የሀገራችን የንግድ ሥርዓት የሚገራው አጥቶ ከመጣበት የተበላሸ መንገድ የተነሳ ለዜጎች ፈተና ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል ። ንግዱ የሆነ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር ኮሽታዎች ከሚፈጥሩት ችግር ባልተናነሰ ሀገር እና ሕዝብን ያልተገባ ዋጋ በማስከፈል በብዙ መልኩ የተበላሸ ትርክት ባለቤት ነው።
በአንድ በኩል የንግድ ሥርዓቱን የሚቆጣጠር ጠንካራ ሀገራዊ ተቋም መፍጠር አለመቻሉ፤ በሌላ በኩል ሀገራዊ የሞራል እሴቶቻችን እየተሸረሸሩ መሄዳቸው ፣ እንደሀገር በንግዱ ዘርፍ ኃላፊነት የማይሰማቸው ስግብግብ ነጋዴዎች እንዲበራከቱ ፣ በዚህም ዜጎች ላልተገባ ችግር እንዲዳረጉ አድርጓል ።
“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው እነዚህን ነጋዴዎች ከዓለም አቀፍ ውድድር ለመታደግ በመንግሥት በኩል ሲወሰድ የነበረው የፖሊሲ ከለላ ፤ ከነጋዴዎቹ ባህሪ አንጻር የተጠበቀውን ውጤት ከማምጣት ይልቅ ፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማባባስ ፤ ሕዝብን ለበለጠ የኑሮ ውድነት አደጋ ተጋላጭ አድርጓል።
ችግሩ የንግድ እንቅስቃሴን ከማዛባት ፤ ለሀገራዊ የኑሮ ውድነት ምንጭ ከመሆን ባለፈ ፤ አጠቃላይ በሆነው የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ትልቅ ፈተና ሆኗል። እንደሀገር ለጀመርነው ለውጥም ተግዳሮት በመሆን ለለውጡ እና ለለውጥ ሃይሉ ፈተና ከሆነ ውሎ አድሯል።
በዘርፉ የሚስተዋለው ሥርዓት አልበኝነት ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ሸቀጦች ጥራትም ላይ ሆነ በዋጋ ስሌት ላይ እየፈጠረ ያለው ተጽእኖ ሀገርን እንደሀገር ለብዙ ኪሳራ እየዳረገ ነው ፤ ዜጎችም የሚፈልጉትን ሸቀጥ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደ አቅማቸው ማግኘት እንዳይችሉም ፈተና ሆኖባቸዋል።
ችግሩ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ገበያ መር በሆነ የዋጋ ስሌት ገበያ ውስጥ ለዘለቄታው እንዳይገኙ ከማድረግ ባለፈ ፤ በዘርፉ ተዋናዮች በሚፈጠሩ ሰው ሠራሽ ችግሮች ዜጎች በሸቀጦች ግብይት ዙሪያ የተረጋጋ መረጃ እንዳይኖራቸው ፤ ሁሌም በስጋት እንዲኖሩ አስገድዷቸዋል።
ከዚህም ባለፈ እንደሀገር በሚፈጠሩ መንገጫገጮች ወቅት ፤ የዘርፉ ተዋንያኖች ሃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ፤መንገጫገጮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚሄዱባቸው መንገዶች ዜጎችን ለተጨማሪ ችግር ከመዳረግ ባለፈ የእለት ተእለት ሕይወታቸው በምሬት እንዲሞላ አ ድርጓል።
በጥቂቶች እና በቤተሰቦቻቸው የሚዘወረው የሀገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ ፤ በተለያዩ ወቅቶች በመንግሥት በኩል ችግሩን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች ትርጉም የለሽ እንዲሆኑ አድርጓል። መንግሥት ችግሩን መፍታት አቅም የሌለው እስኪመስል ድረስ ፤ መንግሥትን ለብዙ ወቀሳዎች ዳርጓል።
ይህ እውነታ ዛሬም መንግሥት የሀገሪቱን የማክሮ ኢኮኖሚ ለመታደግ ተግባራዊ እያደረገው ባለው የፖሊሲ ማሻሻያ ወቅት በተጨባጭ እየተስተዋለ ይገኛል። እነዚህ ሕገወጥነትን የገበያ መርህ እድርገው የሚንቀሳቀሱ የዘርፉ ተዋንያኖች በአንድ ምሽት በሸቀጦች ላይ ያልተገባ ዋጋ በመጫን ዜጎችን እየፈተኑ ነው ።
ይህ ከትናንት ማንነታቸው የሚቀዳው ሕገወጥነታቸው ፤ መንግሥት ተግባራዊ እያደረገው ካለው የንግድ ሥርዓቱን በነጻ ውድድር የሚመራ (ሊበራላይዝድ) የማድረግ እንቅስቃሴ አኳያ በቀጣይ ረጅም እድሜ ይኖረዋል ተብሎ ባይታሰብም ፤ አሁናዊ ተጽእኖው ግን በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ይህንን ታሳቢ በማድረግ አሁን ላይ እየተወሰደ ያለው ርምጃ በራሱ የሚበረታታ ቢሆንም ፤ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት ለሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ስኬት አስተማሪ ፤ ሕገወጦችን ከማስጠንቀቅ እና ሱቆቻቸውን ከማሸግ ባለፈ ዘርፉን እየፈተነ ያለውን የተበላሸ አስተሳሰብ የሚገራ መሆን ይጠበቅበታል።
ርምጃው ከተለመደው የሌባና ፖሊስ ጨዋታ ወጥቶ ፤ ሕገወጦች የሕግን የበላይነት በአግባቡ እንዲረዱ ፤ በዚህም ለሕግ የበላይነት ተገዢ እንዲሆኑ የሚያስችል ፤ ዜጎችንም ከዚህ ዓመታትን ካስቆጠረ ከመጣ ሀገራዊ ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚታደግ ሊሆን ይገባል!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 5 / 2016 ዓ.ም