ሰው እና አካባቢ፣ አንዳቸው የአንዳቸው ስሪትና ውጤቶች ናቸው። ሰው አካባቢውን ይሠራል፤ አካባቢ ደግሞ የሰው ልጆችን ይቀርጻል። እናም ሰው እና አካባቢ/ከባቢ አንዳቸው አንዳቸውን የሚገልጹ፤ አንዳቸው የአንዳቸው ሰብዕናና ልዕልና ማንጸሪያ ሆነው የሚታዩ ናቸው።
ምክንያቱም በዚህ ረገድ ሰው ውብ ስፍራዎችን በፈጠረና ባሰፋ ቁጥር፤ ለራሱና ለማኅበረሰቡ የአዕምሮ ዕረፍትን፣ የዕይታ አድማስን፣ የማንሰላሰያ ዓውድን ፈጠረ ማለት ነው። ይሄ ጉድኝት ደግሞ በሰው እና በተፈጥሮ/አካባቢ መካከል መልካም የሆነ መስተጋብርን በመፍጠር፤ የሰው ልጅ በኑሮው የተረጋጋ፣ ደስተኛ እና ብሩህ የሆነን ነገ የሚያልም እንዲሆን ያደርገዋል። ካልሆነው ሁነቱም፣ ውጤቱም በተቃራኒው ነው።
ይሄን መሰሉ እውነት የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል፤ የአፍሪካ መዲና፣ የኢትዮጵያም መናገሻ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ የትናንት እና የዛሬ እውነት ሆነው ይገለጻሉ። ምክንያቱም አዲስ አበባ ትናንት በጓዳ ጎድጓዳዋ እልፍ የቆሸሹ መንደሮችን ብቻ ሳይሆን፤ የቆሸሹ እና እጅጉን ለጤናም ጎጂ የሆኑ የተበከሉ ወንዞችን ታቅፋ ዓመታትን ዘልቃለች።
ይሄ ገጽታዋ ታዲያ ከተማዋን የማይመጥን ብቻ ሳይሆን፤ ነዋሪዎቿንም ለዘርፈ ብዙ (ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነልቦናዊና የጤና ጉዳዮችን ጨምሮ) ችግሮች ተዳርገው ቆይተዋል። የበዙት የከተማዋ ነዋሪዎችም በተጎሳቆሉ ቤቶችና መንደሮች ውስጥ፣ ከተባይ፣ ከዝናብ፣ ከጎርፍ፣ ከፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎች፣ አለፍ ሲልም ለሞት ከሚያጋልጡ ክስተቶች ጋር እንዲጋፈጡ ሆነው ኖረዋል።
አዲስ አበባ ከስምና ክብሯ በታች በሆነ ገጿ ስትገለጥ፤ ነዋሪዎቿም የከተሜነት ኑሮ ናፍቋቸው፤ ውብና ፅዱ ስፍራ የመኖር መብት እንዳላቸው እንኳን የሚያውቁ እስከማይመስል ድረስ በቆሻሻና ጢሻ ተውጠው ከርመዋል። ታዲያ ከተማዋን ከስምና ከግብሯ ያፋታ፤ ነዋሪዎቿንም ከሰብዓዊም፣ ከሞራላዊም ክብር ያናጠበ እውነት የሆነ ቦታ ላይ መገታት ነበረበት። እናም ከለውጡ ማግስት በተለይም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሀሳብ አመንጪነት የተጀመሩት የከተማ ውበትና ፅዳት ሥራዎች፤ በኋላም የኮሪደር ልማት አስደማሚ ተግባራት መልስ በማግኘት ላይ ነው።
ምክንያቱም፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የበጎ ፈቃድ ተግባር ተከትሎ የተከናወኑ የተጎሳቆሉ መንደሮችን የማደስና የድሃ ቤቶችን የመሥራት ተግባር ሺዎችን የኑሮን ጣዕም እንዲያጣጥሙ ዕድል ሰጥቷል። በገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶች ታግዞ የተከናወነው የአንድነት ፓርክ፣ የወዳጅነት አደባባይ፣ የእንጦጦ ፓርክ፣ የወንዝ ዳር ልማትና ሌሎችም የከተማዋን ነዋሪዎች የንጹሕና ውብ አካባቢዎችን ከፍ ያለ ፋይዳ እንዲረዱ፤ በስፍራዎቹም አረፍ ብለው የተሻለ ነገርን እንዲያስቡ ዕድል ፈጥረዋል።
