ቡና ስትራቴጂክ ሸቀጥ መደረጉ አፍሪካውያን የተፈጥሮ ሀብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የሚያነሳሳ ነው !

ቡና ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካውያን የኢኮኖሚ ዋልታ እና የኑሮ መሠረት ነው። ከአፍሪካ ሀገራት 32 የሚጠጉት ኢኮኖሚያቸው የተመሠረተው ቡና ላይ ሲሆን 70 በመቶ የሚጠጉ አፍሪካውያንም ገቢያቸው የተሳሰረው ከቡና ጋር ነው። በአጠቃላይ ከየትኛውም ምርት በላቀ መልኩ ቡና የአፍሪካውያን የገቢ ምንጭ ነው ማለት ይቻላል። ይህንኑ መሠረት በማድረግም የአፍሪካ ኅብረት ሰሞኑን ቡናን በስትራቴጂክ ሸቀጥነት ዕውቅና ሰጥቶታል።

የአፍሪካ ኅብረት ያሳለፈው ውሳኔ ቡና በዓለም ላይ ያለውን ተፈላጊነት ከፍ እንዲል ከማድረጉም ባሻገር በዘርፉ የሚታዩትን የምርታማነት፤ የተጠቃሚነትና ዕሴትን ጨምሮ ለገበያ የማቅረብ ችግሮችን ለመቅረፍ በር የሚከፍት ነው። ከዚህም ባሻገር በዘርፉ ውስጥ ያሉትን አምራቾች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትልቅ ርምጃ ነው።

አፍሪካ የቡና መገኛና እና ዋነኛ አምራች ብትሆንም ከዘርፉ ያላት ተጠቃሚነት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም ላይ 250 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ኑሯቸው ቀጥታ ከቡና ጋር የተያያዘ ሲሆን በቀን በአማካኝ 2ነጥብ 8 ቢሊዮን የሲኒ ቡናዎች ለገበያ ቀርበው ይሸጣሉ። በዚህም በዓመት እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስበት ግዙፍ ዘርፍ ለመሆን በቅቷል። ሆኖም የዘርፉ ዋነኛ ተዋናዮች የሆኑት አምራች አርሶ አደ ሮች የሚያገኙት ገቢ ከአንድ ስድስ ተኛ ያነሰ ነው።

እንደ አሕጉርም ቢሆን አፍሪካ ከቡና ምርት ተጠቃሚ አይደለችም። እ.ኤ.አ. በ2023 በዓለም አቀፍ ደረጃ 495 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከቡና ምርት የተገኘ ሲሆን አፍሪካ ከዚህ ውስጥ ያገኘችው ከአንድ በመቶ በታች መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ። በመሆኑም የቡና ዘርፍ ለዘመናት ኢ-ፍትሐዊነት የነገሠበትና አፍሪካውያንም ከሃብታቸው በአግባቡ መጠቀም እንዳልቻሉ አመላካች ነው።

ይህንኑ ችግር ከመሠረቱ ለመለወጥ በነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም በካምፓላ በተካሄደው የቡድን 25 የአፍሪካ ቡና አብቃይ ሀገራት ጉባኤ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና ንግዱን ለማስፋፋት ቡናን ከአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ የማጣጣምና የኅብረቱ ስትራቴጂክ ሸቀጥ ሆኖ እንዲሰየም ውሳኔ አሳልፏል።

በመቀጠልም ባለፈው የካቲት ወር 2016 ዓ.ም በተካሄደው 37ኛው የአፍሪካ የመሪዎች መደበኛ ጉባዔ ላይ ቡናን የአፍሪካ ኅብረት 2063 አጀንዳ እንደ አንድ ስትራቴጂካዊ ሸቀጥ ያፀደቀ ሲሆን የአፍሪካ ቡና አብቃይ ሃገራት ድርጅትንም የአፍሪካ ኅብረት ልዩ ኤጀንሲ አድርጎ መሾሙ ይታወቃል።።

ቡና የኅብረቱ ስትራቴጂካዊ ሸቀጥ ተደርጎ መሰየሙ ከኢኮኖሚ አንጻር ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ነው። ውሳኔው ለአፍሪካ ቡና አምራች ገበሬዎች መልካም ዜና ነው። ከዚህም ባሻገር ከአንዱ የአፍሪካ ጫፍ ወደ ሌላኛው የአሕጉሪቱ ጫፍ ቡናን በተመሳሳይ ታሪፍ፣ ጥራት፣ ሕግና መመዘኛ መገበያየት እንዲቻል በማድረግ ለአፍሪካ ሀገራት ነፃ የንግድ ስምምነት እውን መሆን የላቀ ድርሻ ያበረክታል ።

የአፍሪካ ሀገራትም በቡና ምርት ዙሪያ የተባበረ ድምፅ እንዲኖራት የሚያደርግ ከመሆኑ ባሻገር ዓለም ላይ ቡናን በተመለከተ የትኛውም ውሳኔ ላይ በአንድ ድምፅ እንዲወስኑና በቡና አምራቾች ላይ የሚደርሰውን ብዝብዛ በጋራ እንዲከላከሉ በር ይከፍታል።

የአፍሪካ ኅብረት ውሳኔ በእጅጉ ከሚጠቅማቸው ቡና አምራችና ላኪ ሀገራት አንዷና ዋነኛዋ ኢትዮጵያ ነች። ኢትዮጵያ የቡና መገኛና እና በአፍሪካም ቀዳሚዋ ቡና ላኪ ሀገር ብትሆንም በተዛባ የግብይት ሠንሠለት ምክንያት ተገቢውን ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች። ውሳኔውም የተዛባውን የንግድ ሠንሠለት በማስተካከል ኢትዮጵያና መሰል ሀገራት ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።

ኢትዮጵያ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቡና የወጪ ንግድ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ያገኘች ሲሆን በቀጣይም በመጠንም ሆነ በገቢ ረገድ የኢትዮጵያ የቡና ዘርፍ መነቃቃት እንደሚኖረው ይታመናል።

በተለይም ኢትዮጵያም የአፍሪካ ቡና አብቃይ ድርጅትን በሊቀመንበርነት እንድትመራ መደረጉ የኢትዮጵያን ቡና ለሌሎች ሀገራት ለማቅረብ፣ ለመገበያየት እና የንግድ መዳረሻዎችን ለማስፋት ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ ነው ።

በአጠቃላይ የአፍሪካ ኅብረት ቡናን ዋነኛ ስትራቴጂክ ሸቀጥ አድጎ መውሰዱ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን በቡና ላይ ኢኮኖሚውን የተመሠረተውን አፍሪካዊ ከመጥቀሙም ባሻገር አፍሪካውያን የተፈጥሮ ሃብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የሚያነሳሳ ነው!

አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You