በአንድ ሀገር የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ጉልህ ድርሻ ካላቸው ተቋማት መካከል በዋነኛነት የሚጠቀሱት የንግድ ባንኮች ናቸው። ሀገራዊ የገበያ ሥርዓትን ከማዘመን እና ከማቀላጠፍ ባለፈ፤ እነዚህ ባንኮች በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖራቸው ድርሻ ከፍ ያለ ነው። ይህንኑ አስተዋጽኦአቸውን ታሳቢ በማድረግም መንግሥታት ለተቋማቱ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው ይንቀሳቀሳሉ።
ከዚህ ባሻገርም የእነዚህ ተቋማት ውድቀትም ሆነ ስኬት በአንድ ሀገር አጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይ ሊያሳድር ከሚችለው አደጋ አንጻርም፤ ተቋማቱ ከትርፍ ባሻገር ያላቸውን ሀገራዊ ፋይዳ በሚሸከም መንገድ የዕለት ተዕለት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያስችል ጠንካራ የቁጥጥር እና የክትትል ሥርዓት መዘርጋት እና መቆጣጠር ትልቁ የመንግሥት ኃላፊነት ነው።
ከሁሉም በላይ ለዘርፉ የተቀመጡ ሕጎችን፣ መመሪያዎችን እና የአሠራር ሥርዓቶችን ተቀብሎ ውጤታማ በሆነ መንገድ መተግበር መቻላቸውን መቆጣጠር ፣ ችግር ሲያጋጥም ጠንካራ የእርምት እርምጃ መውሰድ፤የአንድ ሀገር የፋይናንስ ሥርዓትን እና ከዚህ የሚመነጨውን ሀገራዊ ተጠቃሚነት ማጽናት የመንግሥት የሁልጊዜ የቤት ሥራ ነው።
በተለይም የባንክ ኢንዱስትሪው ባላደገበት እና ዜጎች ስለባንክ ሥራ ተገቢውን ግንዛቤ ባልጨበጡበት ሀገራዊ ሁኔታ ውስጥ፤ ዘርፉን በጠንካራ ዲሲፕሊን የመምራቱ ጉዳይ ትኩረት የሚሻ ነው፡፡ ይሄ መሆኑም ዜጎችን ከፍ ሲልም ሀገርን ከከፋ አደጋ የመታደግ ያህል ተደርጎ የሚታይ፤ ለዘርፉ ቀጣይ እድገትም ትልቅ አቅም የመፍጠር ጅማሬ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
በእኛም ሀገር የባንክ ሥራ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የተጀመረ፤ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም፤ ዘርፉ የዕድሜውን ያህል መጓዝ ባለመቻሉ ዛሬም በብዙ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ይገኛል። ፈተናዎቹን በራሱ ጊዜ መሻገር አቅቶትም የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት ሲጠይቅ ቆይቷል።
በየወቅቱ በስልጣን ላይ የነበሩ መንግሥታትም፤ ዘርፉ ራሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳድሮ በስኬት ላይወጣ ይችላል የሚል ስጋት ስለነበራቸው፤ በርግጥም የመጡበት መንገድ ለተወዳዳሪነት የሚያነቃቃ ባለመሆኑ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የፖሊሲ ጥበቃ ተደርጎላቸው ቆይተዋል።
በእነዚህ ጊዜያትም በሀገር ውስጥ የሚገኙ ባንኮች ከአደጋ ነጻ በሆነ መንገድ በሚያካሂዷቸው የባንክ ሥራዎች በብዙ አትራፊ ቢሆኑም፤ በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባውን አስተዋጽኦ በአግባቡ መወጣት የሚያስችላቸውን ቁመና መፍጠር ሳይችሉ ዓመታት ተቆጥረዋል።
በአንዳንድ አጋጣሚዎችም የባንኩን ዘርፍ ተአማኒ እና ፍትሐዊ አገልግሎት ጥያቄ ውስጥ በሚከቱ፤ ከዚያም ባለፈ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ሀገር የተቋማቱን ድጋፍ በምትፈልግባቸው አስቸጋሪ ወቅቶች የሀገርን ጥቅም በሚጎዱ ተግባራት ውስጥ ተሳታፊ ሲሆኑም ተስተውሏል።
በዚህም ሕገወጥነትን ከማበረታታት ባለፈ ጤናማ ሀገራዊ የፋይናንስ ሥርዓት እውን እንዳይሆን በራሳቸው ፈተና ከመሆን ባለፈ፤ በውስጣቸው ያደገው ሕገወጥነት አጠቃላይ በሆነው የመንግሥት የፖሊሲ ድንጋጌዎች ስኬታማት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሲፈጥር ቆይቷል። በዚህም መንግሥት እና ሕዝብ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ ሆነዋል።
ይህ በየወቅቱ በአግባቡ ያልተገራው የባንኮች ከሕግ እና አጠቃላይ ከሆነው የፋይናንስ ሥርዓት እና አሠራር ያፈነገጠ አሠራር፤ ዛሬም መንግሥት ተግባራዊ እያደረገ ባለው የማክሮ ፖሊሲ ማሻሻያ ላይ እንዳይደገም የሚመለከተው አካል በቁርጠኝነት ሊንቀሳቀስ ይገባል። ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በጠንካራ እርምጃ ማረም ይጠበቅበታል።
አንዳንድ ንግድ ባንኮቹ በተለይም በገበያ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ የውጪ ምንዛሪ የግብይት ሥርዓት ተግባራዊ በተደረገ ማግስት፤ የገበያ ሥርዓቱ በማይፈቅደው መንገድ የዶላር ግዥ ለማካሄድ የሚያደርጉት ጥረት በተሳሳተ መንገድ ተቋማዊ ትርፋማነትን ብቻ ታሳቢ ያደረገ፤ሀገር እና ሕዝብ የሚጎዳ መሆኑን በአግባቡ ሊያጤኑት ይገባል።
በዚህ መልኩ የሚደረግ ያልተገባ ውድድር ፣ ባንኮቹ ነገ ላይ ለሚጠብቃቸው ጠንካራ ፉክክር አቅም ሊፈጥርላቸው የማይችል ፣ ራሳቸውን ለከፋ አደጋ ተጋላጭ የሚያደርጋቸው ነው። ከሁሉም በላይ አሁን ላይ ተግባራዊ እየሆነ ላለው የማክሮ ፖሊሲ ማሻሻያ በራሱ ፈተና ሊሆን የሚችል ነው።
ከዚህ አኳያ የንግድ ባንኮቹን ለመቆጣጠር ስልጣን የተሰጠው አካል፤እየተስተዋለ ባለው ችግር ዙሪያ የማያዳግም ርምጃ በመውሰድ፤ የባንኮቹ የዕለት ተዕለት አሠራር ለሕግ እና መመሪያዎች የተገዛ መሆኑን፤ በዘርፉ የሚደረጉ ውድድሮች የዘርፉን የውድድር መርሆዎች የተከተሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፤ ባንኮችም ለፖሊሲ ማሻሻያው ስኬታማነት የሚጠበቅባቸውን በኃላፊነት ሊወጡ ይገባል!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 2 / 2016 ዓ.ም