ከዛሬ 18 ዓመታት በፊት ሐምሌ 28 ቀን 1998 ዓ.ም ሌሊቱን በድሬዳዋ ከተማ ከባድ ዝናብ ሲዘንብ አደረ። ከባድ ጎርፍ ተከሰተ። የተከሰተው ጎርፍ ግን አደገኛ ጎርፍ ነበር። መላው ኢትዮጵያን ለሀዘን የዳረገ አደጋ ተከሰተ። እነሆ ከ18 ዓመታት በኋላ በዚሁ በሐምሌ ወር በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም በተከሰተ የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ሕይወት አጣን። ባለፈው ሳምንትም በሲዳማ ክልል ተመሳሳይ አደጋ ተከሰተ። የክረምት ከባድ ዝናብ ለዳግም አደጋ ዳረገን።
መሰል አደጋዎች እንዳይበዙብን ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ እያሳሰብን በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ከ18 ዓመታት በፊት የተከሰተውን የድሬዳዋ የጎርፍ አደጋ እና ለመከላከል የተሰሩ ተከታታይ ሥራዎችን እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን እናስታውስ።
ከ88 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ በግፈኛው የጣሊያን ፋሽስት ተገደሉ። ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ለጣሊያን አልገዛም በማለታቸው፣ እንደ ብዙዎቹ ባንዳዎች በጣሊያን ማታለያ ባለመታለላቸው፣ በወራሪው ጣሊያን ማስፈራሪያ ባለመፍራታቸው፣ ከሕይወታቸው በላይ የሀገራቸውን ክብር አስቀድመው ጥይት አቀባብሎ ከፊታቸው በቆመ ሰው ፊት ‹‹ለሀገሬ መሞት ኩራት ነው!›› ብለው በድፍረት በመናገርና መስዋዕት በመሆን እነሆ የሀገር ፍቅር ምሳሌ ተደርገው ሲዘከሩ ይኖራሉ። በዚሁ ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችንም ባለፉት ዓመታት በዝርዝር ዘክረናቸዋል።
ከ76 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 22 ቀን 1940 ዓ.ም (ጁላይ 29 ቀን 1948) በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ምክንያት ለአሥራ ሁለት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የኦሊምፒክ ውድድር (ጨዋታ) 14ኛው ውድድር በለንደን ተጀመረ። እነሆ በዚህ ዓመት 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታ በሌላኛዋ አውሮፓዊት ሀገር ፈረንሳይ ፓሪስ በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ነው።
ከ113 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 23 ቀን 1903 ዓ.ም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ከግርማዊት እቴጌ መነን አስፋው ጋር ጋብቻቸውን ፈፀሙ።
ከ138 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 24 ቀን 1878 ዓ.ም ደራሲ፣ ሐኪምና የምጣኔ ሀብት ጥናት ባለሙያ የነበሩት ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ተወለዱ።
ከ7 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 24 ቀን 2009 ዓ.ም ‹‹የተረት አባት›› በመባል የሚታወቁት አባባ ተስፋዬ አረፉ።
ከ6 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 24 ቀን 2010 ዓ.ም አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም አረፈ።
ከ44 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 25 ቀን 1972 ዓ.ም ኢትዮጵያዊው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የሞስኮ ኦሊምፒክ የ5 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድርን በማሸነፍ ኢትዮጵያን የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት አደረገ።
ከ128 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 28 ቀን 1888 ዓ.ም (በዓድዋ ድል ዓመት ማለት ነው) የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ሥራ ጀመረ። ሥራውን የጀመረው የሩስያ ሐኪሞች ቡድን በአዲስ አበባ አሁን ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል በሚገኝበት ቦታ ላይ ድንኳን በመትከል የሕክምና አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው ነው።
አሁን በዝርዝር ወደምናየው የድሬዳዋ የጎርፍ አደጋ እና አደጋውን ለማስቀረት ሲደረጉ በቆዩ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ታሪክ እንለፍ።
የታሪክ አንዱ ጠቀሜታው ጥሩ ነገሮችን ለማስቀጠል፣ ከመጥፎ አጋጣሚዎች ደግሞ ለመማር ክስተቶችን ማስታወሱ ነው። በተለይም የክስተቶች ታሪክ ደግሞ በወቅቱ የነበሩ ሁነቶችን ስለሚያስታውስ ሰዎች ወደኋላ መለስ ብለው ‹‹ለካ እንዲህ ሆኖ ነበር!›› ይላሉ። ከእነዚህ መጥፎ ክስተቶች አንዱ ደግሞ የክረምቱ ገናና ወር በሆነው በሐምሌ ወር መጨረሻ፤ ከዛሬ 18 ዓመታት በፊት ተከስቶ የነበረው የድሬዳዋ የጎርፍ አደጋ ነው።
ሳቅ እና ጨዋታ የማይጠፋባት፣ የተከፋውን ሁሉ ፈገግ የሚያሰኝ ሕዝብ ያላት ድሬዳዋ በዚያች ሌሊት ግን ሀዘን ጥላውን ጣለባት። የድሬ ሀዘንም የመላው ኢትዮጵያውያን ሀዘን ሆነ። የሬዲዮ ጣቢያዎች በዋሽንት አሳዛኝ ዜማ ልብ ሰባሪ ድምጽ ሲያወጡ ሰነበቱ። ከዕለት ወደ ዕለት የሚሰማው ዜና የሟቾች ቁጥር እና የጠፉ ቤተሰቦች ቁጥር ብዛት ሆነ። ያቺ የደስታ ምንጭ ድሬዳዋ ለወራት በሀዘን ድባብ ተዋጠች።
ቀኑ ሐምሌ 28 ቀን 1998 ዓ.ም ነው። ሌሊቱን እጅግ ከባድ ዝናብ ጣለ። የጣለው ከባድ ዝናብም ከባድ የጎርፍ አደጋ አስከተለ። በወቅቱ በኢትዮጵያ እንደ ዛሬው የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አልነበሩም። መረጃው ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ጊዜ የመድረስ ዕድል አልነበረውም።
አደጋው የደረሰው ሐምሌ 28 ሌሊት ለሐምሌ 29 አጥቢያ ነው። ሐምሌ 29 ቀን 1998 ዓ.ም ጠዋት በጥቂት የቴሌቭዥን ተጠቃሚዎችና በብዙ የሬዲዮ ተጠቃሚዎች ዘንድ ይህ አሳዛኝ ዜና መሰማት ጀመረ። የድሬዳዋ የጎርፍ አደጋ! በሁለተኛው፣ ሦስተኛውና አራተኛው ቀን… እያለ ግን በሕትመት መገናኛ ዘዴዎችም ተጨማሪ ሐተታዎችን ጨምሮ ተደራሽነቱ እየሰፋ መጣ።
ከአደጋው ክስተት መሰማት በኋላ አሃዛዊ መረጃዎችም መውጣት ጀመሩ። 200 ያህል ሰዎች ሕይወታቸው አልፎ ተገኘ፤ 300 ያህል ሰዎች የደረሱበት ሳይታወቅ ቀረ። 3 ሺህ ያህል ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቀሉ።
የውጭ መገናኛ ብዙኃን በወቅቱ እንደዘገቡት፤ አደጋው በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የተባለ አደጋ ነበር። አደጋው የ15 ሚሊዮን ዜጎችን ሕይወት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንደሚነካ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳዮች ትብብር ጽሕፈት ቤት (UN Office for the Coordination of Humanitarian Affairs) መረጃ ያመለክታል።
ከሐምሌ 30 ቀን ጀምሮ የርዳታ ሰጪ ድርጅቶች (የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ ዩኒሴፍ የመሳሰሉት) እና መንግሥት ወደ ቦታው መድረስ ጀመሩ። የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋትና ዝግጁነት ኤጄንሲ የርዳታ ዝርዝር ሒደቶችን ማሳወቅ ጀመረ። ኤጀንሲው ሐምሌ 30 ቀን አስቸኳይ የምግብና ቁሳቁስ ርዳታዎችን ይዞ በቦታው እንደደረሰ የOCHA መረጃ ያመለክታል።
ከሐምሌ 30 በኋላ በተደረጉ ምርመራዎች ደግሞ የተፈናቃዮችና የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መጣ። 200 የነበረው የሟቾች ቁጥር በምርመራ የተረጋገጠው ብቻ 250 ደረሰ። አጠቃላይ በአደጋው የተፈናቀሉት ደግሞ ከ10 ሺህ በላይ እንደሆነ የወቅቱ መረጃዎች ያሳያሉ። በወቅቱ የነበረው የድሬዳዋ ሕዝብ ብዛት ከ398 ሺህ በላይ እንደነበር በ1997 ዓ.ም የተደረገው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ መረጃ ያመለክታል። ምናልባትም 400 ሺህ ሊሆን ይችላል።
ታሪክን ስናስታውስ በወቅቱ የነበሩ ሁነቶችን ጭምር ይነግረናል። የድሬዳዋ የጎርፍ አደጋ የመድረሱ ዜና በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከተሰማ በኋላ የድጋፍ ትብብሮች ተደርገዋል። የወቅቱ የመንግሥት አካላት እና የተለያዩ ሲቪክ ማህበራት ሀዘናቸውን ገልጸዋል።
ነሐሴ 1 ቀን 1998 ዓ.ም የታተመ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ባገኘነው መረጃ፤ የወቅቱ የድሬዳዋ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ፍስሐ ዘሪሁን ሐምሌ 30 ቀን 1998 ዓ.ም ድሬዳዋ ለደረሱ ጋዜጠኞች ስለአደጋው ሁኔታ መግለጫ ሰጥተዋል። ከንቲባው በሰጡት መግለጫ፤ አደጋው የደረሰው ከሌሊት 7፡00 እስከ 9፡00 ባለው ነው።
ሌሊት 9፡00 ላይ ፖሊሶች ደርሰው ጥይት ወደ ሰማይ በመተኮስ እንቅልፍ የተኛ ሕዝብ እንዲነቃ አድርገዋል። በሚተኮሰው ጥይት እና በሰዎች ጩኸት ለጊዜው አደጋው ያልደረሰባቸው የተገኙ ሰዎች ራሳቸውን እንዲያድኑ እና ሌሎችንም እንዲያድኑ ተደርጓል። የተጎዱትንም ሕይወታቸውን ለማትረፍ ፖሊሶች በሌሊት ጥሪ አስተላልፈዋል።
የፌዴራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት በቦታው ሲደርሱ፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ራሳቸውን ለማዳን በየጣሪያውና አጥሩ ላይ ወጥተዋል። የፖሊስና የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት እነዚህን በየጣሪያውና አጥሩ ላይ የወጡ ዜጎችን በማውረድ ወደ ሌላ አካባቢ አንቀሳቅሰዋል፤ የተጎዱትን ወደ ሆስፒታል ወስደዋል። ተጎጂዎችን ማስተናገድ ከድሬዳዋ ድል ጮራ ሆስፒታል አቅም በላይ ስለነበር በከተማዋ የሚገኙ ሁሉም ክሊኒኮች አገልግሎት እንዲሰጡና መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ጥሪ ተላልፏል። ከመንግሥት በተጨማሪ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ባለሀብቶችም በወቅቱ ርብርብ አድርገዋል።
የጎርፍ አደጋው ደርሶ የነበረው በከተማዋ ስድስት ቀበሌዎችና በገጠር ደግሞ ጭሪ ሚጢ፣ በኬሐሎና ኢጀአነኒ ቀበሌዎች ነበር።
የድሬዳዋ የጎርፍ አደጋ በወቅቱ የነበሩ ተቋማትን ሁሉ ወደ አስቸኳይ ሥራ እንዲገቡ ያደረገ ነበር። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ብዙዎችን ይነካካል የተባለውም ለዚህ ነው። የፌዴራል ተቋማት እንደየሥራ ድርሻቸው ተሰማርተዋል። ለምሳሌ፤ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በጎርፍ አደጋው የፈራረሱ መንገዶችን በአፋጣኝ ጠግኖ ለርዳታ ለሚገቡ ተሽከርካሪዎች ምቹ ማድረጉን በወቅቱ በነበሩ ዜናዎች ተነግሯል።
ነሐሴ 1 ቀን 1998 ዓ.ም የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በድሬዳዋ ተገኝተው ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ጎበኙ። የአካባቢው ማህበረሰብ ያደረገውን መደጋገፍ አድንቀው መንግሥት ተገቢውን ድጋፍና ጥበቃ እንደሚያደርግ ለተጎጂዎች ገልጸዋል። የአካባቢው ነዋሪዎችም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት አድርገዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት በኋላ የፌዴራል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኤጄንሲ በጎርፍ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሒሳብ ቁጥር ተከፈተ። የሒሳብ ቁጥሩ በመገናኛ ብዙኃን ይፋ የተደረገ ሲሆን የሒሳብ ቁጥሩም 0171806845300 ነበር።
