የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ በሚችሉበት መልኩ ሊገሩ ይገባል

የሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ስብራት ውስጥ ስለመኖሩ በብዙ ተነግሯል። በተጨባጭም በየወቅቱ ዘርፉን በሚመለከት የሚወጡ/የሚሰሙ አስደንጋጭ መረጃዎችም ስለ እውነታው ተጨባጭነት ከመናገር አልፈው የጉዳዩን አሳሳቢነት በስፋት እያስገነዘቡ ነው። ችግሩን የሚሸከም ስትራቴጂክ መፍትሔ ማስቀመጥ ካልተቻለ የሀገሪቱ ነገዎች ላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ከባድ ስለመሆኑም ብዙ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ከመነሻው በበርካታ ችግሮች ውስጥ እያለፈ ስለመምጣቱ ብዙዎች ይስማማሉ፣ እንዲህም ሆኖ ግን የሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት የተጓዘባቸው የተጎረባበጡ መንገዶች፣ አሁን ላለው ስብራት በዋነኛ ምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው።

በርግጥ ለችግሩ፣ የመምህራን ብቃት፣ የትምህርት መሠረተ ልማቶች፣ የግብዓት አቅርቦት፣ ሥርዓት አልበኝነት … ወዘተ ተጠቃሽ ቢሆኑም፣ በተለይም በትምህርት ሥርዓቱ ላይ በየግዜው የሚስተዋለው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት፣ ከጥራት ይልቅ ብዛት ላይ የማተኮሩ እውነታ አጠቃላይ በሆነው የትምህርት ሥርዓቱ ላይ ትልቅ ፈተና ሆኖ ቆይቷል።

በዚህም የትምህርት ሥርዓቱ በትምህርት ላይ ጉልህ የሆነ ጥራት ሊያመጣ ሳይችል ቀርቷል። ኅብረተሰቡን ሊያገለግሉት የሚችሉ፣ የተሟላ ክህሎት እና እውቀት ያላቸው ተማሪዎችን ከማፍራት ይልቅ፣ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በፍጥነት አጠናቅቀው የምስክር ወረቀት እንዲይዙ የሚያበረታታ ሆኗል ።

ከዚህ የተነሳም በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ተቋሞቻችን በብሔራዊ ደረጃ በሚሰጡ ፈተናዎች፣ የሚያስመዘግቧቸው ውጤቶች አስደንጋጭ መሆናቸው የተለመደ ከሆነ ውሎ አድሯል፣ ይህም ተማሪዎች ለረጅም ጊዜ ጥራት ላይ ያተኮረ ትምህርት እያገኙ ስላለመምጣታቸው ተጨባጭ ማሳያ እየሆነ ይገኛል።

ለማሳያም በ2014 እና በ2015 ዓ.ም በድምሩ 1,741,619 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በመላው ሀገሪቱ ወስደዋል። ከእነዚህ ውስጥ ያለፉት በድምሩ 57,301 ተፈታኞች ብቻ ናቸው። ተማሪዎች በዚህ ልክ መውደቃቸው ዜጎችን ያስደነገጠ ነው፣ የፈተና አሰጣጡ በዚህ መንገድ ቢሆን ኖሮ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ መልኩ ፈተናውን የወሰዱ ተማሪዎች ውጤት ከዚህ እንደማይለይ መገመት አይከብድም ።

ውጤቱ የብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና በመሆኑ ብዙ ተባለለት እንጂ፣ በየደረጃው ያሉ ተማሪዎች ተገቢውን እውቀት አለመጨበጥ በተደጋጋሚ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የተስተዋለ እና የሚታወቅ ነው። ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ተወርዶ የተማሪዎች የንባብ፣ የጽሕፈት ክህሎት ሲፈተሽ አብዛኛው ከሚጠበቀው በታች እንደሚያገኝ በጥናት የተረጋገጠበት እውነታም ቢሆን የአደባባይ ሚስጥር ነው ።

በርግጥ በእነዚህ ሁለት ዓመታት በፈተናው ላይ የተለወጠ ነገር የለም። የተቀየረ ነገር ካለ እያንዳንዱ ተፈታኝ ኩረጃን በራቀ ሁኔታ የራሱን ፈተና ብቻ መሥራት የሚችልበት አሠራር ተግባራዊ መሆኑ ነው። የተቀየረው ፈተናው ሳይሆን፤ የፈተናው አሰጣጥ ነው።

የውጤት ልዩነቱም የመነጨው ከዚህ ተጨባጭ እውነታ ነው። ከዚህ በፊት፤ ፈተናዎች መታተም ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ በተደራጀ መንገድ የተሰረቀበት ሁኔታ ተስተውሏል። ኩረጃም ባሕል የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ፈታኞች በየክልሉ ሲሄዱ ትልቅ ግብዣ ተደርጎ ጉቦ ተሰጥቷቸው፣ ተማሪዎቹ እንዲኮራረጁ ይደረግ የነበረበትም ሁኔታ ሲስተዋል ቆይቷል።

ከዚህ ባለፈ ሰሞኑን ትምህርት ሚኒስትር ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ ዘንድሮ የመውጫ ፈተና ለመውሰድ ከተመዘገቡ 95 ሺህ 465 የግል ኮሌጆች ተማሪዎች ውስጥ 68 ሺህ 163 ተማሪዎች ፈተናውን ወስደዋል። ከነዚህ ውስጥ ፈተናውን ያለፉት 13 በመቶ ብቻ ሲሆኑ፣ 22 የግል ኮሌጆች ምንም ተማሪ አላሳለፉም።

በፈተናው 25 በመቶ ተማሪዎችን ማሳለፍ የቻሉት 29 የግል ኮሌጆች ብቻ ሲሆኑ፣ በመንግሥት ኮሌጆች 94 ሺህ ተማሪዎች ተመዝግበው 88 ሺህ 94 ተማሪዎች ፈተናውን ወስደዋል፣ ከተፈተኑት ተማሪዎች መካከል 58 በመቶ ማለፋቸው ተነግሯል ። ይህ እውነታ አጠቃላይ የሆነውን ሀገራዊ የትምህርት ስብራት በግልጽ የሚያሳይ ስለመሆኑ አንድ ሁለት የሚያስብል አይደለም ።

በርግጥ በግል ዩኒቨርስቲ/ኮሌጆች ያለው እውነታ ቀደም ሲል የሚታወቅ እና ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ቢሆንም አሁን በተጨባጭ በምዘና የታየው ውጤት፣ በግል ከፍተኛ ተቋማት ዙሪያ ተገቢውን ትኩረት እና ጠንካራ ክትትል ማድረግ ተገቢ እና የግድ መሆኑን በተጨባጭ ያመላከተ ነው።

እነዚህ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በእውቀት እና በክህሎት የበለፀገ ትውልድ በመፍጠር ሂደት ውስጥ ያለባቸውን ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት በሚችሉበት መንገድ ሊገሩ ይገባል። ይህንን ማድረግ ደግሞ ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የዛሬ የቤት ሥራቸው ሊሆን ይገባል!

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You