ከዚህ በኋላ የተተገበረው የኮሪደር ልማት ተግባር ደግሞ፣ የከተማዋን ስምና ገጽ መግለጥ የቻለ፤ የነዋሪዎቿንም ሞራል የቀሰቀሰና የተሻለ ነገርን አብዝተው እንዲሹ ዕድል የሰጠ ሆነው። በዚህም ነዋሪው እንደ ቀድሞው ያረጁ ቤቶች ሲፈርሱ፤ የተበላሹ ስፍራዎች ሲዘምኑ፤ የተጎሳቆሉ መንደሮች ለተሻለ ልማት ሲታጩ፤… ቅሬታ እና ክስ ከማቅረብ ይልቅ በደስታ ተባባሪ ሆኖ መሳተፍ ችሏል።
በኮሪደር ልማት ሥራዎች የታየውም ይሄው ነው። መንግሥት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለመለወጥ ሲል የጀመረው የተቀደሰ ተግባር እንደመሆኑ፤ ነዋሪዎቹም ይሄንኑ በመገንዘብ የልማቱ መሳለጥ ተባባሪም፣ ንቁ ተሳታፊም በመሆናቸው ነው በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅጉን ከፍ ያለ ውጤት የታየበት ተግባራትን ማከናወን የተቻለው።
የኮሪደር ልማቱ ለአዲስ አበባ ስምና ግብር የሚመጥን ብቻ ሳይሆን፤ በልኳም እንድትገለጥ ያደረገ ነው። ለነዋሪዎቿም ውብ ከባቢን፣ ንጹሕን ስፍራን፣ ለዓይን ማራኪ እና ለልብም እረፍትን የሚያጎናጽፉ አከባቢዎችን የፈጠረ ነው። እነዚህ አካባቢዎች የፒያሳን ጎስቋላ መንደሮች አድሰዋል፤ ለአራት ኪሎ አካባቢም የውበት ካባን አጎናጽፏል፤ ለግንፍሌና ቀበና መስመሮችን ሞገስን ቸረዋል፤ ለሜክሲኮና ሣርቤት ሰፈሮችም አንጸባራቂ መልክ ለግሰዋል።
ይሄ ተግባር በእነዚህ ስፍራዎች ብቻ አልተዋሰኑም፤ ከሰሞኑም የቦሌ ኮሪደር ላይ ተጨማሪ ውበትና ግርማን ያላበሰ ተግባር ተፈጽሞ አዲስ አበባን በከፍታ፤ ነዋሪዎቿንም በደስታ አስተሳስሯል። በወቅቱ “የአፍሪካ፣ የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ መግቢያ በር የሆነው የቦሌ መንገድ የኮሪደር ልማት ሥራችን ከተማችንን በሚመጥን ገጽታ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶችን አካትቶ ሌላ ብስራት እና ተጨማሪ ድል ሆኖ ተጠናቋል፤” ሲሉ የከተማዋ ከንቲባ ባስተላለፉት መልዕክትም ይሄንኑ የሚያረጋግጥ ነው።
እነዚህ የኮሪደር ልማት መስመሮች ሰፊ የመኪና፣ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገድ፤ የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንጎች፣ የታክሲ እና አውቶቡስ መጫኛ/ማውረጃዎች፣ የሕዝብ መናፈሻዎች፣ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ ፏፏቴዎች፣ የሕዝብ መፀዳጃ ስፍራዎች እንዲሁም የከተማዋን ፕላን የጠበቀ የቀለምና የመብራት ሥራን አካትተው፤ እጅግ በተዋበ መንገድም ገንብተን ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርገው ለሕዝቡ የተበረከቱ ናቸው።
ይሁን እንጂ እነዚህ ውብ ሆነው ለሕዝቡ የተበረከቱ የልማት ውጤቶችና ውብ ስፍራዎች ለሚፈለገው ዓላማ ይውሉ ዘንድን ከፍ ያለ ጥበቃን የሚሹ ናቸው። በመሆኑም እንዲህ ውብ ተደርጎ የተገነባውን መሠረተ ልማት መላው የከተማዋ ነዋሪ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በባለቤትነት መንፈስ ሊንከባከብ እና ሊጠብቃቸው፤ ከዚህ ጎን ለጎንም የሚመጥኑትን ሌሎች ውብና ፅዱ ከባቢዎችን በመገንባት ሂደት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም