆጥረው ሕወሓት ፤ በነዚህ ዓመታት ውስጥ በትግራይ ሕዝብ ስም በሀገርም ሆነ በትግራይ ሕዝብ ላይ የፈጠራቸው ምስቅልቅሎች ምን ያህል ሀገር እና ሕዝብን ዋጋ እንዳስከፈሉ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
ቡድኑ ትናንት በፈጠረው ስህተት የትግራይ ሕዝብ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ልጆቹን እስከ ተስፋቸው ለመቃብር ዳርጓል ፤ የዚህ ቡድን አንዳንድ የአመራር አባላት ከትናንት ስህተታቸው መማር አቅቷቸው ዛሬ ላይ በልጆቹ መቃብር ላይ ቆመው ለሕግ እና ለሕጋዊ ሥርዓት ደንታ ቢስ ስለመሆናቸው በተግባር እየዘመሩ ነው።
ይህ የቡድኑ አንዳንድ የአመራር አባላት እየሄዱበት ያለው መንገድ እንወክለዋለን የሚሉት የትግራይ ሕዝብ የዘመናት እና የትውልዶች ፍላጎት/ምኞት የሚጻረር፤ በየወቅቱ ለትግራይ ሕዝብ እውነተኛ ፍላጎት ሰማዕት የሆኑ የሕዝብ ልጆችን የመስዋዕትነት ዋጋ የሚያረክስ እና የሚያሳንስ ነው ።
ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሠ ቱሉ (ዶክተር) በይፋዊ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው “በየትኛውም የዓለም ጥግ ያለ ሀገር የሚመራው በሕግና በሥርዓት ነው። ሕግና ሥርዓት ከማንኛውም ሰው፣ ተቋም፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴ፣ ቡድን፣ ስብስብ በላይ ነው። እነዚህ ሁሉ ከሕግ እና ሥርዓት በታች ናቸው። ሕግና ሥርዓትን አክብሮ የማይንቀሳቀስ የትኛውም አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ የመጨረሻ ግቡ ጥፋት ነው፡፡
የሕወሓት ያለፉት ዓመታት የግትርነት ባሕሪም የዚሁ ምሳሌ ነው። ሕወሓት ደጋግሞ እንደመሸሸጊያ የሚያነሳው የፕሪቶሪያ ስምምነት የፌዴራል ተቋማትን አሠራሮች፣ ሕጎችና አካሄዶች በጥብቅ ሊያከብር ግዴታ ጥሎበታል። ቀድሞ የገባውን ግዴታ ሲሸራርፍ የመጣው ሕወሓት ዛሬ በተጨባጭ ተግባር ደምስሶታል፡፡ ድርጊቱ የትግራይ ሕዝብ ያገኘውን አንጻራዊ ሠላም እንደመንጠቅ ይቆጠራል፡፡ አንዴ፣ ሁለቴ፣ መሳሳት ያለና የነበረ ነው፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ተመሳሳይ ስህተት ሦስቴ መፈጸም ግን የመጨረሻው የጥፋት መንገድ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ብቻኛው ተጠያቂ ራሱ ይሆናል” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ሕወሓት እየጓዘበት ያለው ከሕግ እና ከሕጋዊ ሥርዓት ያፈነገጠ መንገድ በየትኛውም መመዘኛ ትክክል ያልሆነ፤ ከቀደመ ስህተት ያልተማረበት፤ ተጨማሪ ክፍተት እና ስህተቱ ለሚያስከፍለው ያልተገባ ዋጋ ደንታ ቢስ የመሆን ማሳያ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ከትግራይ ሕዝብ ፍላጎት በፍጹም ያፈነገጠ፤ ሕገወጥነት ከሚፈጥረው ሁከት እና ግርግር ለማትረፍ የሚደረግ ጥረትም ነው!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9 /2016 ዓ.ም