የኢኮኖሚ አሻጥር በሚሠሩ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት!

አንድ ሀገር ወደ ከፍታ ማማ ልትሸጋገር የምትችለው በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የገጠማትን የኢኮኖሚ ስብራት ተረድታ ለዚያ የሚያስፈልገውን ፖሊሲ ማውጣት፣ አላሠራ ያለውን ፖሊሲ መከለስ ፣ ማሻሻል እና መተግበር ስትችል ነው። የሚወጡ ፖሊሲዎችን ወደ መሬት አውርዶ መተግበር ደግሞ ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ ግዴታ ይሆናል።

በኢትዮጵያ እስከ አሁን ያለው የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ተመንና ዝቅተኛ የዋጋ ንረት መኖሩን ለማረጋገጥ ያለመ ቢሆንም፣ በሂደት ግን ለጥቁር ገበያ መስፋፋት፣ ለከፍተኛ የዋጋ ንረት፣ በከበሩ ማዕድናት ለሚደረግ ሰፊ የኮንትሮባንድ ንግድ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ከባንክ ሥርዓት ውጭ እንዲሆንና ከሀገር እንዲሸሽ አንዱና ዋነኛ ምክንያት ሆኗል፡፡

ይህ ሁሉ ከአምራች ዘርፎች ይልቅ ጥቂት ሕገወጦችና ደላሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑና ሥር የሰደደ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲከስት አድርጓል፡፡ ከዚህም የተነሣ በርካታ የንግድ ድርጅቶችና ባለሀብቶች ተጎጂ ሆነዋል፤ የወጪ ንግድንና የፋብሪካ ምርቶችን ለማስፋፋት፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለማሳደግ የተቀመጡ ፖሊሲዎችንና ጥረቶችን ውጤታማነት ሸርሽሮታል፡፡

በመሆኑም መንግሥት ሀገሪቱ የገጠማትን ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ችግሮችን መፍታትና የተሻለ ዕድገትና ብልጽግና ማረጋገጥ የሚቻለው እስካሁን አሳሪ የሆኑ ፖሊሲዎችን ማየትና ማሻሻያዎች ማድረግ ሲቻል መሆኑን በግልጽ አስቀምጧል። ከዚህ በመነሳትም የሀገሪቱን ችግሮች በአብዛኛው የሚፈታ ጠንካራ የማይክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ማውጣት አስገዳጅ ሆኗል።

ይህም የፖሊሲ ማሻሻያ ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ ወደሆነና በገበያ ላይ ወደተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት እንደሚያሸጋግራትና በኢኮኖሚ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተንሰራፍቶ የቆየውን የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋትና መዛባት እንደሚያሻሽል ታምኖበታል፡፡ በሀገር ውስጥ ያለውን የውጪ ምንዛሬን እጥረት የሚቀርፍ ፣ የውጪ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ፣ ቱሪዝምን የሚያሰፋ፣ ኤክስፖርትን የሚያሳድግ ነው።

ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር በአንድ ጊዜ በአጭር ወቅት አልጋ በአልጋ ይሆናል ብሎ መጠበቅ አይቻልም። ኢኮኖሚው እስኪረጋጋ የሚያጋጥሙ መንገጫገጮች ይኖራሉ። የሽግግር ወቅቱን ተጠቅመው ለመክበር የሚሯሯጡ ሕገወጦች ይበረክታሉ። በዚህ ዙሪያ ቀድሞም እንደ ስጋት የተነሱና መፍትሔም የተቀመጠላቸው አቅጣጫዎች አሉ። እንደስጋት ከተነሱት መካከል አንዱ ሕዝቡ በተለይም አነስተኛ ገቢ ያለው የመንግሥት ሠራተኛና የመሳሰለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ሊያርፍበት ይችላል የሚል ነው።

ይሄንንም ግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት የመፍትሔ ርምጃዎች ያላቸውን አስቀምጧል። በተለይም አነስተኛ ገቢ ባላቸው ዜጎች ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጫና ለማቃለል መንግሥት ከውጭ የሚገቡ የአንዳንድ መሠረታዊ ሸቀጦችን እንደ ነዳጅ፣ ማዳበሪያ ፣ መድኃኒትና የምግብ ዘይት የመሳሳሉትን በጊዜያዊነት ይደጉማል። ይህም ከውጪ የሚገቡት በአንድ ጊዜ ሸማቹ ላይ ጫና እንዳያሳርፉ የሚያደርግ ሲሆን፤ ለመንግሥት ሠራተኛው ደግሞ የደመወዝ ማስተካከያ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ነው።

ይሄ ሀገርን በጋራ ለማሳደግ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስጋቶችን መፍትሔ በመስጠት ሀገርን ወደታለመው የዕድገት ደረጃ ማድረስና ልማቱን ማስፋፋት ጭምር ነው። ለዚህ ፖሊሲ ተግባራዊነትም ሁሉም ዜጋ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያለው መተባበር የውዴታ ግዴታ አለበት። ሀገር የሚገነባው በአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን በሁሉም ትብብር ነውና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በጋራ በመፍታት የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ መሥራት ይገባል።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ምርቶችን መደበቅ በንግዱ ማህበረሰብ በኩል ጎልቶ እየታየ ሲሆን፤ ሸማች አካባቢ ደግሞ የዓመት ቀለብ እስኪመስል ድረስ ሸቀጣ ሸቀጦችን ማግበስበስ ይታያል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ትልቁ የንግድ ማዕከል በሆነው መርካቶ እና አንዳንድ አካባቢዎች የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ይፋ ከተደረገ በኋላ አንዳንድ ነጋዴዎች በሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ሲያደርጉ፤ እቃ ሲደብቁ እና ላለመሸጥ ዘግተው ሲጠፉ ተስተውሏል።

በተለይ ዘይት እና የሕፃናት ወተት ላይ ከሦስት እስከ አምስት መቶ ብር፣ ወርቅ ላይ ደግሞ እስከ ሦስት ሺ ብር ጭማሪ ተደርጓል። ይሄ ተግባር በወገን ላይ የሚደረግ ጭካኔና አጉል ስግብግብነት እንጂ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም። በአንድ ጀንበር ከብሮ ለመገኘት የሚደረግ ሕገ ወጥ ድርጊት በመሆኑም ሊወገዝ ይገባል። በድርጊቱ ውስጥ የተሳተፉት አካላትም ላይ አስተማሪና የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል። በአንዳንድ ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ የመንግሥት አካላት እየተከታተሉ ርምጃ በመውሰድ ላይ ናቸው። ይሄ አስተማሪ ርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 30 /2016 ዓ.ም

Recommended For You