ጣልቃ ገብነቱ የአካባቢውን ሕዝቦች አንድነትና ትብብር ለመሸርሸር የመፈለግ ዝንባሌ ነው!

ሀገራት የየራሳቸው የሆነ ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ፍላጎቶች አሏቸው፤እነዚህን ፍላጎቶቻቸውን እውን ለማድረግ የተለያዩ አማራጮችን ይጠቀማሉ። ይህ ዘመናት ያስቆጠረ ዓለም አቀፍ አካሄድ ነው። ይብዛም ይነስ በዚህ ተጨባጭ እውነታ ውስጥ ያላለፈ ሀገርም ሆነ ማኅበረሰብ የለም።

እነዚህ ፍላጎቶች አሁን ያለውን ዓለም አቀፋዊ እውነታ በመፍጠር ሂደት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው። በተለያዩ ፍላጎቶች ዓለም በምትናጥበት በዚህ ዘመን እውነታው ፤ በብዙ መልኩ የአደባባይ ትርክት ከመሆን አልፎ፤በሀገራት መካከል ለሚኖሩ ግንኙነቶች በአሉታዊ እና በአዎንታዊ ምክንያትነት የሚጠቀስ ነው።

ከቀደመው ዘመን ጀምሮ ሀገራት እነዚህን ፍላጎታቸውን ተጨባጭ ለማድረግ ከኃይል ጀምሮ የተያዩ አማራጮችን ይጠቀማሉ፤ በአብዛኛው ዓለማችን ያስተናገደቻቸው ግጭቶች እና ጦርነቶች በአንድም ይሁን በሌላ ከዚሁ እውነታ ጋር የተሳሰሩ ናቸው። ወደፊትም ዓለማችንን የሚያሰጓት ግጭቶች እና ጦርነቶች ከዚህ ያለፈ ምክንያት ይኖራቸዋል ተብሎ አይታሰብም።

አሁን ላይ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ስለ ሰላም ከሚያዜመው ዜማ እና ስለ ሰላም ካለው መሻት አንፃር፤ፍላጎቶችን እውን በማድረግ ሂደት ከኃይል ይልቅ ውይይት እና ድርድር እንዲሁም ከዚህ የሚመነጭ ዘላቂ መፍትሄ በብዙ መልኩ ተመራጭ ነው። በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ ፍላጎትን የማሟላት መንገድም ተመራጭ ነው።

ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ እስካሁን በመጣንበት መንገድ ዓለምን ብዙ ዋጋ ካስከፈለው ያልተገባ ጣልቃ ገብነት መቆጠብ ፣ሀገራት እና የሀገራት ሕዝቦች የራሳቸውን እጣ ፈንታ በራሳቸው እንዲወስኑ ማበረታታት፤ይህን የማድረግ ነጻነታቸውን ማክበር እና ማስከበር ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነው ።

ባለንበት ዘመን ሞግዚት የሚፈልግ ሀገር እና ሕዝብ የለም፤ የትኛውም ሀገር እና ሕዝብ የሚጠቅመውን እና የሚጎዳውን ለመወሰን የሚያስችል የእውቀት ክፍተት የለበትም፤ ይህን ለማድረግም ሞግዚት አይፈልግም። የሞግዚትነት አስተሳሰብ የቱን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል፤ ከአፍሪካ እና ከአፍሪካውያን በላይ ምስክር ሊሆን የሚችል የለም።

ሞግዚትነት በወለደው ስንኩል አስተሳሰብ አፍሪካውያን የሰብአዊ ማንነታቸውን ፣ሀገራቸውን እና ተስፋቸውን ተነጥቀዋል። በገዛ ሀገራቸው ባይተዋር ሆነው ረጅም የግዞት ዘመን ለማሳለፍ ተገድደዋል። እውነታውን መቀልበስ ከፍ ያለ የህይወት መስዋዕትነት የጠየቀ መራራ ትግል እንዲያደርጉ ጠይቋቸዋል።

ከብዙ መራራ ትግል በኋላ ያገኙትን ነጻነታቸውን በአግባቡ ሳያጣጥሙት ፣ ልዩነቶችን በሚያሰፋ እና ወደ ግጭት በሚወስዱ የሴራ ትርክቶች ተጠልፈው ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ሰላም እና መረጋጋት አጥተው፣ በአንድም ይሁን በሌላ የራሳቸው ላልሆነ አጀንዳ ያልተገባ ዋጋ ሲከፍሉ ቆይተዋል፤ ዛሬም በተመሳሳይ መልኩ እየከፈሉ ያሉ የአህጉሪቱ ሕዝቦች ጥቂት አይደሉም።

አሁን ላይ አፍሪካውያን የሚያስፈልጋቸው በሴራ የተለወሰ የልዩነት ትርክት ሳይሆን ፣ ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት የሚያወጣቸው የጋራ ትርክት/ አጀንዳ ነው። ይህ ደግሞ በቀደመው ዘመን ብዙ ዋጋ የከፈሉበትን የነጻነት ትግል ሙሉ በማድረግ ፣ የሕዝባቸውን በልጽጎ የመገኘት ህልም እውን ማድረግ የሚያስችል ነው።

ከዚህ ውጪ በአፍሪካውያን መካከል ድብቅ የልዩነት የሴራ ትርክት በመፍጠር ፣ ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፍላጎቶችን ተጨባጭ ለማድረግ የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች ፣በየትኛውም ሁኔታ እና መመዘኛ ተቀባይነት የሚኖራቸው አይደሉም። በተለይም ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ለነጻነት ካላቸው ትልቅ ቦታና ከከፈሉለት ውድ መስዋዕትነት አንጻር ለምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት በሯን ፈጽሞ ክፍት እንደማታደርግ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ከዚህም በላቀ ድርጊቱ አፍሪካውያን ለሁለንተናዊ ነጻነታቸው ያካሄዱትን መራራ ትግል እና የከፈሉትን ከፍ ያለ መስዋዕትነት የሚያሳንስ ጭምር ነው።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ እና በሶማሌ ላንድ መካከል እየተደረጉ ያሉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች የሕዝቦቻቸውን አብሮ የማደግ እና የመልማት ፍላጎት ታሳቢ ያደረጉ፤ ከትናንት የሴራ እና የልዩነት ትርክት ወጥተው ለጋራ ተጠቃሚነት ያላቸውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ ያመላከቱ እና ለብዙዎች ምሳሌ ሊሆን የሚችሉ ናቸው።

ይህን ተከትሎ የሚሰሙ አፍራሽ ትርክቶችና ጣልቃ ገብነቶች፣ ለሶማሌ ሕዝብ ሞግዚት ሆኖ የመቅረብ ዝንባሌዎች ፣ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚታየውን አዲስ የትብብር መንፈስ ለማቀዛቀዝ ፣ከዚያም ባለፈ የአካባቢውን ሀገራት ሕዝቦች አንድነትና ትብብር ለመሸርሸር የመፈለግ ዝንባሌ እና ያልተገባ ጣልቃ ገብነት ነው።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You