የድጋፍ ጥሪው እንደተደረገ ከግለሰቦች ጀምሮ ተቋማትና ባለሀብቶች ርብርብ አድርገዋል። ለምሳሌ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 200 ሺህ ብር፣ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ 150 ሺህ ብር፣ የሐረሪ ክልል 100 ሺህ ብር፣ የአዳማ ከተማ 100 ሺህ፣ በአጠቃላይ 550 ሺህ ብር ድጋፍ የተደረገው እስከ ነሐሴ 2 ቀን ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ ነበር።
ከዚያ በኋላ ባሉት ቀናት፣ ሳምንታት እና ወራት ውስጥ የርዳታዎች ቁጥር እየጨመረ ሄደ። የተለያዩ ተቋማት፣ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ኩባንያዎች፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ የተለያዩ ማህበራት ርዳታ እያሰባሰቡ ማስረከብ ጀመሩ። የተለያዩ ተቋማት ሠራተኞች ደግሞ ከ10 እስከ 30 በመቶ የሚሆን የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለግሰው እንደነበር ታሪክ አስቀምጦላቸዋል።
ኢትዮጵያውያን በአደጋ ጊዜ እንዲህ ናቸው። መረዳዳት ባሕላችን መሆኑን እንዲህ ዓይነት የታሪክ አጋጣሚዎች ያሳዩናል። ባለሀብቶችና ተቋማት ላደረጉት ድጋፍ የተጠቀሱት የገንዘብ መጠኖች ከ18 ዓመታት በፊት መሆኑን ልብ እያልን። ከ18 ዓመታት በፊት ከባለሀብቶችና ከተለያዩ ተቋማት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ድጋፍ ማድረግ ትልቅ ነገር ነው።
በነገራችን ላይ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ‹‹በጎርፍ የተጎዱ ወገኖቻችን ሁሌም እናስባለን፤ ስጋቱንም ለመቀነስ ተግተን እንሠራለን›› በሚል መሪ ቃል ክስተቱን ያስታውሰዋል፤ በተለይም በ2008 ዓ.ም 10ኛ ዓመቱ ሲታወስ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የመንግሥት አካላት በተገኙበት ነው። ዳግም እንዲህ ዓይነት አደጋ እንዳይከሰት የጥንቃቄ ሥራዎች ይሰራሉ።
ከጥንቃቄዎች አንዱ ደግሞ ችግኝ መትከል ነው። የድሬ ነዋሪዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን እና የተለያዩ አካላት ተሳትፈውበታል። በየዓመቱ በችግኝ ተከላ ይታወሳል። ባለፉት ዓመታት ይህ ተጠናክሮ ቀጥሏል፤ በአንድ ቀን ብቻ ከ500 ሺህ በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
ዛሬ ያ የመከራ ጊዜ አልፏል። ‹‹አልፎ ለማዋየት ያብቃኝ›› ይላሉ አበው ችግር ሲያጋጥማቸው። አልፎ ለማዋየት ያብቃኝ ማለት ያጋጠማቸው ችግር አልፎ በታሪክነቱ ብቻ ማስታወስ ማለት ነው። ለዚህም ነው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ቀኑን ሲያስታውስ ‹‹‹በጎርፍ የተጎዱ ወገኖቻችን ሁሌም እናስባለን፤ ስጋቱንም ለመቀነስ ተግተን እንሰራለን›› የሚለው። ዳግም ችግሩ እንዳያጋጥም ሥራዎች ይሰራሉ ማለት ነው።
ለዚህም ችግኞች እየተተከሉ ነው። በድሬዳዋ በ5 ሚሊዮን ብር የተገነባ የችግኝ ጣቢያ አለ። በድሬዳዋ የሚዘጋጁ ችግኞች ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ ከጅቡቲ መንግሥት ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት የሚያጠናከሩ መሆናቸውም ተነግሯል።
የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የደን ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት በየዓመቱ ይህን ሥራ አጠናክረው እየሰሩ ነው። በየዓመቱ በሚካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ደግሞ የበለጠ ችግኞች ተተክለዋል ማለት ነው።
መጥፎ ታሪኮችን እንዲህ በበጎ መቀየር ይቻላል፤ ከዚህ በኋላ የድሬዳዋውን የጎርፍ አደጋ የምናስታውሰው በታሪክነቱ ብቻ ነው። ምክንያቱም ዳግም እንደዚያ ዓይነት አደጋ እንዳያጋጥም ተደርጓል። ሌሎች የተፈጥሮ አደጋ የሚያጋጥምባቸውን አካባቢዎችም እንዲህ ዓይነት የመከላከልና የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ሊሰሩባቸው ይገባል። ይህ ጥንቃቄ ተጠናክሮ ይቀጥል እንላለን።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም