ኢትዮጵያውያን በደስታ፣ በሀዘንም ሆነ በልዩ ልዩ ምክንያት በጋራ የሚቆሙባቸው ጠንካራ እሴቶች አሏቸው። ይህ ማህበራዊ መስተጋብር ከጥንት ጀምሮ የነበረ፤ ከትውልድ ትውልድ ተሻግሮ ዛሬ ላይ የደረሰ ጠንካራ ባሕላዊ አደረጃጀትም ያለው ነው።
በዚህ በጎ ምግባር አንድ ሰው ብቻውን ሊወጣው የማይችለውን ችግር በኢትዮጵያዊ እሴት በደቦ፣ በእቁብ፣ በእድር እና በሌሎችም መሰል አደረጃጀቶች ተረባርቦ መፍታት ሲቻል ተኖሯል፤ እየተፈታም ይገኛል። ይህን ሰው በበጎ ፍቃደኝነት የሚያቀናው ወገን ‹‹ነግ በኔን›› አስቦ ፈጥኖ ይደርስለታል። ለዚህ ነው መረዳዳትና መተባበር የኢትዮጵያውያን መገለጫ ሆኖ የሚጠቀሰው።
በችግር ውስጥ የሚማቅቁ ሰዎችን የተመለከቱ አንዳንድ ኢትዮጵያውን ደግሞ ይህ በጎ ተግባር በማስፋት የበጎ አድራጎት ማህበር አቋቁመው በመሥራት አያሌ ዜጎችን ታድገውበታል፤ እየታደጉበትም ይገኛሉ። የበጎ አድራጎቱ ተግባር ግን በአብዛኛው በባሕላዊ መንገድ ሲካሄድ ነው የሚስተዋለው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን የቆየ እሴት ከባሕላዊ አደረጃጀት ባሻገር ዘመናዊና ተቋማዊ ቅርፅ እንዲኖረው ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ይገኛል። በተለይ በተናጠል የማይቻልን ጉዳይ በቀላል ወጪና በተባበረ ክንድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳካት የሚያስችለው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ እየሰራ መሆኑን በተለያየ ጊዜ በሚወጡ መረጃዎች ይፋ አድርጓል።
በአዲስ አበባ ከተማ በመንግሥት የሚመራ የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽንም ተቋቁሞ እየሰራ ነው። በተለይ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ውስጥ በበጎ ሥራ ዙሪያ አያሌ ሥራዎች ሲከወኑ ተመልክተናል። በርካታ ወጣቶችም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አምባሳደር በመሆን አቅመ ደካሞችንን ሲያግዙ ቆይተዋል፤ አሁንም እያገዙ ይገኛሉ።
የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው ሀገረኛ ዓምድ ላይ ከላይ ያነሳነውን ማህበራዊ ጉዳይ በስፋት ለመዳሰስ ወድዷል። በተለይ ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር እየተከናወነ ባለው ተግባር የተገኙ ውጤቶች ምን እንደሚመስሉ ይቃኛል። ለዚህ ጉዳይ መንደርደሪያ እንዲሆነን ከሁለት ሳምንት በፊት በተደረገ አንድ ጥናታዊ መድረክ ላይ የተቃኙ ሃሳቦችን እናነሳለን፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽነርን ባነጋገርንበት ወቅት ያገኘናቸውን ሃሳቦችንም ይዘናል።
በቅርቡ የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ ለአዲስ አበባ ማህበረሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ያካሄዳቸውን ሁለት የጥናት ውጤቶች አስረክቧል። ጥናቶቹ በዋናነት በበጎ ፍቃድ አገልግሎትና በማህበረሰብ ተሳትፎ የተገኙ ውጤቶችና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸው በመድረኩ ላይ ተገልጿል።
በዚህም በማህበረሰብ ተሳትፎ የተሰሩ ሥራዎች የመዲናዋን ሰላም ለማስጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የተደረገው የጥናት ውጤት ማሳየቱ ተመልክቷል። በተለይ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በደህነት ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ኑሮን ለማቃለል ከፍተኛ ሚና መጫወቱን የጥናቱ ውጤት እንዳሳየም ተገልጿል።
ጥናቱ ካመላከታቸው አሉታዊ ጎኖች መካከልም ሀብትን በሚገባ ጥቅም ላይ አለማዋል አንዱ ነው። አዳዲስ አሰራሮችን ለመተግበርና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ጥናት ላይ የተመሠረተ እቅድ ማዘጋጀትና ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ የተመላከተ ሲሆን፣ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና የበጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አብርሀም ታደሰ እንደሚሉት፤ ኮሚሽኑ ከተሰጡት ስልጣንና ተግባሮች አንደኛው የህብረተሰብ ተሳትፎና የበጎ ፍቃድ ሥራዎችን ማስተባበር፣ ወደ ተግባር እንዲገቡ ማስቻልና ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ነው። ላለፉት ዓመታትም በተቋም ደረጃ ተግባራቱ መሬት እንዲወርዱ ለማስቻል ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ሰርቷል።
እንደ ኮሚሽነሩ ገለፃ፤ እነዚህ አፈፃፀሞች በየዓመቱ በሚደረጉ ተቋማዊ ግምገማዎች የሚታዩ ብቻ ነበሩ። አሁን ግን ሁሉም ህብረተሰብ በማህበር ተሳትፎና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስለሚከናወኑ ተግባራት ያለውን ግንዛቤና እውቀት በጥናትና ምርምር ለመለየት ተሞክሯል። አሰራሩን አስመልከቶ ሳይንሳዊ ግንዛቤ እንዲኖር ለማድረግ አዲስ መንገድ መከተል ማስፈለጉንም ይገልፃሉ። በዚህም ሁለት ርእሰ ጉዳዮች ላይ በአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ አማካኝነት ጥናቶቹ እንዲሰሩ መደረጋቸውን አስታውቀዋል። የመጀመሪያው ጥናት በህብረተሰቡ ተሳትፎ የሚሰሩ ተግባራት ያላቸው ፋይዳ ማመላከትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸው፣ ጥናቱም የተገኘ ውጤትና ያጋጠሙ ችግሮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል። ሁለተኛው ደግሞ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ የሚያጠነጥን እንደሆነ ገልፀዋል።
‹‹በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዙሪያ በዋነኝነት አገልግሎቱን ባሕል ማድረግና በህብረተሰቡ በራሱ እንዲመራ ማድረግ ያስፈልጋል›› የሚሉት ኮሚሽነሩ፤ በተለይ ደግሞ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር በቀዳሚነት ሚናቸውን መወጣት ያለባቸው ተቋማትና የህብረተሰብ ክፍሎች የሚለዩበትንና ወደ ተግባር የሚገባበትን መንገድ ለማመቻቸት አዳዲስ ደንቦች መፅደቃቸውን ይናገራሉ።
ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም ሳይንሳዊ ጥናቱ መከናወኑ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርላቸው ያስረዳሉ። በተለይ በጎ ፍቃደኝነት ባሕል እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው፣ በህብረተሰቡ ውስጥ እየመጣ ያለው ለውጥ በምን መልኩ ማምጣት ቻለ? የእስካሁኑ ተግባርስ ምን ውጤት አሳይቷል? ለሚሉትም በጥናቱ መልስ ማግኘት እንደተቻለም ይገልፃሉ።
‹‹ኮሚሽኑ ክረምት ጠብቆ ብቻ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ የበጎ ፍቃድ ሥራንና የህብረተሰብ ተሳትፎ ማስተባበርን ይሰራል›› ያሉት አቶ አብርሀም፤ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል። በተለይ ህብረተሰቡ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በቅንጅት እንዲሰራ፤ የራሱን ችግሮች በራሱ እንዲፈታ ማድረግ ያስቻሉ ተግባሮች መከናወናቸውን ያስረዳሉ። በተለይ በበጎ ፍቃድ ዘርፍ የህብረተሰቡ፣ የባለሀብቱ፣ የወጣቱና የአጠቃላይ የከተማው ነዋሪ ተሳትፎ ከታቀደው በላይ እንደነበርም ጠቅሰዋል። ይህን ተግባር በመምራት ብቻ ሳይሆን በተግባር ተሳታፊ በመሆንም ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ እርከን የሚገኘው አመራር ሚና ከፍተኛ መሆኑን ይገልፃሉ።
እንደ ኮሚሽነሩ ገለፃ፤ ተቋማዊ አፈፃፀም ከጊዜ ወደጊዜ ውጤታማ እየሆነ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2016 በጀት ዓመት ብቻ በበጎ ፍቃድ ማስተባበር ከሀብት አንፃር እስከ 12 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ለበጎ ፍቃድ ሥራ የዋለ መሆኑን አስታውቀዋል።
በህብረተሰብ ተሳትፎ በሚሰሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ደግሞ ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ ፈሰስ መደረጉንም ይናገራሉ። በልማትና በበጎ ፈቃድ ሥራ ላይ የሚውለው ሀብት በዋናነት ከራሱ ከህብረተሰቡ የሚወጣ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ሀብት ተግባር ላይ ሲውልም ራሱ ነዋሪው በሚመርጣቸው ተወካዮች አማካኝነት መሆኑን አስታውቀዋል።
‹‹በመኖሪያ ቤት ግንባታ ላይ ባለሀብቶች ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ናቸው›› የሚሉት አቶ አብርሀም፣ ከአሥር በላይ ወለል ያላቸው ሕንፃዎች ተገንብተው በበጎነት ለሀገር ባለውለታዎች፣ ለአቅመ ደካሞች እና በልዩ ልዩ ምክንያት ራሳቸውን መደገፍ ላልቻሉ ነዋሪዎች እየተላለፉ መሆናቸውን ይናገራሉ። የበጎነት ተግባሩም በማህበረሰቡ ውስጥ ትልቅ ተስፋ ማሳደሩን ጠቅሰው፣ ቀጣይ ለሚከናወኑ ተመሳሳይ ተግባራት መሠረት መሆኑን ያነሳሉ።
ኮሚሽነሩ እንዳሉት፤ ከቁሳዊው ጉዳይ በላይ በወጣቶች የስብዓና ግንባታና በማህበረሰቡ የመረዳዳት ባሕል ላይ ውጤት ያመጡ ሥራዎች እየተሰሩም ናቸው። የበጀት ዓመቱ ከጥቃቅን ጉድለቶች ባሻገር ውጤታማ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንዲሁም የማህበረሰብ ተሳትፎ የተከናወነበት ነበር።
የተያዘው ክረምትም በአብዛኛው ተማሪዎች የሚያርፉበት ከመሆኑ አንፃር ካሳለፍነው ግንቦት 18 ጀምሮ የበጎ ፍቃድ ሥራ በይፋ መጀመሩን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል። ዜጎች በጎ ተግባር ላይ መሳተፍን እየተለማመዱና ባሕሉን በይበልጥ እያጠናከሩት ነው የሚሉት ኮሚሽነሩ፤ በተለይ ወጣቶች በዚህ ላይ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ይናገራሉ።
