በኢትዮጵያ ከሚካሄዱ የኢንቨስትመንት ሥራዎች መካከል በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚካሄደው ይጠቀሳል። ይህ ኢንቨስትመንት በውጭ ኩባንያዎች የሚካሄድ እንደመሆኑ ይዞት የሚመጣው ካፒታል ወይም የውጭ ምንዛሪ፣ ቴክኖሎጂና በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላለ በብልጽግና ጎዳና ላይ የሀገር እውቀት በእጅጉ ይፈለጋል።፡
እንደ ቻይና ያሉት ያደጉት ሀገሮች ጭምር በእጅጉ የሚፈልጉትን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ፋይዳ የኢትዮጵያ መንግሥታትም በሚገባ በመገንዘብ ለኢንቨስትመንቱ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ ጥረት አድርገዋል። ዘርፉን አላላውስ ሲሉ የቆዩትን ችግሮች ለመፍታትም ያላሻሻሉት አሠራር የለም ማለት ይቻላል።
ፈተናዎቹ ከባድ ቢሆኑም በዘርፉ ብዙ ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶችን በመሳብ፣ ባለሀብቶቹ የወጪ ምርቶችን እያመረቱ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኙ የተደረጉባቸው ሁኔታዎች ታይተዋል።
የለውጡ መንግሥትም ይህን ለውጥ ባለፉት ስድስት ዓመታት ለማስቀጠል ብዙ ጥረት አድርጓል። እንደ ሰላም እጦት ላሉ ተግዳሮቶች በባህሪው ድንጉጥ ለሆነው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ያለፉት የኢትዮጵያ ዓመታት ምቹ ሊሆኑ እንደማይችሉ ይታመናል።
በኮቪድ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በታዩ ግጭቶች ፣ በዓለም አቀፍ ተቋማትና በምእራባውያኑ ያደጉት ሀገሮች ጫናዎች እንዲሁም በሌሎች ዓለም አቀፍና አካባቢያዊ ሁኔታዎች ስትፈተን የቆየችው ኢትዮጵያ፣ እነዚህን ፈተናዎች እንደ መልካም አጋጣሚ ጭምር በመጠቀም በተለያዩ ዘርፎች ለውጦችን አስመዝግባለች።
በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም ዘርፍ ቢሆን ለውጦች አሳይታለች። ሀገሪቱ እንደ ሀገር ብቻም ሳይሆን እንደ ክፍለ አህጉርና አህጉርም በዘርፉ ያሳየቻቸው ለውጦችም ይህንኑ ያመለክታሉ።
ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃዎች መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው፤ መረጃዎቹ እንደጠቆሙት፤ በ2016 በጀት ዓመት ሦስት ነጥብ 82 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል። ይህም የዕቅዱን 80 በመቶ ያህል ነው፤ ይህ አፈጻጸም ከቀደመው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የ11 ነጥብ አምስት በመቶ ጭማሪም አለው። አፈጻጸሙም ከ2014 ወዲህ የተመዘገበው ትልቁ ውጤት ተብሏል።
ለውጦቹ በሀገር ደረጃ ብቻ የሚጠቀሱ አይደሉም፤ ሀገሪቱ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በሳበችው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር መሆን ችላለች። የዓለም ኢንቨስትመንት ሪፖርት መረጃን ዋቢ ያደረጉ ምንጮችም ይህንኑ አረጋግጠዋል። ለኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢ የሚችሉትን ኬንያንና ኡጋንዳን ልቃ በመገኘትም በክፍለ አህጉሩ ፊት ለፊት ላይ መቀመጥ ችላለች።
ሀገሪቱ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመነት የምታስመዘግበው ለውጥ እንደሚቀጥል መረጃዎች ያመለክታሉ። በ2017 በጀት ዓመት አራት ነጥብ 52 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ከታቀደበት ሁኔታም መረዳት ይህንኑ መገንዘብ ይቻላል።
በሀገሪቱ ባለፈው በጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባሮችም በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እያስመዘገበች ያለችውን ውጤት ማስቀጠል እንደምትችል ያመላክታሉ። ከተለያዩ ሀገሮች ከመጡ የኢንቨስትመንት አካላትና ባለሀብቶች ጋር የተደረጉ ውይይቶችና ይህን ተከትሎ ባለሀብቶች በሀገሪቱ ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ያሳዩት ፍላጎት ከፍተኛ እየሆነ ያለበት ሁኔታ እንዲሁም አዳዲስ ሀገራት በዘርፉ ለመሰማራት ያሳዩት ፍላጎት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቱ እንደሚጨምር ይጠቁማሉ።
የውጭ ባለሀብቶች በጅምላና ችርቻሮ ንግድ እንዲሰማሩ የሚያስችል አዋጅ ማውጣቱ፣ የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሠሩ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ፣ ወደ ሥራ የገባው የካፒታል ገበያ ለውጭ ባለሀብቶች ጭምር ክፍት መሆኑ፣ ሌሎች ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች እንደመሆናቸው ዘርፉ በቀጣይ ብዙ ለውጥ የሚመዘገብበት ይሆናል ብሎ መገመት ይቻላል።
ሰሞኑን ወደ ትግበራ የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና እሱን ተከትሎ ብሄራዊ ባንክ ያወጣው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያም በተለይ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱ መጨመር ያላቸው ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑ በመንግሥትም በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም እየተጠቀሰ ይገኛል።
ማሻሻያው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመልሱ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፤ ማሻሻያው መውጣቱን ተከትሎ ሀገሪቱ ለልማቷ በእጅጉ የሚያስፈልጋትን ብድር ማግኘት ያስቻላት ሆኗል። የእነዚህ ተቋማት ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ማዞር የውጭ ባለሀብቶችና ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ኩባንያዎች ኢትዮጵያን ምርጫቸው እንዲያደርጉ አዎንታዊ ተጽእኖ ሊያሳርፍ ይችላል።
ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚሆኑ ምቹ ከባቢዎችን መፍጠር እንደታቸለና በዚህም ለውጥ ማምጣት እንደተጀመረ ሁሉ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱን ይበልጥ ለመሳብ የሀገሪቱን የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎች ዘላቂነት ባለው መልኩ በማስተዋወቅ ላይ መሰራት ይኖርበታል።
ባለሀብቶቹ ዘርፉን ለመቀላቀል ሲመጡ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ፣ አቅም ያላቸውን ባለሀብቶች መሳብ መቻል፣ ኢንቨስትመንቱ ከቁጥር ባሻገር ውጤታማ በሚሆንበት ላይ በትኩረት መስራት በቀጣይ በትኩረት ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም