የረድኤት ድርጅቶች አውደ ርዕይ

በኢትዮጵያ የሚዘጋጁ ኤግዚቢሽኖችና ባዛሮች በአብዛኛው ሸማቹን ከነጋዴው የሚያገናኙ ናቸው። በባዛርና ኤግዚቢሽን ነጋዴው ያሉትን ምርቶችና አገልግሎቶች ለሸማቾች የማስተዋወቅ እድል ይፈጠርለታል። በተመሳሳይ ሸማቹም በአንድ ቦታ ላይ ተገኝቶ የተለያዩ ምርቶችን ከነጋዴው የመግዛት እድል ይፈጠርለታል።

ከንግድ ውጪ የሆኑና ማህበራዊ ይዘት ያላቸው ባዛሮችና ኤግዚቢሽኖች ሲዘጋጁ ግን እምብዛም አይታይም። የሚዘጋጁትም በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ሆኖም ከተለመደው ባዛርና ኤግዚቢሽን ወጣ ያለና በተለይ በአካል ጉዳተኞችና ሌሎች ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ የሚንቀሳቀሱ የእርዳታ ድርጅቶችና በጎ አድራጎት ማህበራት የሚሳተፉበት አውደ ርዕይ በነሐሴ አጋማሽ ይካሄዳል።

አቶ ናትናኤል ዘርይሁን በታሜሶል ኮሚዩኒኬሽን ‹‹አዲስ ነገር በአዲስ ዓመት›› ኤክስፖ የማርኬቲንግ ዳይሬክተር ሆነው ያገለግላሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ በአብዛኛው የሚካሄዱ ባዛሮችና ኤግዚቢሽኖች ንግድን መሰረት ያደረጉና ሸማቾችን ከአምራቾች የሚያገናኙ ናቸው። ይሁንና የንግድ ባዛርና ኤግዚቢሽኖችን ማህበራዊ ይዘት ካላቸው ጋር ቀይጦ ማካሄድ ይቻላል።

ይህም ህብረተተሰቡ ከንግድ ባለፈ በባዛርና ኤግዚቢሽኖች ከሚቀርቡና በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ከሚሰሩ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ጋር በሁለንተናዊ መልኩ ግንኙነት ለመፍጠር ያስችለዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን የእርዳታ ድርጅቶቹና ማህበራቱ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በጉልበትና በሌሎችም መንገዶች ለመደገፍ አጋጣሚዎች ይፈጠሩለታል።

እንደ ማርኬቲንግ ዳይሬክተሩ ገለፃ ‹‹አዲስ ነገር በአዲስ ዓመት›› ኤክስፖ መካሄድ ከጀመረ ሀያ አመታትን አስቆጥሯል። ይሁንና ዘንድሮ ከነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የሚካሄደው ከዚህ በፊት ሲካሄዱ የነበሩ ኤክስፖዎችን በደንብ በማጤን አዲስና ማህበራዊ ይዘት ያላቸው ባዛርና ኤግዚቢሽኖች እንዲካተቱበት ተደርጓል። ሰዎች በቀላሉ የሚፈልጓቸውን ነገሮች ሊያገኙ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ኤክስፖው በመንደር ይከፋፈላል። በነዚህ መንደሮች ውስጥ ማህበራዊ ይዘት ያላቸውና እንደ ጤና፣ ትምህርት፣ እውቀት፣ ልጆች፣ ስፖርት፣ መዝናኛና ሌሎችም እንዲካተቱ ይደረጋል።

ኤክስፖው በመንደር ተከፋፍሎ መካሄዱ ተሳታፊዎች በመደበኛነት ከሚያደርጓቸው የንግድና ባዛር እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ ማህበራዊ ይዘት ባላቸው መንደሮች ውስጥ ገብተው የጤና ሁኔታቸውን ለመረዳት፣ ትምህርታዊ መረጃዎችን ለማወቅና የትምህርት ቁሳቁሶችን ለልጆቻቸው ለመግዛት፣ እውቀትን ለማሳደግ የሚረዱ መፃህፍትን ለመሸመትና ከእውቀት ጋር የተያያዙ ውይይቶችንና ክርክሮችን እንዲያደርጉ ብሎም ልጆቻቸውን ለማዝናናት፣ ለማቆየትና ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ለማስቻል እድል የሚሰጥ ነው።

በዚህ አውደ ርዕይ በአካል ጉዳተኞችና ሌሎች ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ የሚንቀሳቀሱ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት የራሳቸውን መንደር በነፃ ወስደው ገቢ እንዲያሰባስቡና ለጎብኚዎች ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ እድል ተመቻችቷል። በዚሁ መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅቶቹና ማህበራቱ ጥሪ ተደርጎላቸው ምዝገባ እያካሄዱ ይገኛሉ።

ማርኬቲንግ ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ በኤክስፖው ‹‹የበጎ ስራ መንደር›› በሚል ስያሜ 50 የሚሆኑ መንደሮች በበጎ አድራጎት ስራ ለተሰማሩ ድርጅቶችና ማህበራት ይዘጋጃሉ። በዚህ መንደር የሚገቡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ለአካል ጉዳተኞችና ሌሎች ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች ከሚያስባስቡት ድጋፍ በተጨማሪም በጎፋ ገዜ ወረዳ በመሬት መንሸራተት ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን ላጡ የመልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ እንደሚያሰባስቡ ይጠበቃል።

እንዲህ አይነቱ ማህበራዊ ይዘት ያለው ኤክስፖ ደግሞ የራሱ ጠቀሜታ አለው። ከዚህ ውስጥ አንዱ ሰዎች ከተለመደው የንግድ ኤክስፖ ባሻገር በማህበራዊ ህይወት ላይ ያሉ ኤግዚቢሽኖች መልካቸው ምን እንደሆነ እንዲገነዘቡ ያደርጋል። በማህራዊ ህይወት ላይ አተኩረው ከሚሰሩ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ጋርም እጅና ጓንት ሆነው እንዲሰሩ እድል ይፈጥራል። ይህም አካል ጉዳተኞችና ሌሎች ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል።

በሌላ በኩል ኤክስፖው ማህበረሰቡ የሚፈልገውን ማህበራዊ እንቅስቃሴ በአንድ በተወሰነ መንደር ውስጥ እንዲያገኝ ያስችለዋል። ማህበራዊ ህይወትንም ያንፀባርቃል። መንደር የሚለው ፅነሰ ሃሳብ በራሱ ኢትዮጵያ ከመንደር ጀምራ ሀገር ሆና እንደተሰራች ያመላክታል። በዚህ ኤክስፖም ይህንኑ ማህበራዊ ህይወት ለማንፀባረቅ ነው የታቀደው። በቀጣይ ደግሞ ትንሷ ፈረንሳይ፣ ትንሷ መርካቶ በማለት የዛ አካባቢ ተወላጆች በጋራ ወደ ንግዱ አለም ገብተው እንዲሳተፉ ጥሪዎች ተላልፈዋል።

በኤክስፖው የሚዘጋጀው መንደር ውስጥ አንድ ሰው ለአዲስ አመት ምን ይፈልጋል የሚለው መነሻ ከግምት ውስጥ ገብቶ ነው ጤና፣ ትምህርት፣ ልጆች፣ ስፖርት፣ መዝናኛና ሌሎች ልዩ ልዩ ማህበራዊ ጉዳዮች እንዲካተቱ የሚደረገው። ስለዚህ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራትም በኤክስፖው መንደር ውስጥ ገብተው ለማህበረሰቡ የሚሰጡትን ፋይዳ ያስተዋውቃሉ። ከማህረሰቡ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያጠናክራሉ። ለሚደግፏቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ገቢ ለማሰባሰብም እድል ይፈጠርላቸዋል።

በተጨማሪም ወጣቶች ተደራጅተው ሰፈራቸውን ማስጠራት የሚችሉበትን፣ ስራ የሚሰሩበትን ሁኔታ ለመፍጠርና ለወጣቱ የተሻለ እድል ለመሰጠት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ትላልቅ ሃሳብ ይዘው የመጡ ነገር ግን በአቅም ምክንያት ምርትና አገልግሎታቸውን ለማህበረሰቡ ማድረስ ላልቻሉ ወጣቶች በኤክስፖው ቦታዎች በነፃ እንዲሰጣቸው ይደረጋል። ይህንንም እድል ብዙዎች እንደሚጠቀሙበት ይጠበቃል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 2 / 2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

 

Recommended For You