እንደሚባለው ወጣቶች በተቃርኖ ሃሳብ ላይ ብቻ የሚቆሙ አይደሉም፤ በመፍትሔ ሰጪ ተግባሮች ላይ የሚሳተፉ ጭምር ናቸው ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ወጣቶች በርካታ መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህ ኃይል በበጎ ተግባር ላይ እየተሳተፈ መሆኑን አስታውቀዋል።
አቶ አብርሀም የሚመሩት የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን በየጊዜው የሚያወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው ዓመቱን ሙሉ እቅድ በማውጣት በርካታ ሥራዎችን ያከናውናል። ከእነዚህ አፈፃፀሞች ውስጥ ደግሞ የበጎ ምግባር ሥራዎች ቀዳሚ ናቸው። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለነገ ሀገር ተረካቢዎች መሠረት የሚጥሉ በጎነትን ፣ መረዳዳትንና የሀገር ፍቅርን ለማስተማር የማይተካ አበርክቶ እንዳላቸውም ግንዛቤ ይፈጥራሉ።
በራስ በጎ ፍቃድ የሚከናወኑ ሰብዓዊ ተግባራት ታዳጊዎች በመልካም ስብዕና እንዲታነፁ፣ ያላቸውን እንዲያካፍሉ ፣ የተቸገሩ ወገኖችን እንዲደግፉና በፍቅርና በመልካም ሥነ ምግባር ተኮትኩተው ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ እንደሚያግዙ በማመን ይህ መልካም እሴት እንዲቀጥል እየተሰራ ስለመሆኑም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ማስተባበሪያ ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ከሚገኙ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እና ምግባሮች ውስጥ በተያዘው ክረምት ለአቅመ ደካሞች የነፃ ሕክምና መስጠት አንዱ ነው። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በዚህም ከፍለው መታከም ለማይችሉ በየቤታቸው ተኝተው በህመም ለሚሰቃዩ ወገኖች እፎይታ የሚሰጥ እድል ተመቻችቷል፤ ይህም ባለፉት ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተግባር ላይ ውሏል። ነፃ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ቦታዎች ታካሚዎች በማህበራዊ ድረ ገፆች እንዲሁም በመገናኛ ብዙሃን እንዲያውቁ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የእድሉ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ተደርጓል።
ሕክምናው ሲሰጥባቸው ከነበሩ ስፍራዎች መካከል መገናኛ የካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ግቢ ውስጥ በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ነፃ ሕክምና ሲሰጥ ነበር። በሆስፒታሉ አማካኝነት ‹‹በጎነት ለጤና›› በሚል መሪ ሃሳብ ለተከታታይ ቀናት ተግባሩ ቀጥሎም ነበር።
ሆስፒታሉ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለ50 ሺህ ከፍለው መታከም የማይችሉ ሰዎች በየካ ክፍለ ከተማ ቅጥር ግቢ ውስጥ ነፃ ሕክምና ለመስጠት አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱንና እቅዱንም ማሳካቱን ኮሚሽኑ ያወጣው መረጃ ያመለክታል። ለሰባት ቀናት በቆየው በዚህ አገልግሎት ከፍለው መታከም የማይችሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ጥሪ ሲተላለፍ ቆይቷል።
ሌላው በተመሳሳይ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ የተሰማራው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነበር። ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝ ሆስፒታል ከልደታ ክፍለ ከተማ የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር ለሦስት ሺህ ከፍለው መታከም የማይችሉ ነዋሪዎች ነፃ የሕክምና አገልግሎት መስጠቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በተመሳሳይ ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅም እንዲሁ ይህንኑ አገልግሎት መስጠቱን የኮሚሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል አስታውቋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በይፋ ከተጀመረበት ግንቦት 18 ጀምሮ በተያዘለት እቅድ መሠረት በውጤታማነት ፣ ሁሉንም ባሳተፈና ማህበራዊ ችግሮችን በሚያቃልል መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝም ኮሚሽነሩ አቶ አብርሀም ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል። ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እየጎላ የመጣውን ይህን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አጠናክሮ መቀጠል እና የ2017 ዓ.ም የእቅድ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቅ የኮሚሽኑ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሆኑም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 3/2016 ዓ.ም