በአገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ዘርፈ ብዙ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ። በተለይ በፖለቲካው ረገድ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባትና በየደረጃው መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጭምር እውቅናና አድናቆት የተቸራቸው እንደሆኑ ይታወቃል።
በዚህም መሰረት በአገራችን ለአመታት የዘለቁ ችግሮች ሲፈቱ ቆይተዋል። ለምሳሌ ለውጡን ተከትሎ በእስር ላይ የቆዩ የፖለቲካ እስረኞች በምህረትና በይቅርታ እንዲፈቱ ተደርጓል፤ የመናገርና ሃሳብን በነጻነት የመግለፅ መብት ተግባራዊነት ተከብሯል፤ ከሃገር ውጭ ለሚገኙና በሽብርተኝነት ለተፈረጁት የፖለቲካ ሃይሎች ጭምር ምህረት ተደርጎ በሰላማዊ መንገድ አንዲታገሉ ሰፊ መድረክ ተሰጥቷል፤ የፖለቲካ ምህዳሩን ሊያጠቡ ይችላሉ የተባሉ ህጎች እንዲሻሻሉና ዜጎች በአገራቸው በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፤ …ሌሎችም በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።
በሌላም በኩል በአገሪቱ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ህግ አውጭው፣ ህግ አስፈጻሚውና ህግ ተርጓሚው አካላት ተቀናጅተው እንዲሰሩ ሰፊ የማስተካከያ ስራዎች ተሰርተዋል። ከዚህም ጎን ለጎን በተለያዩ ተቋማት ያለውን አሰራርና አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ተቋማትን ሪፎርም የማድረግ እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በዚህ ረገድ በተለይ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እየተከናወነ የሚገኘው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ተጠቃሽ ነው።
ከዚህም ጎን ለጎን በአገራችን በህገወጥ መንገድ የተደራጁ ሃይሎች ሙስና እንዲስፋፋ በማድረግ ሲያካሂዱ የነበረውን አሰራርና ሌብነት ለመቆጣጠር ሰፊ እንቅስቃሴ ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም መሰረት ላለፈው አንድ አመት በተለያዩ መንገዶች በተደራጀ ሁኔታ ሲፈፀሙ የነበሩ የሙስና ወንጀሎችና ኢሰብኣዊ ድርጊቶች እንዲታረሙ ለማድረግ መንግስት ከፍተኛ የማስተካከያ እርምጃ ወስዷል፤ እየወሰደም ይገኛል።
ከዚህም ባሻገር መንግስት ሃገራዊ አንድነትን ለመፍጠርና የዜጎች ሰብኣዊና ዴሞክራሲዊ መብቶች ተጠብቀው ሁሉም ዜጋ ለአገሩ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት የተለያዩ የአእምሮ ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በዜጎች መካከል ያለውን የቆየ የአብሮነትና የመቻቻል ባህልም ይበልጥ ለማዳበርና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጠረ ያለውን የዜጎች መፈናቀል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቀረት የተለያዩ የህዝብ ለህዝብ መድረኮች ሲካሄዱ ቆይተዋል።
በኢኮኖሚ ዘርፍም ቢሆን ባለፈው አንድ አመት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ተደርጓል። በተለይ በከፍተኛ ሁኔታ ያጋጠመውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቋቋምና ገበያውን ለማረጋጋት፤ በሂደትም የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚን ለመገንባት የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል። ከነዚህም ውስጥ አጋር አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ በማድረግና በብድር ችግሩን ለመፍታት የተሄደበት መንገድ አንዱ ሲሆን በሌላም በኩል ትላልቅ የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወደ ግል ይዞታ በማዘዋወር እና ትላልቅ የውጭ ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ በማድረግ ችግሩን የመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው።
በዲፕሎማሲ መስክም ቢሆን ባለፈው አንድ አመት የተከናወነው ስራ ስኬታማ ነው። በተለይ ለ20 አመታት የዘለቀውን የኢትዮ ኤርትራ ሞት አልባ ጦርነት እንዲያከትምና በሁለቱ አገር ህዝቦች መካከል በትብብር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲፈጠር የተሰራው ስራ ተጠቃሽ ነው። ከዚህም ጎን ለጎን ከሌሎች የጎረቤትና የአውሮፓ እንዲሁም የአሜሪካና ሌሎች ወዳጅ አገራት ጋር የተፈጠረው ጠንካራ ግንኙነት የለውጡ ትሩፋት ነው።
በዚህ ሂደት ውስጥም አገሪቱን ወደተሻለ የእድገት ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ። ከነዚህም ውስጥ አንዱ የክረምቱን መግባት ተከትሎ የተጀመረው የችግኝ ተከላ መርሃግብር ይጠቀሳል። በዚህ መርሃ ግብርም በመላ አገሪቱ አራት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል እቅድ ተይዞ ሰፊ ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል።
ከዚህም በተጨማሪ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመላ አገሪቱ ከአስር ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሰማራት የተለያዩ የልማት ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ። በመላ አገሪቱ የህግ የበላይነት ለማስከበር፣ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠርም መንግስት የጀመራቸው ዘርፈ ብዙ ስራዎች እንዳሉ ይታወቃል።
በሌላ በኩል መንግስት ያቀዳቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። በተለይ በተለያዩ ወቅታዊ ችግሮች እየተጎዳ የመጣውን የአገራችንን ኢኮኖሚ በማሻሻል የህብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታት ሰፊ ጥረት እያደረገ ይገኛል። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ በአገራችን በተለይ የግል ባለሃብቱን ተሳትፎ በማሳደግና በተለያዩ ዘርፎች የሚከናወኑ የልማት ስራዎች በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በተለይ በመጪው የምርት ዘመን ለግብርናው መስክ ልዩ ትኩረት በመስጠት በዘርፉ ከፍተኛ ስራ እድልን ለመፍጠርና ምርትና ምርታማነትንም ለማሳደግ ተጨማሪ 20 ቢሊየን ብር በጀት በመመደብ እየሰራ ይገኛል። ይህም በዘርፉ ያለውን ችግር ከመፍታትም በዘለለ በአገራችን የኢኮኖሚያዊ ሽግግር ሂደት ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚያመጣ ይጠበቃል።
በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተገነቡትና ወደስራ በመግባት ላይ የሚገኙትም የኢንዱስትሪ ፓርኮች በቀጣይ ለኢኮኖሚያዊ ሽግግሩ ትልቅ ትርጉም ያላቸው ናቸው። እነዚህ ፓርኮች የተፈለገውን ውጤት እንዲያስመዘግቡ ደግሞ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ነው።
በአጠቃላይ መንግስት የጀመራቸው የተለያዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች አገሪቱን ወደተሻለ የእድገት ደረጃ ለማስኬድ ትልቅ መስመር እየያዙ የመጡበት ሁኔታ እንዳለ ይታወቃል። በመሆኑም ይህ መንገድ እንዳይደናቀፍ እያንዳንዱ ዜጋ ሊያስብበት ይገባል። ሰሞኑን እንደአገር የገጠመን ችግርም ለአፍታም ቢሆን ሳያዘናጋን ፊታችንን ወደ ልማት በማዞር ለነገዋ የበለፀገች ኢትዮጵያ በየተሰማራንበት ዘርፍ ጠንክረን እንስራ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2011