የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን መገለጫና ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የአየር መንገድ ኢንዱስትሪም በመሪነት ሚናው ይታወቃል። በዓለም አቀፍ ደረጃም የበረራ አድማሱን በማስፋት አገልግሎቱንም የተቀላጠፈና የዘመነ በማድረግ ዝናን አትርፏል።
አየር መንገዱ በእዚህ ሁሉ የላቀ ተግባሩ በከፍታ ላይ ከፍታን እየደረበ ይገኛል። የበረራ አድማሶቹን በማስፋት፣ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመጠቀም፣ የአውሮፕላኖቹን ብዛት በየጊዜው በማሳደግ፣ የአውሮፕላን ባለሙያዎችን በማሰልጠን፣ የሌሎች ሀገሮችን አውሮፕላኖችን ጨምሮ በመጠገን፣ ወዘተ ዝናው በዓለም የናኘ ነው።
ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት በርካታ እውቅናዎችን በማግኘትም ይጠቀሳል። የቅርብ የሆኑትን እንኳ ብንጠቅስ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ዓለም በሩን ዘግቶ ተቀምጦ እያለ በዓለም አቀፍ ደረጃ መንገደኞችንና መድሃኒቶችን በማጓጓዝ የሰው ልጅን ሕይወት በመታደጉም ይታወሳል። በዚህም ሠብዓዊ ተግባሩ በቅርቡ ዓለም አቀፍ እውቅና ተቸሮታል። አየር መንገዳችን በአሜሪካ ላደረገው አገልግሎትም የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ፊርማ ያረፈበትን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የስኬታማነት ሽልማትን በቅርቡ በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ተበርክቶለታል።
አየር መንገዱ አሁንም ይህን ከፍታውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችሉትን ተግባሮች ማከናወኑን ቀጥሏል። እየጨመረ የመጣውን የመንገደኞች ብዛት በሚገባ ማስተናገድ የሚያስችለውን ግዙፍና ዘመናዊ የአውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት እያከናወነ ያለው ተግባርም ይህንኑ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቢሾፍቱ ቅርብ ርቀት ላይ አቡሴራ በሚባል አካባቢ ለሚያስገነባው ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ የዲዛይን ሥራና የማማከር አገልግሎት ከሚያካሂደው ‹‹ዳር›› ከተሰኘው ታዋቂ የውጭ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል። በስድስት ቢሊዮን ዶላር የሚገነባው ይህ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ እየጨመረ የመጣውንና በቀጣይም የሚጨምረውን የአየር መንጉዱን ተጓዦች ብዛት ለማስተናገድ እንዲሁም ሀገሪቱን የአፍሪካ ዋና የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ማእከል ማድረግን ያለመ ነው።
ኩባንያው በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በኡጋንዳ ሌሎች ሀገራት የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ዲዛይን በመሥራትና በማማከር አገልግሎት የሚታወቅ ሲሆን፣ የዲዛይን ሥራውን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሠርቶ የሚያስረክብ ይሆናል፤ በግንባታ ተቋራጭ መረጣ ላይ በሚካሄደው ሥራም አማካሪ ሆኖ ይሠራል። ከዚህ ሁሉ መረዳት የሚቻለው የግንባታ ፕሮጀክቱ በከፍተኛ የኤክስፐርት ደረጃ እና አቅም እንደሚካሄድም ነው።
የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ ፕሮጀክት በሁለት ምዕራፍ የሚካሄድ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ በአመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል የግንባታ ፕሮጀክት ይካሄድበታል። ግንባታውም በአምስት ዓመታት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ተደርጎ ነው የሚካሄደው። ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚካሄድበትም ነው።
ሁለተኛው ምዕራፍ እጅግ ሰፊና የአየር ማረፊያውን መንገደኞች የማስተናገድ አቅም በዓመት ወደ 100 ሚሊዮን የሚያሳድግ ይሆናል። የአየር ማረፊያውን ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጋር የሚያስተሳስሩ የባቡርና የመንገድ መሠረተ ልማቶችን ጨምሮ ሌሎች ሰፋፊ ተያያዥ ሥራዎች የሚካሄዱበትም ይሆናል።
አየር መንገዱ ይህን ግዙፍ ፕሮጀክት ለመገንባት መንቀሳቀስ ከጀመረ ቆይቷል፤ አሁን ወደ ዋናው ግንባታ ለመግባት ወደሚያስችለው ወሳኝ ሥራ ገብቷል። የዚህ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ወደ ትግበራ እየተሸጋገረ መምጣት በራሱ የአየር መንገዱን ጥንካሬ፣ በከፍታ ላይ ከፍታ የመደረብ ህልሙን እውን ለማድረግ ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነ ይጠቁማል።
አየር መንገዳችን በከፍታ ላይ ከፍታ እየደረበ የመጣው ግን ነገሮች አልጋ ባልጋ ሆነውለት እንዳልሆነም መታወቅ ይኖርበታል። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተቋሙን ስም ለማጥፋት ሙከራዎች ተደርገውበታል። ለእነዚህ ሙከራዎች ጆሮም ሳይሰጥ ሥራና ሥራውን ብቻ እየተመለከተ ‹‹ውሾቹ ይጮኻሉ ግመሉ ግን መንገዱን ቀጥሏል›› እንደሚባለው አየር መንገዱ ለላቀ አገልግሎት የሚያበቁትን ግዙፍ ተግባራት እያከናወነ ስሙንና አቅሙን በእጅጉ እየገነባ ይገኛል።
አየር መንገዱ ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች እየተጠቀመ፣ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን እያፈራ የሀገር ውስጥ በረራውን እያሰፋ በአፍሪካም ሆነ በመላው ዓለም ተወዳዳሪነቱን ወደ ላቀ ደረጃ እያደረሰ ነው ለእዚህ ከፍታ የበቃው። በቀጣይም የሚሆነው ይሄው ነው። ምከንያቱም ኢትዮጵያን ኢትዮጵያውያንን የሚመጥነው ሁሌም ከፍ ማለት ነውና!
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም