ፍለጋውድ ሽቶ ወይንስ ቆንጆ ሽቶ ?

ሽቶዎች በተለያዩ ሀገራት በተለያየ መንገድ ተሰርተው ለገበያ ይቀርባሉ። ፈረንሳይ በዚህ በእጅጉ ትታወቅበታለች። ለመጀመሪያ ጊዜ ሽቶን በመጠቀም የሚታወቁት ግብጽ እና ጥንታውያን ቻንያውያን መሆናቸውን መረጃዎችም ይጠቁማሉ። ሽቶ ከ17ተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንደነበርም እነዚሁ መረጃዎች ይጠቁማሉ፤ እነዚህ ሽቶዎች ደረጃ እና ዓይነት አላቸው፤ ዋጋቸውም እንዲሁ ይለያያል።

ሽቶን አብዝቶ ከመውደድ አንስቶ ከሌሎች ሀገሮች አምጥታ በመሸጥ ወደ ንግዱ ዓለም የገባቸው መሠረት ካሳ እንደምትለው፤ ሰዎች የሚቀቡት ሽቶ መለያ ጠረናቸው እስከሚሆን ድረስ በቅርባቸው ባሉ ሰዎች በሽቷቸው የሚታወቁበት ሁኔታ አለ። በተገኙበት ቦታም መልካቸው ሳይታወቅ በሽቶው ብቻ ማን እንደሆኑ እስከ ማወቅም ሲደረስ ይስተዋላል። ይህ ሊሆን የሚችለው እነዛ ሰዎች ለዓመታት አንድ ሽቶ ብቻ ምርጫቸው አድርገው ሲጠቀሙ ነው።

የሽቶ አድናቂዎች እና ወዳጆች ከመደርደሪያቸው ላይ ሽቶ በፍጹም የማይጠፋ አንድ እና ከዛም በላይ ሽቶ ያላቸው ናቸው። ለእለት ተዕለት ብለው የለዩዋቸው እና የክት ብለው የሚያስቀምጧቸው ሽቶዎችም አሏቸው። ለሽቶ ምንም ያህል ገንዘብ ቢያወጡ አይቆጫቸውም። በርካታ ሽቶዎች ቢኖራቸውም እንዲሁ አይጠሉም። ሽቶ በጣም ከመውደዳቸው የተነሳም ላይበረክትላቸው ይችላል፤ እነዚህ የሽቶ አፍቃሪዎች የሚጠጣ ሽቶ ቢኖር ሲሉ የሚናገሩበት ሁኔታም ያጋጥማል።

የእነዚህ ሽቶ ወዳጆች ሌላኛው ገጽታ ደግሞ ሰዎች የተቀቡት ሽቶ ምን ዓይነት እንደሆነም ማወቅ ይችላሉ። ሽቶውን የተቀባው የማያውቁት ከሆነና የተቀባውም የሚወዱትን ሽቶ ከሆነም ከማድነቅ ወደኋላ አይሉም። እነዚህ የሽቶ ወዳጆች አንድን ሰው በሚያዘወትረው የሽቶ ዓይነት ወይንም ጠረን መለየትም ይችላሉ።

‹‹ ወደ ሥራው ከመግባቴ በፊት ሽቶ በጣም እወድ ነበር፤ ከዛ በኋላ ነው ለምን እራሴ እያመጣሁ አልሸጥም ብዬ መሸጥ የጀመርኩት። ›› የምትለው መሠረት፣ ብዙ ዓይነት ሽቶዎችን ከተለያዩ ሀገራት በማምጣት ለገበያ ታቀርባለች።

አንዳንዶች ትልልቅ ስም ያላቸው ሽቶዎች ጥሩ ጥራት እንዳላቸው ተደርጎ ሊታሰብ ይችላል ይላሉ። መሠረት ግን ትልልቅ ስም ያላቸው ሽቶዎች ሁሉ ጥሩ ላይሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ እንዳለ ትናገራለች፤ አንድ ሽቶ ደረጃውን የጠበቀ ነው እንዲባል ቢያንስ ሶስት መገለጫዎችን በመሠረታዊነት ማሟላት እንደ አለበት ከልምዷ ተነስታ ታብራራለች።

ትልልቅ ስም ያላቸው ሽቶዎች ከሚጋሩት መገለጫ አንዱ ሽቶውን ከተቀባነው በኋላ ቆዳችን ላይ የሚቆይበት የጊዜ ርዝማኔ ነው ስትል ጠቅሳ፣ ሽቶዎች ጥራት ካላቸው ግብዓቶች በሚሰሩበት ጊዜ መዓዛቸው ቆዳችን ላይ ረዘም ላለ ጊዜ ይቆያል ነው የምትለው። ስለዚህ አንድን ሽቶ ጥራቱን የጠበቀ ነው፤ አይደለም የሚለውን ለማረጋገጥ ተቀብተውት የሚቆይበትን ጊዜ ማየት እንደሚያስፈልግ መሠረት ጠቅሳለች። ‹‹ የሽቶው መዓዛ ለበርካታ ሰዓታት፣ ከአንድ ቀንም በላይ አብሮን የሚቆይ እና ለአፍንጫም የማይረብሽ ከሆነ ጥሩ ሽቶ ነው ማለት ይቻላል›› ስትል ትገልጻለች።

በተለምዶ ውስብስብ መዓዛ ያላቸው ሽቶዎች አንድ መዓዛ ብቻ ካላቸው ሽቶዎች የበለጠ ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው ይባላል። ይህ ግን ሁልጊዜ ትክክል ላይሆን እንደሚችል ማስታወስ ተገቢ ነው። ውስብስብነትን ከሽቶ ጥራት ጋር ማያያዛችን በቅንጦት ብራንዶችና በሀሰተኛ ብራንዶች መካከል ያለውን ልዩነት ለመጥቀስም ጭምር መሆኑንም ልብ ይላሉ። ብዙ ጊዜ የቅንጦት ሽቶዎች የሚጠቀሟቸው ጥራት ያላቸው ግብዓቶች በከፍተኛ ጥናትና የጥራት መለኪያዎች ውስጥ አልፈው ስለሚመጡ ደረጃቸውን የጠበቁ የሚሆኑበት እድል ሰፊ ነው።

ሽቶዎች ከትንሽ እስከ ትልቅ በተለያየ መጠን ተዘጋጅተው ለገበያ ይቀርባሉ። ሰዎች ሽቶ ከመግዛታቸው በፊት እዛው ተቀብተው እንዲሞክሩት ይደረጋል፤ አልያም ደግሞ ለሙከራ ተብሎ በትንሽ ብልቃጥ የተዘጋጀ ሽቶ ለደንበኞች ይቀርባሉ።

ሽቶን ለማዘጋጀት ለዚህ ተብለው የተለዩ ኬሚካሎች፣ አበባዎች ፣ ፍራፍሬዎች እና ግብዓቶች ያስፈልጋሉ። በርካታ ዓይነት ሽቶዎችን በማምረት የሚታወቁ ብራንዶች ሲኖሩ፣ ለወንዶች እና ሴቶች ተብለው የሚለዩ ሽቶዎችም አሉ። ሰዎች በአጠቃላይ ያላቸው የቆዳ ባህሪ የሚለያይ ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ በጾታ ባይለይም በአብዛኛው ሴቶች ለስለስ ያለ እና ጣፋጭ ጠረን ያለው ሽቶን ይመርጣሉ፤ ወንዶች ደግሞ ጠንከር ያለ መአዛ ያለው ሽቶ ይመርጣሉ።

የሽቶ ዋጋም እንደ ብራንዱ ዓይነት እንደሚለያይ የምታነሳው ወይዘሮ መሠረት የሚዘጋጁበት መንገድ ለሚኖራቸው ዋጋ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው የምትለው። አንደኛ ደረጃ ሁለተኛ ደረጃ ተብለው በገበያው ላይ ይገኛሉ፤ ከአንድ መቶ ሺህ ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ሽቶዎች በገበያ ላይ እንደሚገኙም ተናግራለች። ‹‹ብዙ ዓይነት ሽቶዎች ስላሉ ትክክለኛውን ሽቶ ተጠቃሚ ያልሆነን ሰው ለመለየት ያስቸግራል። ›› የምትለው ወይዘሮ መሠረት፣ እሷ ግን ሁሉንም ዓይነት ሽቶ እንደየሰዎች ምርጫ በሱቋ ውስጥ ትይዛለች። በጣም ውድ የሚባሉ ሽቶዎችን የሚጠቀሙ ሰዎች ጥቂት መሆናቸውን ተናግራ፣ እነዚህን መሰል ሽቶዎች ከማምጣቷ በፊት ከደንበኞቿ ግማሽ ክፍያ እንደምትቀበልም ነው ያስታወቀችው።

የፋሽን ኢንዱስትሪው ሁሌም ቢሆን ሽቶ ለማምረት ጥልቅ የሆኑ ጥናቶችን ያካሂዳል። አንድ ሽቶ ለገበያ ከመቅረቡ በፊት በቆዳ እና በሌሎች አካላት ላይ ጉዳት አለማድረሱ ለማረጋገጥ አስፈላጊ የደህንነት መመዘኛዎችን ማለፍ ግድ ይለዋል።

ሽቶን አብዝተው የሚወዱ እና የሚጠቀሙ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል ቀጥታ ከቆዳቸው ጋር አገናኝተው ሲቀቡት አንዳንድ እንደ ሽፍታ ያሉ ምልክቶች የሚያጋጥሟቸው ሰዎችም አሉ፤ እነዚህም በጥንቃቄ በልብሳቸው ላይ ይቀባሉ። ሽቶዎች በተለያየ መንገድ ለገበያ የሚቀርቡ ሲሆን፣ አንደኛ ደረጃ የሆኑ ሽቶዎችን ለመግዛት በሽቶው ላይ ያለውን መግለጫ ወይንም ባርኮድ መመልከት ፣ የተሰራበትን ሀገር ማየት እና ሽቶው የተሰራባቸው ንጥረ ነገሮች ማንበብ ያስፈልጋል።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You