መንግሥት ለሀገሪቱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎችን ይዞ የመጣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በቅርቡ ወደ ሙሉ ትግበራ ማስገባቱ ይታወቃል:: ማሻሻያውን ተከትሎም ብሄራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ስርአት ማሻሻያ አውጥቷል:: የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ስርአት ማሻሻያም በውጭ ምንዛሬ ግብይት ላይ የነበረውን ስር የሰደደ ችግር ለመፍታት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ታምኖበታል:: በማሻሻያው መሰረት የውጭ ምንዛሬ ከብሄራዊ ባንክ እጅ ወጥቶ በገበያ የሚመራበት ሁኔታ ተፈጥሯል::
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እና እሱን ተከትሎ የወጣው የውጭ ምንዛሬ ግብይት አስተዳደር ስርአት ማሻሻያ ትልቅ የሚባሉ ውሳኔዎች መሆናቸውን የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም አስታውቀዋል፤ ባለሙያዎቹ ትግበራው የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ስርዓት በጠበቀ መልኩ በጥንቃቄ መመራት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል:: መንግሥትም የማሻሻያውን ትግበራ ተከትሎ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በማመን ችግሮቹን ለመፍታት የበኩሉን እንደሚሰራ ባረጋገጠው መሰረት እየሰራ ነው::
ማሻሻያው ወደ ትግበራ እንደገባ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች መታየት ጀምረዋል:: የዋጋ ጭማሪ፣ ምርት መደበቅና የመሳሰሉት በስፋት ታይተዋል:: ምንም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት በሌለበት ሁኔታ ሀገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች ላይ ሳይቀር የዋጋ ጨማሪ ተከስቶ ህብረተሰቡን እየጎዳ ይገኛል::
ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም ይህንኑ አረጋግጠውልናል:: ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ያገኘነው መረጃም ይህንኑ አመላክቶናል::
የየካ ክፍለከተማ ወረዳ 01 /ፈረንሳይ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ/ ነዋሪዋ ወይዘሮ ካሰች መኩሪያ ማሻሻያው ወደ ትግበራ ከመግባቱ በፊት አንድ ኪሎ ጤፍ 130 ብር ይሸጥ እንደነበር ያስታውሳሉ:: እሱም ይሁን ብለን እየገዛን ነበር ያሉት ወይዘሮ ካሰች፣ አሁንም ዋጋው ጨምሮ 170 ደርሷል፤ ከቀነሰ ብዬ መግዛቱን ትቼዋለሁ ብለዋል:: የዋጋ ንረቱ በዚሁ ከቀጠለ እና ቁጥጥር ካልተደረገበት ቀጣዩ ጊዜ እንደሚያሰጋቸው ይገልጻሉ ::
ማሻሻያው መደረጉን ተከትሎ በተለያዩ ምርቶች ላይ አላግባብ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ እርምጃ እየወሰድኩ ነው ማለቱን ጠቅሰን፤ ይህን ተከትሎስ ምን ለውጦች አሉ ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄም የጤፍ ዋጋ በአንዳንድ ወፍጮ ቤቶች እና አቅራቢዎች በፊት ከነበረው ትንሽ የቀነሰበት ሁኔታ እንደነበር ተናግረው፣ በፊት ይሸጥበት ከነበረው ዋጋ ግን የጨመረ መሆኑን ጠቁመዋል:: ወይዘሮ ካሰች በሌሎች ምርቶች ላይ የሚታየውን የዋጋ ጭማሪ ለማረጋጋት ቁጥጥሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል ::
ሌላኛዋ የሁለት ልጆች እናት ወይዘሮ ወይንሸት አይቼው በበኩሏ፤ በየእለቱ የምትጠቀማቸውን ምርቶች ለመግዛት ሁልጊዜ ወደ ምትገዛበት ሱቅ ብትሄድም አንድ ሺህ 50 ብር ይሸጥ የነበረው የአምስት ሊትር ዘይት ዋጋ 1500 ብር ሆኖ አግኝታዋለች:: እንደ ምስር ፣ ሩዝ፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ እና ሌሎች ምርቶች እንዲሁ ከሌላው ጊዜ በተለየ የዋጋ ጭማሪ ማሳየታቸውን ታስታውሳለች:: ‹‹ ምናልባት ሌሎች ሱቆች ላይ ሊቀንስ ይችላል ብዬ ብሄድም አንዳንድ ሱቆች ላይ እንዲያውም ምርቶቹ የሉም ብለው መልሰውኛል›› በማለት አብራርታለች ::
የዋጋ ማሻሻያውን ተከትሎ በአንዳንድ የንግድ ሱቆች ላይ የተስተዋለው ይህ የዋጋ ጭማሪ ወደ ነበረበት እንዲመለስ በተደረገው ቁጥጥር ለውጦች የመጡበት ሁኔታ እንዳለም ወይዘሮ ወይንሸት ገልጸለች:: ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ የነበረው ዘይት አንዳንድ ሱቆች ላይ ዋጋው ወደ ነበረበት መመለሱን ጠቅሳለች :: የዋጋ ጭማሪውን ለመግታት ቁጥጥር ከማድረግ ባለፈ በየአካባቢው በሚገኙ የሸማች ሱቆች ላይ ምርቶች ቢቀርቡ የተሻለ መሆኑን ወይዘሮ ወይንሸት አመልክታለች::
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከመደረጉ አስቀድሞ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመግዛት በተለያዩ የአዲስ አበባ ከተሞች የቅዳሜ እና እሁድ ገበያ በሚል አገልግሎት የሚሰጡ ቦታዎች መሸመት የምታዘወትረው ወይዘሮ ሰናይት ሹምዬ በበኩሏ ‹‹ ከዚህ በፊት 45 ብር እና 50 ብር ይሸጥ የነበረው ሽንኩርት በእጥፍ ጨምሮ 120 ብር ገብቷል›› ብላለች:: 30 ብር እና 25 ብር የነበረው ቲማቲምም እንዲሁ 70 እና 90 ብር እየተሸጠ መሆኑን አስታውቃለች::
በዋጋ ጭማሪው ምክንያት መግዛት የምትፈልገውን የምርት መጠን ወደ ግማሽ ለማድረግ እንደወሰነችም ትገልጻለች:: ‹‹ በቅዳሜ እና እሁድ ገበያ ላይ ከዚህ በፊት እሁድ ምሽት ድረስ በቂ አቅርቦት ነበር፤ አሁን ግን እነሱም አንዳንድ አትክልቶችን በጊዜ ጨርሰናል ›› በማለት በእነዚህ ስፍራዎች ላይ የአቅርቦት እጥረት መኖሩንም ጠቅሳለች:: በተለያዩ የንግድ ሱቆች ላይ ገበያውን ለማረጋጋት እየተደረገ በሚገኘው ክትትልና ቁጥጥር አስቀድሞ እንደነበረው ባይሆንም አሁን ላይ ሽንኩርትም 90 ብር እየተሸጠ እንደሆነ ገልጻለች ::
በቀጣይ ይህን መሰሉን የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠር ይበጃል ያለችውን መፍትሄ ሰንዝራለች:: ‹‹ ቁጥጥሩ ሰው በብዛት በሚኖርበት አካባቢ በሚገኙ ሱቆች ላይ ቢደረግ መልካም ነው፤ ምክንያቱም እኛ በየቀኑ የምንጠቀመው ከዚያ ነው›› ስትል ገልጻ፤ በቅዳሜ እና እሁድ ገበያ ላይ በቂ ምርቶች እንዲቀርቡ ማድረግ እንደሚገባም አስታውቃለች:: ለእዚህም የሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቃለች::
የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ‹‹ አብዛኛው ነጋዴ ህግና ሥርዓትን ተከትሎ እንደሚሰራ ጠቅሰው፣ ህገወጥ ነጋዴዎች ግን የተደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ በገበያው ላይ ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ሲያደርጉ ይስተዋላል ብለዋል:: ቢሮው እነዚህን ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች ለመቆጣጠር ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል::
እሳቸው እንዳሉትም፤ ማሻሻያውን ተከትሎ በህገወጦች የተደረገውን የዋጋ ጭማሪ ተከትሎ ቢሮው ባደረገው የቁጥጥርና ክትትል ስራ የተለያዩ የንግድ ሱቆች በተለያዩ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ አድርገው ተገኝተዋል:: የዋጋ ጭማሪ ባደረጉት ላይም እርምጃ እየተወሰደባቸው ነው::
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ የንግድና ግብይት እንቅስቃሴው ህግ እና ሥርዓትን የተከተለ እንዲሆን የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል:: ቢሮው በህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተው ተገኙ ባላቸው 769 የሚጠጉ የንግድ ሱቆች ላይ እርምጃ ወስዷል :: ከእነዚህ ውስጥም 340 የሚሆኑት አለአግባብ ዋጋ በመጨመር የተስተዋለ የንግድ እንቅስቃሴ ሲሆን፣ በዚህም ሱቆቹ እንዲታሸጉ ተደርጓል :: 423 የሚደርሱ ምርትን በማሸሽ፣ በመደበቅ እና የዋጋ ዝርዝር ባለመለጠፍ በገበያው ላይ እጥረት እንዲፈጠር ሲያደርጉ በቁጥጥር ስራው ተደርሶባቸዋል::
ቢሮው ከማዕከል እስከ ወረዳ በመቀናጀት ጠንካራ የሆነ ክትትል እና ቁጥጥር እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል ::
ከዋጋ ጭማሪው በተጨማሪ አንዳንድ መደብሮች ደግሞ ምርቶች የሉም የሚል ምላሽ እየሰጡ መሆናቸውን በመጥቀስ ይህን ችግር ለመፍታት እየተከናወነ ስላለው ተግባር የጠየቅናቸው የኮሙኒኬሽን ኃላፊው ‹‹ይህንንም ችግር ለመፍታት በከተማው ላይ የምርት መሸሸግ ሊደረግባቸው ይችላሉ በተባሉ መጋዘኖች ላይ ፍተሻ እየተደረገ ይገኛል›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል:: ቢሮው በሚያደርገው የክትትልና ቁጥጥር ስራ በአዲስ አበባ ዙሪያ ወደሚገኙ ከተሞች ምርቶችን የማሸሽ ሁኔታ መኖሩን ገልጸው፣ ይህንንም ችግር ለመፍታት ከኦሮሚያ ክልል እና ከክልሉ የሸገር ሲቲ አስተዳደር ጋር በመሆን ፍተሻዎች መደረጋቸውንም አስታውቀዋል:: በተደረገው ፍተሻም በቡራዩ በሶስት መጋዘኖች ላይ ክምችት ተገኝቶ እንዲታሸግ ተደርጓል ብለዋል::
ይህ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለአንዳንዶች አዲስ ሃሳብ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቢሮው በንግድ ሥርዓት ውስጥ ያሉ ህጎችን አክብረው በማይሰሩ ላይ እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የታለመለትን አላማ እንዲያሳካ ቢሮው ከሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ነው፤ በተለይ በምርት አቅርቦት ላይ እየሰራ ይገኛል:: ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ፣ ከኢትዮጵያ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመሆን አዳማ ፣ ጅግጅጋ እና ሰመራ ከተሞች ላይ በተለያየ ምክንያት ቆመው የነበሩ ምርት የጫኑ መኪኖች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ እየተደረገ ነው:: በዚህም ባለፈው ሳምንት 273 ኩንታል ዱቄት ፣ ሩዝ ፣ እንዲሁም ዘይት እና ስኳር የጫኑ ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ ተደርጓል :: የተለያዩ ብራንዶች ያሉት 20 ሺህ ካርቶን ዘይት ባለ 5 ሊትር እንዲሁም በመርካቶ ገበያ እንዲራገፍ ተደርጓል ::
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የንግድ ስራው ህግና ሥርዓቱን ተከትሎ እንዲካሄድ ለማስቻል እንዲሁም በሌላ በኩል የምርት አቅርቦት በበቂ ሁኔታ እንዲኖር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት እየሰራ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል::
ማህበረሰቡም በህገ – ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ በሚገኙ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎችን እንዲደግፍ ጠይቀው፣ ህብረተሰቡ ቢሮው ህገ- ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር በሚሰራው ስራ እንዲሳተፍ 8588 ነጻ የስልክ መስመር ይፋ አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል ::
በተለያዩ የንግድ ሱቆች በዘይት እና ሌሎች ምርቶች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች እና ምርት በማሸሽ እና በመደበቅ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ አሁንም ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው ያሉት ኃላፊው፤ ምግብና መጠጥ በሚያቀርቡ የገበያ ማዕከላት ላይ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል:: ህብረተሰቡ የከተማ አስተዳደሩ ባስገነባቸው የገበያ ማዕከላት በመሄድ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት እንደሚችልም አቶ ሰውነት ጠቁመዋል ::
የምርት አቅርቦት ከተማ ውስጥ በስፋት እንዲኖር በማድረግ እና ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በመቆጣጠር ግንዛቤዎችን በማስፋት እና ህገወጥ እንቅስቃሴዎች ሲመለከት ህብረተሰቡ የሚጠቁምባቸውን መንገዶች በመፍጠር የገበያ አለመረጋጋቱን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል ::
ይህ በእንዲህ እንዳለ የማክሮ ኢኮኖሚውን ማሻሻያውን ምክንያት በማድረግ የንግድ ሥርዓቱን በማዛባት ወደ ሕገወጥነት የገቡ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ እና የተመቻቸላቸውን ሕጋዊ የአሠራር ሥርዓት ተከትለው እንዲተገብሩ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አሳስቧል።
የአገልግሎቱ ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤ ማሻሻያውን ምክንያት በማድረግ ወደ ሕገ ወጥነት በመግባት የንግድ ሥርዓቱን ለማዛባት የሚሞክሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምክንያት ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ እንደሌለም አስገንዝበዋል።
ማሻሻያው በተሟላ መልኩ ወደተግባር ሲገባ ጥቂት ስግብግብ ነጋዴዎች በከተሞችና በክልል ከተሞች የሚፈጥሩት ሕገወጥነት እየተስተዋለ መሆኑን በመጥቀስ፤ እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ድርጊቱ ምክንያታዊ መሠረት የሌለው መሆኑንም በመጥቀስ ተቀባይነትም እንደማይኖረው ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። መንግሥት የቁጥጥር ሥራ በማከናወን ሱቆችን የማሸግና ነጋዴዎቹም ላይ እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል። አብዛኞቹ ነጋዴዎች የማሻሻያውን አስፈላጊነት በመረዳት ሥርዓቱን ተከትለው የንግድ እንቅስቃሴን በማከናወን ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል። ትግበራው ፋይናንሻል መረጋጋት ለማምጣት፣ የልማት ፕሮጀክት ውጤታማነትን እንዲሁም የመንግሥትን ገቢ ለማሻሻል ያለመ መሆኑንም አመልክተዋል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም